አዲስ አበባ ከተማን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ ምክንያቱና ሥጋቱ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 24 2017በቅርቡ መሐል አዲስ አበባን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ ያደረሰዉ ጉዳት ነዋሪዎችን ተመሳሳይ አደጋ ይደገማል ለሚል ሥጋት ሲያጋልጥ፣የግንባታና የከተማ ይዞታ ጉዳይ ባለሙያዎችን ደግሞ እያነጋገረ ነዉ።ባለሙያዎች እንደሚሉት ወንዝ ላይ አነስተኛ ዉኃ መከተርያም ሆነ ግድብ ሲሠራ ፣ የወንዙን ተፋሰስ መጠን በማጥናት እና ከሜትሪዮሎጂ መረጃ በማስላት ያልተጠበቀ ጎርፍ ሲመጣ ማስተንፈሻ መንገዶችን አስቀድመው ማበጀት የግድ ይላል::የከተማይቱ አስተዳደር ባለስልጣናት በበኩላቸዉ ጎርፉ የደረሰዉ ዘንድሮ ያልተጠበቀ ከፍተኛ የዝናብ መጠን በመጣሉ ነዉ ባዮች ናቸዉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነህንጻ መምህር አርክቴክት ዮሃንስ መኮንን ከሰሞኑ መስቀል አደባባይ አጠገብ አቋርጦ በሚሄደው ጅረት ላይ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በወንዙ ላይ እየተከናወኑ ባሉ መከተሪያዎች (ግድብ) የጎርፍ መጠን ሲጨምር ማስተንፈሻ አማራጭ ስላልታሰበለትና መጠነኛ የስራ ላይ ክፍተት በማጋጠሙ ነው ይላሉ፡፡ ባለሙያው በሰጡት ሙያዊ ትንተናቸው፤ “ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ውሃ ከዚህ በፊት ይኖራል፤ ግን አሁን ሰሞኑን በምናየው መንገድ እያጥለቀለቀ ስታይ አዲስ ክስተት ነው” በማለት ተዳፋት ላይ ያለው የአዲስ አበባ አቀማመጥ ጎርፍ በፍጥነት ሳይተኛ ለማለፍ አመቺ በመሆኑ የጎርፍ ውሃ ለረጂም ጊዜ ከተማዋ ላይ የመቆየት እድል የለውም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ የጎርፍ አደጋ ለምን በረታ?
በቅርብ ጊዜ የሚታየው የመዲናዋ ጎርፍ ከከዚህ ቀደሙ የሚለይበት አራት መሰረታዊ እውነታዎች ያሉት ነው የሚሉት ባለሙያው የዝናብ መጠኑ በተጋነነ ልዩነት ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ከፍ ማለቱን ከሜትሮሎጂ መረጃዎች ማረጋገጥ መቻሉና በከተማዋ መንገድ ዳሮች የተሰሩ ውሃን የማያሰርጉ ኮንክሪቶች ለጎርፍ መጠኑ መጨመር አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡ እንደ ባለሙያው አስተያየት ሌላኛውም መንስኤ እነዚህ ናቸው፡፡ “አንዳንድ ቦታዎች ከሰሞኑ መኪኖችን አንሳፎ የታየው የጎርፍ አደጋ ደግሞ ከዲዛይን ችግርም ጋር የተያያዘ ነው” ያሉት ባለሙያው ከተማዋ ውስጥ አንዳነድ ቦታዎች ላይ ውሃ ከትሮ ለመያዝ ካለው ፍላጎት ጋር ተያይዞ በግድቦቹ ግንባታ ወቅት ከፍ ያለ ጎርፍ ስመጣ ማፋሰሻዎችን አስቀድሞ አለማዘጋጀት ለችግሩ ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ በመንገድ ላይ ያሉ የፈሳሽ መቀበያ ቱቦዎች በቂ የውሃ ማፋሰሻ እንዲቀበሉ አድርገው አለመሰራቱ ሌላው መንስኤ ነው ያሉት አርክቴክት ዮሓንስ በቂ ጥናት እና ክትትል በዚህም ላይ መደረግ ስገባው ክፍተት መታየቱ የጎርፍ አደጋን ለማስከተል መቻሉን በምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡
የዝናብ መጠን ከፍ ማለት ብቸኛው መንስኤ ነውን?
ከዚህ በተቃራኒ ግን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከሰሞኑ በመዲናዋ ላይ የተከሰተው የጎርፍ አደጋን ያስከተለው የሙያዊ ጥናት ጉድለት ሳይሆን በክረምቱ ወቅቱ በተከሰተ ከመጠን በላይ በሆነ ዝናብ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ “ከፍተኛ የበረዶ ዝናብ እየጣለ በተሸከርካሪ እስከማንሳት የቻልነውን ጨምሮ ጎርፍ ተከስቷል፡፡ ግን ከሰራናቸውና በጣም ከምንኮራባቸው ስራዎች የጎርፍ እና በተለያየ መንገድ የሚወገድ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓት ነው” ያሉት ከንቲባዋ ይህም በከተማዋ ታሪክ በእጅጉ የላቀ ስራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ስራዎቹም ዓለማቀፍ ባለሙያዎችን ጭምር አሳትፎ በሰፊ ጥናት እንደተከናወነ ጠቁመዋል፡፡
የሙያዊ ጥንቃቄ ጉድለት ከባለሙያዎች ሃሳብ አኳያ…
የኪነህንጻ ባለሙያዎች አርኪቴክት ዮሃንስ መኮንን ግን በአስተያየታቸው፤ “የከተማ አስተዳደሩ የእርምት ሃሳቦችን ተቀብሎ ተሳስተናል ከማለት ይልቅ ትችትን ሁሉ ማጣጣል ተገቢ ነው ብዬ አላምንም” ብለዋል፡፡ ባለሙያው እሳቸውን ጨምሮ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሚሰጡ ባለሙያዎች መልካም ስራ ያሉትን የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳር ልማትን ከመቃወም አኳያ ሳይሆን ያለበቂ ሙያዊ እገዛ በችኮላ የተሰሩ ስራዎች፤ አንዳንደ ሙያዊ ያልሆነ የአስተዳደራዊ ውሳኔ የታዩበት እንደመሆኑ የሚቀርብ እንጂ የባለሙያዎች አስተያየት ስራዎችን ከማጣጣል እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ “ለከንቲባ ጽህፈት ቤት ጨምር ምክረሃሳብ አቅርቤ አውቃለሁ” የሚሉት አርክቴክት ዮሓንስ ባለሙያዎች የሚያቀረቡትን ትችትና ሃሳቦችን ችላ በማለት የተሰሩ መንገዶች ጭምር በተደጋጋሚ ስፈርሱ መታየታቸውን እንደ ጉድለት መመልከታቸውንም አስረድተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ