አዲስ መንግስት የሚመሰርቱት የጀርመን ወግ አጥባቂና የመሀል ግራ ፓርቲዎች የተስማሙበት ውል
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 7 2017ወግ አጥባቂዎቹ የጀርመን ክርስቲያን ዴሞክራት እና የክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች CDU/CSU ከመሀል ግራው ከሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ SPD ጋር ተጣምረው መንግስት ለመመስረት ሲያካሂዱ የቆዩት ንግግር ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በስምምነት አብቅቷል። የካቲት 16 ቀን 2017 ዓም የተካሄደው የጀርመን ምርጫ አሸናፊ የ69 ዓመቱ ፍሪድሪሽ ሜርስ የዛሬ ሦስት ሳምንት ተሰናባቹን መራኄ መንግስት ኦላፍ ሾልስን ተክተው ስልጣኑን ይይዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና ሜርስ መራኄ መንግስት ከመሆናቸው በፊት ስምምነቱ በሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በSPD አባላት መጽደቅ ይኖርበታል። የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ግን ስምምነቱን አልቀበልም ሲል አስታውቆ ነበር። ሜርስ የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲም በተመሳሳይ ሁኔታ ከሁለት ሳምንት በኃላ በሚያካሂደው ጉባኤ ላይ ውሉን ማጽደቅ አለበት።
እነዚህ ከተከናወኑ በኋላ ከጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት 630 መቀመጫዎች 328ቱን የያዙት ተጣማሪዎቹ ፓርቲዎች ሜርስን መምረጥ ይችላሉ። ሜርስ ፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ባሳወቁበት ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት ስምምነቱ ለጀርመን ህዝብም ሆነ በአውሮጳ ኅብረት ውስጥ ላሉ የጀርመን አጋሮች ግልጽ ምልክት ሰጥቷል።
«ሀገራችንን እንደገና ወደፊት የምናራምድበት ጠንካራ እቅድ አለን። የጥምረቱ ስምምነቱ የጥልቅ ምክክር እና ድርድር ውጤት ነው። ከሁሉም በላይ ግን ለአገራችን ዜጎች በጣም ጠንካራ እና ግልጽ ምልክት ነው። በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ላሉ አጋሮቻችንም ግልፅ ምልክት ነው። ጀርመን እርምጃ መውሰድ የሚችል እና ለመስራት የሚያስችል ጥንካሬ ያለው መንግስት እያገኘች ነው።»
ከጥምር መንግስቱ ዓላማዎች ውስጥ የኤኮኖሚ እድገትን ማበረታታት የመከላከያ ወጪን ማሳደግ እና በስደተኞች ጉዳይ ላይ ከከዚህ ቀደሙ የበረታ እርምጃ መውሰድ ይገኙበታል። በየካቲቱ የጀርመን ምርጫ የስደተኞች ጉዳይ የህዝቡን ትኩረት ከሳቡት ውስጥ አንዱ ነበር። ሜርስ ከስምምነቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ አዲሱ ጥምር መንግስት ከከዚህ ቀደሞቹ መንግስታት በተለየ ጠንከር ያለ የስደት ፖሊሲ እንደሚያራምድ ተናግረዋል።
"በስደት ፖሊሲ ላይ አዲስ መንገድ እንከተላለን፣ በተሻለ ሁኔታ እናደራጀዋለን እንቆጣጠራለንም መደበኛ ያልሆነ ስደትንም በሰፋት እናስቆማለን፣ በብሔራዊ ድንበሮች ላይ ቁጥጥር ይደረጋል፤ የጥገኝነት ማመልከቻዎችንም ውድቅ እናደርጋለን። ወደ አገራቸው የመመለስ እርምጃዎችን እንወስዳለን ። በፈቃደኝነት ስደተኞችን የማስገባት መርሀግብርን እናቆማለን ፣ የቤተሰብ አባላትን እንደገና ማገናኘትን እናቋርጣለን ።»
የጀርመን ምክር ቤታዊ ምርጫና የጥምር መንግስት ምስረታው ጥያቄ
በባለ114 ገጽ የውል ስምምነት መሠረት ጀርመን በተለይ ወንጀለኛ እና አደገኛ የሚባሉ ስደተኞችን ወደ ሶሪያ እና አፍጋኒስታን ማባረር ትጀምራለች። በቅርቡ ይመሰረታል ተብሎ የሚጠበቀው የጀርመን መንግስት ተግባራዊ የሚያደርገው ጠንካራ የስደት ፖሊሲ በተለይ የትኛዎቹን ስደተኞች እንደሚመለከት የሕግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋን ለዶቼቬለ አስረድተዋል።
በውል ስምምነቱ የተሻሻለው ፈጣን የዜግነት አሰጣጥ ሕግም እንደገና ይቀይራል። በስምምነቱ መሠረት ከሦስት ዓመታት የጀርመን ቆይታ በኋላ የጀርመን ዜግነት ማግኘት ያስችል የነበረው ሕግ ከአሁን በኋላ ተግባራዊ አይሆንም። የውጭ ዜጎች የጀርመን ዜግነት ማግኘት የሚችሉት ጀርመን ውስጥ ለአምስት ዓመታት ከኖሩ ብቻ ነው።
የጀርመን መከላከያ ወጪን ማሳደግ አዲስ መንግስት የሚመሰርቱት ተጠማሪ ፓርቲዎች የተስማሙበት ሌላው ጉዳይ ነው። ይህም ጀርመን አባል የሆነችበት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት በምህጻሩ ኔቶ ፣ለአባል ሀገራት ካስቀመጠው የወታደሮችና የጦር መሣሪያዎች መጠን ጋር ለማስተካከል ታስቦ የተደረገ መሆኑ በስምምነቱ ተጠቅሷል።
የጀርመን ምርጫ ውጤትና የመንግሥት ምስረታ ጥረት
ተጣማሪዎቹ ፓርቲዎች እስካሁን በሰዓት 12 ዮሮ ከ82ሳንቲም የነበረው ዝቅተኛ የስራ ክፍያ ከጎርጎሮሳዊው 2026 ዓም አንስቶ ወደ 15 ዩሮ ከፍ እንዲል ተስማምተዋል። ከዚህ ሌላ ከጡረታ እድሚያቸው በኋላ የሚሰሩና ሌሎች ዝቅተኛ ደሞዝ ያላቸው ጨራተኞች የስራ ግብር ይቀነስላቸዋል። ስራ አጦች የሚያገኟቸው ጥቅማ ጥቅሞች ላይ ማሻሻያዎች ለማድረግ እና ለመስራት ፈቃደኛ ያልሆኑት ላይም ጠንካራ ማዕቀቦችን መጣልም በስምምነቱ ጠቅሷል።
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር