አንድ-ለአንድ፤ ከያደሳ ቦጂአ ጋር
ዓርብ፣ የካቲት 21 2017አንድ-ለአንድ፤ ከያደሳ ቦጂአ ጋር
አርቲስት ያደሳ ቦጂአ በተሰጦ የታደለ ነዉ ። ሰአሊ፤ ገጣሚ፤ ሙዚቀኛ፤ ብሎም የዘመናዊዉ የአሳሳል ዘዴ ግራፊክ ዲዛይነር ባለሞያ። አርቲስት ያደሳ ቦጃ በተለይ በተለይ የአፍሪቃ ኅብረት ሰንደቅ አላማን በመቅረጹ ከኢትዮጵያን አልፎ በአህጉሪቱ፤ ብሎም በዓለም ስሙ እና አገሩን ያስጠራ ሆንዋል። ሰሞኑን በአዲስ አበባ 38 ኛዉ የአፍሪቃ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ሲካሄድ፤ ኢትዮጵያ የአሁጉሪቱን እና የዓለም ተወካዮችን ስታስተናግድ ነበር። ኅብረቱም ያደሳ ቦጂአ የቀረፅዉን ሰንደቅ አላማ እያዉለበለበ መሪዎችን አስተናግዷል። አርቲስት ያደሳ ቦጂአ ምን ተሰምቶት ይሆን?
«በእዉነቱ እንደተከታተልነዉ በጣም የሚያኮራ ነዉ። አገራችንን በሚያኮራ መልኩ፤ አፍሪቃን እና የዓለም ተወካዮችን አስተናግዳ በጣም ጥሩ ጊዜ ያለፈ መሆኑን ያየንበት ነዉ። በእዉነቱ ኢትዮጵያ በአፍሪቃዉ ቀንድ የአፍሪቃ ዋናዋ ተሟጋች መሆንዋን ያሳየችበት ታሪክ በየጊዜዉ እየታየ መሆኑን ያየንበትም ነዉ። በዚያ ላይ ደግሞ እኔ የሰራሁት ባንዲራም፤ የአህጉሪቱ መለያ ሆኖ የበለጠ ጎልቶ የታየበት ጊዜም ነበር። ለነገሩ ዓመቱን በሙሉ በህብረቱ የሚታየዉ ይኼዉ ባንዲራ ነዉ። ግን ደምቆ እና በየቦታዉ ሲዉለበለብ ታይቷል። ይህ በእዉነቱ ያኮራል፤ ልብ ያሞቃል፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። ሁላችንም ያስሜት ሊሰማን ይገባል። ምክንያቱም ኢትዮጵያዉያን ለአፍሪቃ ኅብረት ብዙ ነገር አበርክተዋል፤ እያበረከቱም ነዉ።»
አርቲስት ያደሳ ለኅብረቱ ያንተ ስራ እንዴት ነዉ የተመረጠዉ እንዴት ተሰጠህ?
«ይህ ስራዬ፤ በመጀመርያ ደረጃ በአቅሜና እና ደረጃዬን ይዤ ያለ እግዚአብሔር ግቡን አላደርስም ነበር። ዉድድሩ ሲካሄድ በኔ በኩል ያለዉን ሁሉ ሰርቼ ላኩኝ። ግን እዚህ ደረጃ የደረሰበት ምክንያት አሁን የሚታዩትን ነገሮች ተንብዬ፤ አብሪ ጽፊ ስለነበረ ነዉ። በጽሑፊ ላይ ባንዲራዉን መስራት ወይም ዲዛይን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ ባንዲራዉ ምን ሊያመጣ ይችላል ፤ ወደፊት አፍሪቃ ወዴት ነዉ መሄድ ያለባት የሚለዉን፤ አብሪ አያይዤ ጽፊ ነበር። ይህ ባንዲራ የአፍሪቃን ንጋት የሚያበስር መሆን አለበት፤ አዲስ ምዕራፍ መክፈት አለብን፤ ከቅኝ ግዛት እና ከሌሎች ተላቀን አፍሪቃዉያን በራሳችን በመቆም ራሳችንን ከሌሎች ሰዎች እጅ ማዉጣት አለብን። ከእርዳታ ቀንበር ራሳችንን ማላቀቅ አለብን፤ የሚሉ ነገሮችን አያይዤ ጽፊ ነበር የላኩት። እና ይህ በመሪዎቹ ላይ ትልቅ ትኩረትን እንደጣለ እና በዚህም እንደተመረጠ ተገንዝቤያለሁ።»
አርቲስት ያደሳ ቦጂአ፤ የሰራዉን የህብረቱን ባንዲራ ተከትሎ የአፍሪቃ መንግሥታት አነጋግረዉህ ያዉቃሉ?
«በጣም ብዙ የአፍሪቃ መንግሥታት መሪዎች አግኝተዉ አነጋግረዉኛል። እንኳን ደስ ያለህም ብለዉኛል። ከኛ ከኢትዮጵያ ብጀምር፤ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፤ በክብር ቤቴ መንግሥት ጠርተዉ ደስታቸዉን ገልፀዉልኛል፤ አመስግነዉኛል። ከአፍሪቃ መሪዎች ዉስጥ የታንዛንያ መሪ የነበሩት፤ የቀድሞዉ የደቡብ አፍሪቃ መሪ ጠርተዉ አነጋግረዉኛል። ይህን የሰራሁትን የአፍሪቃ ኅብረት ባንዲራ ለመጀመርያ ጊዜ በኅብረቱ ግቢ የሰቀልነዉም፤ ከሊቢያዉ መሪ ከኮነሪል ሞአመር ጋዳፊ ጋር ነበር። በዝያ ጊዜ የወቅቱ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽነር ነበሩ። ጋዳፊ በአፍሪቃ ኅብረት የሰሩት የመጨረሻ ስራ፤ አዲሱን የአፍሪቃ ኅብረት ባንዲራን መስቀል ነበር። እኔም ከጋዳፊ ጎን ቆሜ ነዉ ባንዲራዉ የተሰቀለዉ። ባንዲራዉ ወደ 53 የሚሆኑ ሃገራት መሪዎች በተገኙበት ነበር የተሰቀለዉ። በዚህም በጣም ብዙ የአፍሪቃ መሪዎች ደስታቸዉን ገልፀዉልኛል። በወቅቱ የተመድ ዋና ፀኃፊ የነበሩ ባንኪሙንም በስብሰባዉ ላይ ታድመዉ ነበር።»
አርቲስት ያደሳ ቦጂአ አንተ ለአፍሪቃ ኅብረት በቀረፅከዉ ባንዲራ ስር ፤ ዛሬም በኮንጎ፤ በሱዳን፤ በኢትዮጵያ ግጭት ጦርነት ግድያ አፈና ሙስና ይካሄዳል። እና ይህ ባንዲራ ወቅታዊዉን የአሁጉሪቱን ገጽታ ይገልፃል ትላለህ?
«በእዉነቱ ባንዲራዉ የአፍሪቃ ዘላቂ መፍትሔ፤ ሰላም እና እርስ በእርስ መረዳዳት ፤ መደጋጋፍ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነዉ። በአፍሪቃ ዉስጥ በየጊዜዉ እንደምናየዉ በየቦታዉ ግጭት፤ አላስፈላጊ የሆነ ንትርኮች እና ዉድመትን ነዉ። ዉጤቱ በመጨረሻ ዜሮ ነዉ። በዚህ አካሄድ ምንም ጥሩ እና ወደ አደገ ቦታ አያደርሰንም። እና የሚያዋጣን ሰላም እና ፍቅር መከባበር ነዉ። የሚያዋጣን አንዳችን ለአንዳችን መቆርቆር እንጂ፤ እርስ በራስ መጋጨት፤ ራሳችንን ከመጉዳት በስተቀር ማናችንንም ወደፊት የሚያመጣ አይሆንም። ስለዚህ ይህን ማለፍ ስላለብን ይመስለኛል አሁን በዚህ ወጀብ ዉስጥ እያለፍን ያለነዉ። ግን ወደፊት ልክ ባንዲራዉ ላይ እንደተሳለዉ፤ አፍሪቃ ወደ ሰላም ወደ ብርሃን፤ ወደ አንድነት፤ እና መፈቃቀር ያመራታል የሚል እምነት አለኝ። ምኞቴም እሱ ነዉ። ነገር ግን በምንም አጋጣሚ ባለን ሁኔታ በሙሉ፤ ለፍቅር ለሰላም ለኅብረት፤ ለመዋደድ እና ለመከባበር መስራት አለብን የሚል እምነት ነዉ ያለኝ።»
አርቲስት ያደሳ ቦጂአ፤ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ትገመግመዋለህ። በተለያዩ ክልሎች ግድያ ግጭት አፈና እንዳለ በየጊዜዉ ይዘገባል?
«ይህንንም ቀደም ሲል ተናግሪዋለሁ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያየነዉ ግጭት የትም አላደረሰንም። ከግጭት ዉዝግብ ያገኘነዉ ምንም ነገር የለም። እስካሁን ድረስ ጊዜያችንን ያሳለፍነዉ በማይረቡ ግጭቶች ነዉ። አሁን የግድ ወደ ሰላም መመለስ አለብን። ምክንያቱም በሃይል ስልጣን እንደማይያዝ አዉቀናል፤ በሃይል ማሸነፍ እንደማይቻል ተረድተናል። ግን በመሃል ላይ እያለቀ ያለዉ ደሃዉ ህዝብ ነዉ። እየፈረሱ ያሉት መተካት የማንችላቸዉ መሰረተ ልማቶች ናቸዉ። ኑሮ የተወደደዉ በግጭቶቻችን ምክንያት ነዉ። ስለዚህ ግጭቶቹን መቆማ እና ወደ ሰላም መመለስ አለብን። ይህ ካልሆነ በሰላም መኖር አንችልም።»
አርቲስት ያደሳ በሙዚቃ ስራህ በአገር ዉስጥም በዓለም አቀፍም ደረጃ እዉቅናን ያገኘ ነዉ። ሙዚቃዎቹ ሰብዓዊ መብትን የሚያቀነቅኑ፤ ስለ ስደተኞች ጉዳይ ድምፅ የሚሆኑ እና ሰላምን የሚሰብኩ ናቸዉ። ከ30 ዓመት በላይ በኖረበት በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘዉ አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር የስደተኞችን ጉዳይ አሳሳቢ እንዳደረገዉ ያደሳ ተናግሯል። አሜሪካ የተገነባችዉ እና የተገኘችዉ በስደተኞች ነዉ የሚለዉ አርቲስት ያደሳ፤ አሁን ስደተኞችን እየታሰሩ መባረራቸዉን ማየቱ በጣም የሚያሳዝን እና አንገት የሚያስደፋ ነዉ፤ ሲል ገልፆታል። ይሁንና ይህን ፀረ-ሰብዓዊ ድርጊትን በጥበቡ ለመታገል ስራ ላይ እንደሆነ አርቲስት ያደሳ ተናግሯል።
ከአርቲስት ያደሳ ቦጂአ ጋር ያደረግነዉን ሙሉ ቃለ ምልልስ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር