አንድ - ለ - አንድ፣ ኢትዮጵያ «የኃይል እጥረት የለም፣ መብራት ግን ይቆራረጣል» ባለሙያ
ዓርብ፣ ሚያዝያ 10 2017ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታስገነባዉግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በሚቀጥሉት 6 ወራት ዉስጥ እንደሚጠናቀቅ እየተነገረ ነዉ።ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከ6000 ሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይችላል ተብሎ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።ግድቡ እስካሁን ድረስ በአምስት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት ቢጀምርም ርዕሠ-ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አሁንም የኃይል መቆራረጥና እጥረት በሰፊዉ ይታያል።የግድቡ ግንባታ ሲጀመር በኢትዮጵያ ዉኃ፣መስኖና ኃይል ሚንስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት አቶ ፈቂአሕመድ ነጋሽ ኑሩ እንደሚሉት ግን ኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር እጦት እንጂ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር የለባትም።አቶ ፈቂአሕመድ የዛሬዉ የአንድ ለአንድ ዝግጅት እንግዳ ናቸዉ።ነጋሽ መሐመድ አነጋግሯቸዋል።
ባለፈዉ ሳምንት ደወልኩላቸዉ።ከሰላምታ ልዉዉጥ በኋላ፣ ወደ ጉዳዬ ልገባ ሥል ግን «ሞባይሌ ባትሪ እየጨረሰ ስለሆነ ማታ ደዉልልኝ» አሉኝ።
«ለምን» ጠየቅኩኝ።
«እኛ ጋ መብራት ከጠፋ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑ» መለሱ።
መሸ።ደወልኩኝ።ጠየቅኋቸዉም «አሁን መብራት መጣ?»
«አዎ አንድ ሰዓት ላይ ነዉ የመጣዉ።» መለሱ።አቶ ፈቂ አሕመድ ነጋሽ ኑሩ።
የዉሐ ሐብት አስተዳደር፤ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች፣ የሐድሮ ዲፕሎማሲ ባለሙያ አማካሪ ናቸዉ።ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያስገነባችዉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሕዳሴ ግድብ የዓለም ርዕስ በነበረበት ዘመን በኢትዮጵያ የዉኃ ሐብት፣ የመስኖና የኃይል ሚንስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ኃላፊ ነበሩ።ኋላ የአባይ ተፋሰስ ኢንሼቲቭ (Nile Basin Initiative) የምሥራቅ አፍሪቃ ዋና አማካሪም ነበሩ።
ከያኔ እስካሁን የዉኃ ሐብትና አጠቃቀምን፣ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ጉዳይ ከሁሉም በላይ የሕዳሴ ግድብን የዉኃ ይዘት፣ የግብፆችን ሥጋት መሠረተ ቢስነት፣ ግድቡ የሚያመነጨዉ ኃይል የሚኖረዉን ፋይዳ በተመለከተ በሚሰጡት ሙያዊ ማብራሪያና ትንታኔ እናዉቃቸዋል።አቶ ፈቂአሕመድ «ግድቡ መጀመሪያ ከተያለት ጊዜ በላይ ብዙ ዓመታት መፍጀቱን 10ና 11 ዓመቱን «ተፈጥሯዊ» ይሉታል።ከዚያ በላይ ያለዉን ግን «ዘግይቷል።»
የግብፆችን ሥጋትና ማስጠንቀቂያም «የሚጠበቅ ግን የምዕራባዉያንን ሥሥ ብልት ለማግኘት እንደ ካርታ የተጠቀሙበት« ይሉታል።አቶ ፈቂአሕመድ የግድቡ ግንባታ «ወደ ግብፅ የሚፈሰዉን የዉኃ መጠን አይቀንሰዉም» በማለት አበክረዉ ሲከራከሩ ነበሩ።አሁንም በአቋማቸዉ እንደፀኑ ነዉ።«ባሁኑ ወቅት የሕዳሴ ግድብ ሙሉ ነዉ» አሉ ቀጠሉም «የአስዋን ግድብ ሙሉ ነዉ» እያሉ ቀጠሉ።
ግድቡ በከፊል አገልግሎት እየሰጠ (ኃይል እያመነጨ) ነዉ።የአቶ ፈቂአሕመድ ሰፈር ነዋሪ ግን እንደ አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ አሁንም «መብራት ሔደች፣ መጣች» ይላል።ለምን?
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር