አሳሳቢዉ የኮሮና ስርጭት በጀርመን
ሐሙስ፣ ኅዳር 24 2013ማስታወቂያ
በጀርመን በኮሮና ተኅዋሲ ወረርሽኝ የሚሞተዉ ሰዉ ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መጥቶአል ሲል በሃገሪቱ የተዛማች ተኅዋሲ ተቋም አስጠነቀቀ። ሮበርት ኮህ የተባለዉ እና የተዛማች ተኅዋሲ ጉዳዮችን የሚያጠናዉ ተቋም ዛሬ ይፋ እንዳደረገዉ ጀርመን ዉስጥ በኮቪድ 19 ባስከተለዉ ሕመም ባለፈዉ 24 ሰዓት ዉስጥ ብቻ 479 ሰዎች ሞተዋል። ባለፉት 24 ሰዓታት 22,046 ሰዎች በተኅዋሲዉ ተይዘዋል። በጀርመን በተለይ በአዛዉንቶች መኖርያ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ነዉ ፣ የሕክምና እና የጤና ተቋማት ዉስጥ የሚገኝ የሕሙማን ማስታመምያ አልጋዎች እና ቦታዎች ከአቅማቸዉ በላይ ሰዉ ተቀብለዋል አልያም በሕሙማን ሞልተዋል ሲል ዛሬ የጥናት ተቋሙ ከቀትር በፊት መረጃዉን ይፋ አድርጓል። ባለፈዉ ሰሞን በጀርመን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ከአለፈዉ አንድ ወር ጀምሮ ሆቴሎች ቡና ቤቶች የመዝናኛ እና የእስፖርት እና የመዋኛ የመሳሰሉ የማኅበረሰብ የጋራ መገልገያ ተቋማት እስከ ጥር 10 ቀን 2021 እንዲዘጉ ሲሉ ማራዘማቸዉ ይታወቃል።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ