ትግራይ ክልል የእርስበርስ ግጭት እንዳይከሰት ሥጋት መፈጠሩን የሲቪክ ተቋማት ገለጹ
ሐሙስ፣ ሰኔ 5 2017በትግራይ ክልል 'አንዣበበ' ያሉት የእርስበርስ ግጭት ስጋት እንዲቀረፍ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሊሠራ ይገባል ሲሉ ሁለት ሲቪክ ተቋማት ባወጡት መግለጫ ጥሪ አቀረቡ። ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች እና የዴሞክራሲና ማኅበራዊ ፍትህ ድምፅ የተባሉ ሁለት ሲቪክ ተቋማት እንደሚሉት በትግራይ ክልል እየተተስተዋሉ ባሉ ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት በክልሉ የእርስበርስ ግጭት እንዳይከሰት ሥጋት ተፈጥሮ እንዳለ አመልክተዋል። የመቐለ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ተጨማሪ አለው ።
በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ የጋራ መግለጫ ያወጡት ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች እና የዴሞክራሲና ማሕበራዊ ፍትህ ድምፅ የተባሉ ሁለት ሲቪክ ተቋማት እንደሚሉት በትግራይ እየተተስተዋሉ ባሉ ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት በክልሉ የእርስበርስ ግጭት እንዳይከሰት ስጋት ተፈጥሮ እንዳለ ያመለክታል። ይህ አደጋ ደግሞ አሳሳቢ እና የትግራይ ክልል ሕዝብ ሊቋቋመው የማይችል ነው ያሉት እነዚህ ሲቪክ ተቋማት ሊከሰት የሚችል ብለው የሰጉት ግጭት ለማስቀረት በትግራይ ያሉ ሁሉም አካላት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ የግጭት ስጋት ዙርያ ማብራሪያ የሰጡን መግለጫው ካወጡት መካከል የሆኑት የዴሞክራሲና ማሕበራዊ ፍትህ ድምፅ ስራ አስከያጅ አቶ መልአኩ ሃይሉ፥ የትግራይ ሐይሎች ወታደራዊ መኮንኖች ባለፈው ጥር 15 ቀን 2017 ዓመተምህረት ለአንድ የፖለቲካ ሃይል ደግፈው ካወጡት መግለጫ ወዲህ እንዲሁም ቀጥሎ የቀድሞ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር 'በሐይል' ከስልጣን ከተወገደ በኃላ በትግራይ ሐይሎች መካከል መከፋፈሎች መፈጠራቸው ያነሳሉ። ይህ ክፍፍል ሌላ ታጣቂ ሐይል እንዲፈጠር፥ የአደገኛ ግጭት ስጋት እንዲኖርም ማድረጉ ገልፀዋል።
የትግራይ ኃይሎች አባላት የነበሩ ታጣቂዎች እንዲሁም ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፥ የተለየ ፖለቲካዊ አመለካከት በመያዝ በትግራይ አለ ያሉት ስርዓት ለማስወገድ በአፋር እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ራሳቸው እያደራጁ መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ በቅርቡ ተናግረው የነበሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ በማንኛውም ፖለቲካዊ ልዩነት በሰላም መፍታት ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።
ጀነራል ታደሰ "ከሰላም ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም። ይህ ሆኖ እያለ ትጥቅ ማንሳት ሜዳ መውረድ የመሳሱ ትመለከታለህ። ይህ ከችግሮቻችን መካከል አንዱ ነው። ማንኛውም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ይቻላል። ከሰላማዊ መንገድ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም። ፋሺዝም የለም፣ በሀይል ካልሆነ በሰላም ሊወገድ አይቻልም የሚባል ነገር የለም፣ ሰላም እስካለ ድረስ ሁሉም ችግር ሊፈታ ይችላል" ብለዋል።
ጀነራሉ ጨምረውም ፖለቲካዊ ልዩነቶች በኃይል የመፍታት ባህል ሊቀር ይገባል ሲሉም ገልፀዋል። በጋራ መግለጫ ያወጡት እና ስጋታቸው የገለፁት ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች እና የዴሞክራሲና ማሕበራዊ ፍትህ ድምፅ በበኩላቸው ይህን ያንዣበበ የእርስበርስ ግጭት ስጋት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረታቸው እንደሚቀጥሉ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል። የዴሞክራሲና ማሕበራዊ ፍትህ ድምፅ ስራአስኪያጅ አቶ መልአኩ ሃይሉ፥ በተለይም የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ይህን ችግር ለመቅረፍ አካታች እና አቃፊ ሊሆን ይገባዋል ይላሉ።
በዚህ ጥሪ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች በአፋር ክልል አሉ ከተባሉ የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች አባላት መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ህወሓት በቅርቡ አውጥቶት ነበረ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት የፈረመው የፕሪቶርያ ውል ከማክበር በተቃራኒ ትግራይ የሁከት ማእከል ለማድረግ እየሰራ ነው ብሎ መክሰሱ አይዘነጋም።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ