ትኩረት በአፍሪቃ፤የሱዳን መከላከያ ጦር ድል፣ የሩሲያ ተፅዕኖ በአፍሪቃ
ቅዳሜ፣ መጋቢት 13 2017የሱዳን መከላከያ ጦር ድል የፈጥኖ ደራሹ ጦር መጨረሻ-መጀመሪያ ይሆን?
ቻተም ሐዉስ የተሰኘዉ የብሪታንያ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ሊና በድሪ «የሱዳንን ጦርነት በተመለከተ ቀጥሎ የሚሆነዉን ነገር አስቀድሞ መገመት የምትችል አይመስለኝም።» አለች-በቀደም።አላበለችም።
ረመዳን ነዉ።የሙስሊሞች ቅዱስ ወር።የሱዳን ተፋላሚዎች በዚሕ በተከበረ ወር ተኩስ እንዲያቆሙ፣ በጦርነቱ ለተጎዳዉ ህዝብ ርዳታ ይደርስ ዘንድ እንዲፈቅዱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽን ጨምሮ ብዙ ፖለቲከኛ-ዲፕሎማቶች ደጋግመዉ ጠይቀዋል።የተፋላሚ ኃይላቱ መሪዎች ጥያቄዉን ዉድቅ አድርገዉ አንዳቸዉ ናይሮቢ ላይ ለትይይዩ መንግሥት ምሥረታ፣ ሌላቸዉ ካይሮ ላይ ለፀረ-ትይዩ መንግሥት ዘመቻ ሲታደሙ ዉጊያዉ ለመቀጠሉም፣ የሱዳን ሕዝብ ስቃይ ሰቆቃ ለመጨመሩም ፍንጭ መሆኑ ለብዙ ተንታኞች በርግጥ አላጠራጠረም ነበር።
ይሁንና ብዙ ተንታኞች፣ ሊና በድሪ እንዳለችዉ የዘነጉት ጦርነቱ ሐቻምና ሚያዚያ በተጫረበት ሥፍራ ካርቱም ፕሬዝደንታዊ ቤተ-መንግሥት ለሁለተኛ ዓመቱ ሳምታት ሲቀሩት ትናንት የሆነዉ እስከሚሆን ድረስ መገመት አለመቻላቸዉ ነዉ።
አንጋፋዉ ቤተ መንግሥት-የድል ሽንፈት አብነት
በ1820ዎቹ ማብቂያ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) አል ሒክማንደር በጭቃ፣ በ1899 ፊልድማርሻል ሔርበርት ኪችነር በድንጋይ ያስገነቡት፣ በ2015 ዑመር አል በሽር በዘመናይ አብነበረድ እንዳዲስ ያሳነፁት የካርቱም ቤተ-መንግሥት ኃይለች እንደተፈራረቁበት-- ሥሙንም እንቀያየሩለት ዘመናት አስቆጥሯል።
ሚያዚያ 15፣ 2023 ኃይለኛዉ፣ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ነበሩ።ጦራቸዉ ቤተ-መንግሥቱን በቀላሉ ተቆጣጠረ።ዘንድሮ ትናንት ግን የሁለት ዓመቱ ታሪክ ተቀየረ።የሱዳን መከላከያ ጦር ቤተ መንግሥቱን መልሶ ያዘ።
«አላሁ አክበር-ይላል ወጣቱ ሻምበል።የረመዳን ወር 21ኛዉ ቀን፣ ማርች 21ናዉ ቀንም ነዉ።ይሕ የሪፐብሊካን ቤተ-መንግሥት ነዉ።»
የፈጥኖ ደራሹ ጦር ትናንት ማርፈጃዉ ላይ ባወጣዉ መግለጫ ቤተ-መንግሥቱን ለመያዝና ላለማስያዝ የሚደረገዉ ዉጊያ አላበቃም ብሎ ነበር።ፈጥኖ ደራሹ ጦር በመግለጫዉ «የዳኢሽ አባላትና ቅጥረኞችr ባላቸዉ በሱዳን መከላከያ ጦር ባልደረቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አስታዉቆም ነበር።
የሱዳን መከላከያ ጦርም «አሸባሪና የዳግሎ ሚሊሺያ» ካለቸዉ የፈጥኖ ደራሽ ታጣቂዎች ጋር ወታደሮቹ ከፍተኛ ዉጊያ ገጠመዉ እንደነበር አልካደም።የመከላከያ ጦር አዛዦች እንዳሉት ወታደሮቻቸዉ የፈጥኖ ደራሽ ጠላቶቻቸዉን እየደመሰሱ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲቃረቡ በሰዉ አልባ አዉሮፕላን በተሰነዘረባቸዉ ጥቃት ሶስት የመንግስት ጋዜጠኞችና በርካታ ወታደሮች ተገድለዋል።
የመጨረሻዉ ድል ግን የጄኔራል አብዱልፈታሕ አል ቡርሐን መሆኑን የሱዳን መከላከያ ጦር ቃል አቀባይ ብርጌድየር ጄኔራል ነቢል አብደላሕ አረጋግጠዋል።
«ኩሩዉና ፅኑዉ ሕዝባችን ሆይ! ምንግዜም ሕያዉ በሆነዉ የጀግኖች ተጋድሎ ታሪካቸዉ የደመቀዉ ኃይሎቻችን ዛሬ በካርቱም ግንባር ሌላ የጀግንነት ዘዉድ ደፍተዋል።ማዕከላዊ ካርቱም ዉስጥ አሸባሪዉን የአል ዳግሎ ሚሊሻ ቅሪቶችን ደምስሰዉ የአረብ ገበያን፣ የሪፐብሊካን ቤተ-መንግሥትን እና የሚንስትሮችን ፅሕፈት ቤቶች ተቆጣጥረዋል።ይሕ ድል ለፅኑዉ ሕዝባችን መታሰቢያ ነዉ።ድሉ እስኪሟላና የሐገራችን እያንዳዷ ጋት ከሚሊሻዎችና ከደጋፊዎቻቸዉ እስኪፀዳ ድረስ፣ በሁሉም የጦር ግንባር የምናደርገዉ ትግልና ይቀጥላል።»
የፈጥኖ ደራሹ ጦር አደገኛ ርምጃ
የሱዳን መከላከያ ጦር ባለፉት ተከታታይ ወራት በተደረጉ ዉጊያዎች ጠላቱን ድል እያደረገ የተለያዩ ከተሞችን ተቆጣጥሯል።ይሁንና የፈጥኖ ደራሹ ጦር በተለይ ምዕራባዊ ሱዳን ግዛት ዳርፉር ዉስጥ በበርካታ አካባቢዎች ያለዉን ይዞታ እያጠናከረ ነዉ።
ታዛቢዎች እንደሚሉት ፈጥኖ ደራሹ ጦር በቅርቡ ኬንያ ዉስጥ SPLM-N Al-Hiluን ከመሳሰሉ አማፂያን ጋር የትይዩ መንግስት ለመመስረት መስማማቱ በሱዳን ደቡባዊ ግዛትም ለመንቀሳቀስ ይረዳዋል።የትይዩ መንግሥት ምሥረታዉ ሱዳንን ለሁለት የሚገምስ ጣጣ ማስከተሉ እንደማይቀርም እየተነገረ ነዉ።ብቻ ሱዳን፣ ሱዳናዊቱ ተንታኝ እንዳለችዉ፣ አሁን ለተንታኝ ግምት አስቸጋሪ ሆናለች።
የሩሲያ ተፅዕኖ በአፍሪቃና የተቃራኒዎችዋ ሥልት
ሩሲያ በአፍሪቃ ሐገራት ላይ የምታደርገዉ ተፅዕኖ እየጠነከረ ነዉ።የዶቸ ቬለዉ ዳቪድ ኤሕል እንደሚለዉ የሩሲያን ተፅዕኖ ማቆም አልተቻለም።የአፍሪቃ መንግሥታት በሚያደርጉላቸዉ ጥያቄና ግብዣ መሠረት በተለያዩ የአፍሪቃ ሐገራት የሚሠፍሩት የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ቁጥር እየጨመረ ነዉ።
ቅጥረኛ ወታደሮቹ ከአፍሪቃ የሚወስዱት ወርቅን የመሰለ ዉድ ማዕድንና የጣዉላ ግንድ መጠንም እየጨመረ ነዉ።GI በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የድንበር ተሻጋሪ የተደራጀ ወንጀል ጉዳይ አጥኚ ተቋም ተንታኝ ጁሊያ ስታይንያርድ እየጨመረ የመጣዉን የቅጥረኛ ወታደሮች ቁጥርንም ሆነ የሚዘርፉትን ሐብት መጠን በአሐዝ አይጠቅሱም። ግን «ብዙ» ይሉታል።
«ከጥቂት ዓመታት በፊት በተመዘገበዉ መሠረት ሱዳን ዉስጥ በሰፈሩባቸዉ አካባቢዎች የሚገኙ ወታደራዊ አዉሮፕላን ማረፊያዎችን በመጠቀም በርካታ ወርቅ ከሐገሪቱ አስወጥተዋል።ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክና ማሊ ከሚገኙ የማዕድን ሥፍራዎችም ተመሳሳይ ነገር ማድረጋቸዉ ታይቷል።ከየደረሱባቸዉ ሐገራት የተፈጥሮ ሐብትን በድብቅ ለማስወጣት ጠንካራና ትልቅ ሚና አላቸዉ።»
ሐብት በድብቅ የማጋዙ ሚስጥር ከመዉጣቱ በተጨማሪ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ባለፈዉ ዓመት ሐምሌ ሰሜን ማሊ ዉስጥ ከሸመቁት የትዋሬግ አማፂያን ጋር በገጠሙት ዉጊያ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።ባለፈዉ ታሕሳስ በሩሲያ የሚደገፈዉ የሶሪያ ፕሬዝደንት የበሽር አል አሰድ መንግሥትም በጠላቶቹ ተሸንፏል።
እነዚሕ፣ የሐብት ማጋዝና የሽንፈት ዜናዎች ሩሲያና የወታደሮቿ አፍሪቃ ዉስጥ የነበራቸዉን ስምና ዝና ማደብዘዙ አልቀረም።ዕዉነታዉ ግን ተቃራኒ መሆኑ እንጂ ዚቁ። የየሐገሩ ሕዝብ ለሩሲያ ያለዉ ፍቅርና ድጋፍ እየጨመረ፣ ብዙ መንግሥታት ከቀድሞ ቅኝ ገዢ ከምዕራባዉያን መንግሥታት እየራቁ ከፑቲንዋ ሩሲያ ጋር ወዳጅነታቸዉን እያጠናከሩ ነዉ።
የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮችን ተፅዕኖ እንዴት መቀነስ ይቻላል?
የድንበር ተሻጋሪ የተደራጀ ወንጀል ጉዳይ አጥኚ ተቋም GI እንደሚለዉ የሩሲያን ቅጥረኛ ወታደሮችን ተፅዕኖ ለመቋቋም የአፍሪቃ መንግስታትና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ተባብረዉ መጣር አለባቸዉ።በGI ትንታኔ መሰረት የአፍሪቃ መንግሥታትና ተቋሙ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እያለ የሚሸፋፍነዉ ምዕራቡ ዓለም አምስት ጉዳዮችን በጋራ መሥራት ከቻሉ ሩሲያ አፍሪቃ ላይ ያላትን ተፅዕኖ ማዳከም አይደገድም።
GI የዘረዘራቸዉ አምስት ነጥቦች የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች የሰፈሩባቸዉን ሐገራት ከማራቅ ይልቅ መተባብር ቀዳሚዉ ነዉ።በሩሲያ ተባባሪዎች ላይ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ማድረግ-ሁለት፣ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮችን በማዕቀብ መቅጣት-ሶስት፣ ሩሲያ የምታሰራጨዉን የተዛባ መረጃ ለማክሸፍ ተጨማሪ ርምጃዎች መዉሰድ-አራት እና ሕገ-ወጥ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማገድ ለሚደረገዉ ጥረት ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ-አምስት
የሳሕል ሽርክና ፣ ማዕቀብ ወይስ ትብብር?
የፖለቲካ ቀዉስ፣ የአማፂያን ጥቃት፣የሩሲያ ተፅዕኖም ጠንከር ብሎ የሚታይበት ምዕራብ አፍሪቃ ነዉ።የሳሕል አካባቢ ሐገራት የሚባሉት የማሊ፣የቡርኪና ፋሶና የኒዤር የጦር መኮንኖች በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣን በመያዛቸዉ የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ (ECOWAS) ከአባልነት አግዷቸዋል።
ሶስቱ ሐገራትም ECOWASን ትተዉ የሳሕል መንግሥታት ትብብር (በፈረንሰይኛ ምሕፃሩ AES) ያሉትን ማሕበር መሥርተዋል።ማሕበሩ ከኤኮኖሚ ይልቅ የአማፂያንን ጥቃት በጋራ ለመመከት ያለመ የፀጥታና የወታደራዊ ትብብር ነዉ።የGI ተንታኝ ጁሊያ ስታንያርድ እንደሚሉት በተለይ ፀጥታን በማስከበሩ ረገድ ከሶስቱ ሐገራት ጋር ከመራራቅ ይልቅ ድልድይ መገንባቱ ጠቃሚ ነዉ።
«የአማፂያኑ እንቅስቃሴ በየሐገራቱ ዘመናዊ ድንበር የተገደበደ አይደለም።ሥለዚሕ ከECOWAS የወጡት ሐገራት በፖለቲካዉ መስክ ማራቁ ሌላ ችግር ነዉ።በዘገባችን ይሕንን ጠቁመናል።የሆነ ዓይነት የትብብር መስክ መቀጠል አለበት። በተለይ ድንበር በማይገድበዉ በፀጥታ ጉዳይ ትብብሩ አስፈላጊ ነዉ።»
CSIS በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የዩናይትድ ስቴትስ የሥልታዊ ጥናት ማዕከል ባልደረባ ቤቬርልይ ኦቺያንግም ተመሳሳይ ሐሳብ አላቸዉ።ECOWAS በተለይ ፀጥታን ለማስከበር ከሶስቱ ሐገራት ጋር ለመተባበር ሙከራዎች ማድረጉን ኦቺያንግ ይጠቅሳሉ።
«አጠራጣሪ ቢሆኑም፣ ለምሳሌ ሥለሩሲያ ወታደራዊ ተሳትፎ፣ ፀረ ዴሞክራቲሲ አስተዳደሮች ቢሆኑም አብሮ መስራት የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ አለበት።የፀረ-ሽምቅ ኃይል ለመመሥረት ECOWAS በሚያደርገዉ ጥረት የሳሕል ወታደራዊ መንግሥታት የመከላከያ አዛዦች በዉይይቱ እንዲካፈሉ ለማድረግ እየሞከረ ነዉ።የሳሕል መንግስታት ሐሳቡን ዉድቅ ያደርጉታል።ግን በረጅም ጊዜ አማፂያኑን እያንዳዱ ሐገር መቋቋም እንዳለባቸዉ መረዳታቸዉ አይርም።»
የሩሲያ የሎጂስቲክ ተባባሪዎች
ሩሲያ፣ አፍሪቃ ዉስጥ ያላት ወታደራዊ ሥምሪት በቅርብ አመታት ዉስጥ ብዙ ተለዉጧል።ቀደም ሲል ወታደሮች የሚያዘምተዉ ቫግነር የተባለዉ የቅጥረኛ ወታደሮች ኩባንያ ነበር።የኩባንያዉ ባለቤት የቭጌኒይ ፕሪጎዢን የዛሬ ሁለት ዓመት በአዉሮፕላን አደጋ ከተሞቱ በኋላ ግን የቫግነር ኩባንያ አብዛኛዉ ክፍል የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር ጠቅልሎታል።
ሩሲያ አፍሪቃ ዉስጥ ለምታዘምትና ለምታስፍረዉ ኃይል በመነሻና ማረፊያነት የሚያገለግለዉ ሶሪያ የሚገኘዉ የሩሲያ የጦር ሠፈር ነዉ።ሶሪያ ዉስጥ የመንግሥት ለዉጥ በመደረጉ የሩሲያ የጦር ሠፈር መዘጋቱ አይቀርም ብለዉ የሚያምኑ ተንታኞች አሉ።
እነዚሕ ተንታኖች እንደገመቱት ወይም እንደሚመኙት ሶሪያ የሚገኘዉ የሩሲያ ጦር ሠፈር ከተዘጋ የሩሲያ ተቀናቃኞች በሩሲያ ተባባሪዎች ላይ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት የሚያደርጉበት ጊዜ አሁን ነዉ።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የገጠመችዉ ጦርነት ዉጤትም አፍሪቃ ዉስጥ ያላትን ተፅዕኖ ከሚበይኑ ጉዳዩች አንዱ ነዉ።አሁን የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት እንደጀመሩት ጦርነቱ በሰላማዊ ድርድር ካበቃ ግን ሩሲያና ተቀናቃኞችዋ አፍሪቃን ለመቀመራት የገጠሙት ሽኩቻ መልክና ባሕሪ መቀየሩ አይቀርም።
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ