ታላቁ የህዳሴ ግድብ አገልግሎት መጀመርና ቀጣዩ ዲፕሎማሲ
ሰኞ፣ የካቲት 14 2014ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች የምትገኘው የኃይል ማመንጫ ግድብ በትናንትናው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በርካታ የአገሪቱ ባለስልጣናት በተገኙበት የመጀመሪያ ዙር የኃይል ማመንጨት ሥራ ተበስሯል፡፡ ይሁንና የግድቡ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠበት 2003 ዓ.ም. ጀምሮ በስድስት ዓመት ውስጥ በ80 ቢሊየን ብር እንደሚጠናቀቅ ቢገመትም፤ ከ10 ዓመታት በላይ ጊዜ ወስዶ በ84 በመቶ ገደማ የግንባታ ደረጃ እንኳ እጥፍ የግንባታ ወጪ አስፈልጎታል፡፡
ለዚህም ዋናው ምክኒያት የፕሮጀክቱ መጓተት እና የውጪ ምንዛሪ ግሽበት ያመጣው ጫና መሆኑን የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስከያጅ በተለይም ለዶይቼ ቬለ አብራርተዋል፡፡ አንድ የውሃ ዘርፍ ጥናት ወይም ሃይድሮ ፖለቲካ ተንተኝ እንደሚሉትም የግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመር፤ ሲስተዋል ለነበረው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረቶች መለሳለስ ዋስትና አይሆንም፡፡
ግድቡ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ባለው በአንዱ ተርባይን አሳክቷል የተባለው የኃይል ማመንጨት ስራ በትናንትናው እለት ይፋ ሆኗል፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹትም ግድቡ ያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በሁለት መስመሮች አገልግሎት ላይ ወደ መዋል ተሸጋግረዋል፡፡
እንደ የግድቡ ስራ አስፈጻሚ ማብራሪያ የግድቡ የግንባታ ጊዜ መጓተት ዘርፈ ብዙ ዋጋን ያስከፈለ ሆኗል፡፡ አሁን ላይ የግንባታ ሂደቱ 84 በመቶ መሻገሩ የሚነገርለት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስካሁን 163 ቢሊየን ብር ገደማ ወጪ አስወጥቷል፡፡ በቀጣይ ሶስት ዓመታት አጠቃላይ 202 ቢሊየን ማለትም በተጨማሪነት 16 በመቶውን ግንባታ ለማጠናቀቅ 40 ቢሊየን ብር ገደማ እንደሚያስፈልግና በቀጣይነት ግን በሂደት ሌሎች ተርባይኖችን ወደ ስራ የማስገባቱ ስራ እንደሚቀጥልም ስራ አስከያጁ አብራርተውልናል፡፡
በብዙ መልኩ ከታችኛው የተፋሰስ አገራት ጋር ኢትዮጵያን ሲያወዛግብ የቆየው የግድቡ ግንባታ አሁን ላይ አገልግሎት ወደ መስጠት መሸጋገሩ የዲፕሎማሲውን ሙግት ያቃልል ወይስ ይበልጥ ያባብስ ይሆን ሲል የውሃ ሃብት አስተዳደር የግል አማካሪ የሆኑትን ፈቅ አህመድ ነጋሽን ጠይቀናቸዋል፡፡
ከአስር ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የግድቡ ግንባታ ላይ ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር የሚደረገው ድርድር ምናልባት በቀጣይ መቋጫስ ያገኝ ይሆን። ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ መጠን ያለው ውሃ እንደሚይዝ የሚጠበቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስካሁን በሁለት ዙር የውሃ መያዝ ሂደቶች 17.5 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃን መያዝ ችሏል።
ስዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ