ክፍተቱ የሰፋው የውጭ ምንዛሪ ተመን እና የትይዩ ገበያው
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 17 2017ተፈላጊውን ግብ ያልመታው የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሰሞኑ 150 ሚሊየን ዶላር ግድም ለንግድ ባንኮች በውጪ ምንዛሪ ክምችት ብያከፋፍልም የንግድ ባንኮች እና ገለልተኛ የውጪ ምንዛሪ ቢሮዎች የውጪ ምንዛሪ መጠን በ10 በመቶ ስለመስፋቱ እየተነገረ ነው፡፡
ባሁን ወቅት በኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች አንድ የአሜሪካ ዶላር በ140 ብር ገደማ ሲመነዘር በውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች (forex bureaus) እና ትይዩ ገበያዎች እስከ 160 ብር እየተመነዘረ እንደሆነm ተገልጿል።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ከአንድ ዓመት በፊት በወሰደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጪ ምንዛሪ በነጻ ገበያ እንዲመራ ሲወስን የባንኮች የውጭ ምንዛሪ መጠን ከትይዩ ገበያው ጋር የሚኖረው ልዩነት በእጅጉ እንዲጠብ ግብ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም ቢያንስ በዚህ አንድ ዓመት ተፈላጊውን ግብ መምታት አለመቻሉን ባለሞያዎች ያነሳሉ፡፡
ለምን ይሆን?
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁናዊ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ በተለይም ደግሞ የብር እና ዶላር ምንዛሪ ከባንክ ባንክ መጠነኛ ልዩነት ቢኖረውም ከ141.7 እስከ 142.3 ግገደማ እየተመነዘረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከገለልተኛ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እና ከትይዩ ገበያው የዶላር-ብር የዋጋ ንጽጽር አኳያ 10 በመቶ እና ምናልባትም ከዚያም የላቀ ልዩነት እንዳለው ነው የሚነገረው፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር አጥላው ዓለሙ ይህ ከአንድ ዓመት በፊት አገሪቱ ባከናወነችው የኢከኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ በነጻ ገበያ እንዲመራ የወጠነችው ውጥን ተፈላጊውን ግብ ላለመምታቱ ማሳያ ነው ብለውታል፡፡
“የሪፎርሙ አንደኛው ግብ የነበረው የባንኮች እና ትይዩ ገቢያው የውጭ ምንዛሪ መጠን እንዲቀራረብ ቢሆንም፤ እየተቀራረበ አሁን ላይ ልዩነቱ እየሰፋ መጥቷል ከዚህ አኳያ ግቡን አልመታም” የሚሉት ባለሙያው፤ የሪፎርፉ ሌላኛው ግብ የሆነው የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ እንዲገኝ የማድረግ ዓላማ የነበረው ቢሆንም አሁንም እጥረት በመኖሩ የውጪ ምንዛሪው “ከራሽኒንግ” አልወጣም በማለት ወደ ውጪ በስፋት የሚላክ ምርት በሌለበት በቂና ተፈላጊውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ቀላል አልሆነምም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከህጋዊ የውጭ ምንዛሪ ውጭ ያሉትን የሂሳብ ቁጥሮች እንደሚያግድ አሳውቋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገዢው ማሞ ምህረቱ የንግድ ባንኮች ለውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች በተለይም ለነጋዴዎች የሚሰጡበት አሰራር ቀላል እና ምቹ እንዲሆን ስራዎች መሰራታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶ/ር አጥላው ግን የባንኮች እናትይዩ ገበያው የምንዛሪ መጠን እየሰፋ እንጂ ረዘም ላለ ጊዜ ጠቦ ሲቆይ እየታዬ አይደለም በማለት ለዚህም መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡ “ይህ ልዩነት እየሰፋ የመጣው ለውጪ ገበያ የሚላክ ስለሌለን ነው፡፡ ከዚያ በተቃራኒ አብዛኛውን ሸቀጦች ከውጭ ገበያ የምናስገባ ነው” በማለት ክፍተቱ ላይ መስራቱ ብቻ ለውጥ ማምጣት እንደምችል ጠቁመዋል፡፡
አገሪቷ ወደ ውጪ የምትልከው ዝቅ ብሎ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው ከፍ ሲል የግድ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስለምፈጠር ሰዎች ወደ ትይዩ ገበያ መሄድን አማራጭ ማድረጋቸው የማይቀር ነው ያሉት ዶ/ር አጥላው፤ ባንኮች ተፈለገው የውጭ ምንዛሪ በሚፈለግ መጠን እንዲሰጡ ምርቱና የተመረተውን ወደ ውጭ ገበያ መላኩመበረታታት አለበት ሲሉ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ባለሙያው አክለውም የተመረቱትን ምርቶች እንኳ (በተለይም የየቅባት እህሎችን) ባለው የሰላም እጦት ሁኔታ ወደ ገቢያው በገፍ ማቅረብ ቀላል እንዳልሆነም በመግለጽ፤ በነዚህም ላይ ስራዎችን መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አክለውም ብሔራዊ ባንክ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በትይዩ (ጥቁር) ገበያ ላይ መረር ያለ እርምጃ እንደሚወስድ በማሳወቅ ከትይዩ ገበያው ጋር ከውጪ በገንዘብ አስተላላፊነት የሚሰሩ ተቋማትን እስከማገድ መድረሱን አስታውሰው፤ መሰል እርምጃዎችም ቢሆኑ በህጋዊውና በትይዩ ገበያ መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መጠን ለማጥበብ እንደ ዘላቂ እርምጃ መታየታቸውን በጥርጣሪ ነው ያነሱት፡፡ ጥቁር ገቢያው በየትኛውም መንግስታዊ ታሪክ ተፈቅዶ ወይም እንዲኖር ተፈልጎ አያውቅም ያሉት ባለሙያው፤ ነገር ግን ጠፍቶ እንደማያውቅ አንስተው ነገሩ በኢኮኖሚ ስልት እንጂ በማሳደድ ዘላቂ እልባት እንደማያመጣ አስገንዝበዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ