ብዙዎችን ያስጨነቀው የሙቀት ማዕበል
ቅዳሜ፣ ሰኔ 28 2017
በእርግጥም ሙቀቱ ያሰቃያል፤ በሰሞኑ ኃይለኛ ሙቀት ውስጥ ነፋን አቅም አጥቷል፤ ሰው ሠራሹ አየር ማቀዝቀዣ ከድምጹ ባሻገር ጆሮ ላይ እየጮኸ ያውካል። ውኃውን ቢጠጡት ሆድ ይወጥር ካልሆነ እምብዛም ጥም አይቆርጥም። እውነትም ተፈጥሮ ከፍቷታል።
ከመጠን ያለፈው ሙቀት በአውሮጳ ሃገራት ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ አስገድዷል። በተለይ ስፔን እና ፖርቱጋል እጅግ ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል እተጋፈጡ ነው። በአብዛኛው በደቡባዊ አውሮጳ ሃገራት ከ40 ዲግሪ በላይ የደረሰው ኃይለኛ ሙቀት ሰደድስ እሳትም አስከትሏል። በጣሊያን፤ ስፔን እና ግሪክን በመሳሰሉት ሃገራት ባለሥልጣናት ተጨማሪ የሰደድ እሳት ማስጠንቀቂያ ለሕዝባቸው አስተላልፈዋል። በተለይ ከፍተኛ የሙቀት መጠን በተመዘገባቸው በጣሊያን፣ ግሪክ፣ ስፔን እና ፖርቱጋል የሀገሬው ነዋሪዎች እና ቱሪስቶች መጠለያ ለመፈለግ ተገደዋል።
ሁለት ሦስተኛው የፖርቱጋል አካባቢ ከ42 ዲግሪ በላይ በደረሰውሙቀት ምክንያት ሰደድ እሳት ሊነሳ ይችላል የሚል ማስጠንቀቂያና ከፍተኛ ዝግጅት ላይ ነበር። በጣሊያን አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በኃይለኛው ሙቀት ምክንያት ባለሥልጣናት ኅብረተሰቡ ከቤት ውጪ የሚያደርጋቸውን የመዝናኛ እንቅስቃሴዎች እንዲገድብ ለማስገንዘብ ተገደዋል። ጣሊያን የግንባታ ሥራተኞች በሙቀቱ ምክንያት ሥራቸውን እንዲያቆሙ ትዕዛዝ ሰጥታለች። የሀገሪቱ ባለሥልጣናት በኃይለኛው ሙቀት ለሚፈጠር ማንኛውም የጤና ችግር የመጀመሪያ እርዳታ አገልግሎትን ከማዘጋጀት አልፈው ሰዎች በየቦታው የሚጠጡት እንዲያገኙ አመቻችተዋል።
ስዊዘርላንድ ደግሞ የኒኩሊየር ኃይል ማመንጫም እንዲሁ በኃይለኛው ሙቀት ሳቢያ በከፊል ተዘግቷል። ኦስትሪያ ውስጥ ደግሞ ሙቀቱ ድርቅና ሰደድ እሳት አስከትሏል። ኃይለኛውን ሙቀት ተከትሎ ምዕራብ ጀርመን ውስጥ የወረደው ከባድ ወጀብና ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ትላልቅ ዛፎችን ሳይቀር እየገነደሰ ጉዳት አስከትሏል።
ሳይንስቲስቶች እንዲህ እየተዳጋገመ ተጠናክሮ በመከሰት ላይ ያለውን የሙቀት ማዕበል ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ያያይዙታል። እንደውም እንዲህ ያለው ጽንፍ የወጣ የአየር ሁኔታ በደቡባዊ የአውሮጳ ሃገራት ተደጋግሞ ሊከሰት እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።
አፍሪቃዊቱ ሞሮኮን ጨምሮ፤ ጀርመን፤ ኔዘርላንድ፤ ስዊዘርላንድ፤ ቼክ ሪፑብሊክ፤ ቱርክ፤ እና ሌሎችም የአውሮጳ ሃገራትን በዚህ ወቅት በሙቀት ማዕበል ያጥለቀለቀው ለረዥም ወራት ከባቢ አየሩ ውስጥ የተጠራቀመው የሙቀት ጉልላት ነው ይላሉ የሮያል ሜትሪዎሎጂ ማኅበረሰብ ዋና ኃላፊ ሊዝ ቤንትሊ።
«የተለየ ደረቅ ነበር፤ የፀደይ ወራታችን በጣም ደረቅ ነበር። ስለዚህ መሬቱ ደረቅ ነው፤ ይህ ማለት ፀሐይ ስትወጣ ከመሬቱ እርጥበትን ለማትነን ያን ያህል ኃይል አይፈልም ማለት ነው። ኃይሉ ሁሉ መሬቱን ለማሞቅ ይውላል። እናም ሞቃት ፀሐይ ነበር፤ ያ ደግሞ የአየር ሁኔታው ከፍ እንዲል ያደርገዋል። ያ የሙቀት ጉልላት አለ፣ ስለዚህ ከደቡብ ተጨማሪ ሙቀት እንስባለን። በዚያ ላይ ከዩናይትድ ኪንግደም እና በተለይም በሜዲትራኒያን የባሕር ሙቀት ሞገድ አለን።»
የዓለም የሙቀት መጠን እየጨመረ እና የሙቀት ማዕበሉ እየተባባሰ በሄደበት በዚህ ወቅት ቀዝቀዝ ባለ የአየር ሁኔታ ውስጥ መቆየት በጣም አስፈላጊ መሆኑ ሰሞኑን ደጋግሞ እየተነገረ ነው። የሙቀት መጠኑ መጨመር የማቀዝቀዣ ስልት ፍላጎትን ከፍ እያደረገው በመሄድ ላይ ነው። የአየርም ሆነ የምግብ ማቀዝቀዣ መሣሪያዎች ደግሞ ከሚወስዱት ኃይል ጎን ለጎን ከባቢ አየርን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚበክሉና ለአጠቃላይ የዓለም ብክለት ዓይነተኛ አስተቃጽኦ ያደርጋሉ በሚል ትችት እየቀረበ ነው። በዚህ ሆነ በዚያ ግን የሙቀቱ ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠበቃል።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ