ቤላሩስያ፤ በፕሬዚዳንቱ ላይ የተነሳዉ ተቃዉሞ እንደቀጠለ ነዉ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 12 2012የቤላሩስያ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቀዉ ከፍተኛ ተቃዉሞ ዛሬም ለአስረኛ ቀን እንደቀጠለ ነዉ። ከአስር ቀን በፊት በቤላሩስ በተካሄደዉ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሉካሼንኮ መንግሥት ስልጣን ላለመልቀቅ ከፍተኛ የድምፅ ማጭበርበር ፈፅሞአል ሲል በሃገሪቱ ታዋቂዉና ከፍተኛ ደጋፊ ያለዉ ተፎካካሪዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ይከሳል። ትናንት ምሽት መዲና ሚኒስክ ላይ ወደ 5000 ሺህ የሚሆን ሕዝብ ባካሄደዉ የተቃዉሞ ሰልፍ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን እንዲፈታ ጠይቀዋል። ትናንት እለቱን በሃገሩቱ በሚገኙ የተለያዩ ተቋሟት እና ኩባንያዎች ዉስጥ ፕሬዚዳንት ሉካሼንኮን በመቃወም ሰልፍ ወጥተዋል። ፕሬዚዳንት ሉካሸንኮ ትናንት ሚኒስክ ዉስጥ የሚገኝ አንድ የመንግሥት ፋብሪካን በጎበኙበት ወቅት ከፋብሪካዉ ሰራተኞች በኩል ከፍተኛ የተቃዉሞ ጩኸት ደርሶባቸዉ ነበር። በሳምንቱ መጨረሻ ሉካሼንኮ መዲና ሚኒስክ ላይ ደጋፊዎቻቸዉ የድጋፍ ሰልፍ እንዲያደርጉ ጠርተዉ በሰልፉ ላይ ተገኝተዉ ባደረጉት ንግግር በሃገሪቱ ተሃድሶ እንዳደርግ ተጠይቄያለሁ ከነገ ጀምሮ ተሃድሶ እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዉ ነበር። በዚሁ እለት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት- ኔቶ በቤላሩስ ምዕራባዊ ድንበር አካባቢ የጦር ሰፈር እየገነባ ነዉ ሲሉ ስጋታቸዉን ገልፀዉ ነበር። የቤሉሩስያ የፕሬዚደንትነት ስልጣኑን ላለፉት 26 ዓመታት የተቆናጠጡት ሉካሼንኮ ሰሞኑን በሃገሪቱ የተካሄደዉን ምርጫ ማሸነፋቸዉ ሲነገር ቻይና እና ሩስያ የእንኳን ደስ ያሉት ዉደሳን ሲያስተላልፉ ፤ ፖላንድ ዩክሬይን ላቲቪያና ሉትዌንያ ፤ ምርጫዉ በመጭበርበሩ ቤላሩስያ አዲስ ምርጫን እንድታካሂድ ጥሪ አቅርበዋል። ዛሬ ደሞ እኔ እስካልገደላችሁኝ ድረስ በቁሜ እያለሁ ዳግመኛ ምርጫ አይካሄድም ሲሉ የቤላሩስያዉ ፕሬዚደንት አስረግጠዉ ተናግረዋል።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ