በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት የጠየቀዉ ህወሓት
ሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2017ህወሓት በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተሰጠው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እና እግድ ሊያበቃ ጥቂት ቀናት በቀሩበት፥ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት እንዲመለስለት ጠየቀ። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ህወሓት ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለሶስት ወር ማገዱ፣ በሶስት ወር ማስተካከያ የማያደርግ ከሆነ በቀጥታ እንደሚሰረዝ አስታውቆ ነበረ። ከዚህ በተጨማሪ የህወሓት 1337 መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች ካደረጉት ስብሰባ በኃላ በሳምንቱ መጨረሻ ባወጡት የአቋም መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶርያ ውል ሙሉበሙሉ ለመፈፀም ቁርጠኛ አይደለም ብለዋል። አደራዳሪ አካላትም ቢሆን 'ትጥቅ ፍቱ' ከማለት ውጭ ስምምነቱ በሙሉእነት እንዲፈፀም የሚያሳዩት ፍላጎት ውሱን ነው ሲል ህወሓት ወቅሷል።
1337 የሚሆኑ በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ህወሓት መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች ለቀናት ካደረጉት ውይይት በኃላ በሳምንቱ መጨረሻ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቋም ያንፀባረቁበት መግለጫ በማውጣት ስብሰባቸው አጠናቀዋል። ከፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት መመለስ ጋር በተገናኘ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውዝግብ ውስጥ ያለው በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት፥ ፓርቲው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ ፓርቲ ምዝገባ የማካሄድ ፍላጎት እንደሌለው በድጋሚ አስታውቋል።«የትግራይ ጊዚያዊ መንግስት አካታች አደለም» ተቃዋሚዎች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሀይል መሠረት ባደረገ "የአመፅ ተግባር ላይ መሳተፍ" የሚል ምክንያት በመጥቀስ በ2013 ዓመተምህረት ህወሓትን ከፓርቲነት ሰርዞ የነበረ ሲሆን፥ ከሰላም ስምምነቱ በኃላ ቦርድ ባለፈው ነሓሴ 3 ቀን 2016 ዓመተምህረት ህወሓት የክልል ፓርቲ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ በልዩ ሁኔታ የምዝገባ እና የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ሰጥቶት እንደነበረ ይታወሳል። ይሁንና የተሰጠው ፍቃድ ተከትሎ ሊፈፅማቸው የሚገቡ ተግባራት ባለመከወኑ ህወሓት ለሦስት ወራት ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እግድ ማስተላለፉ፥ ማስተካከያዎች ካልተደረጉ ደግሞ ፓርቲው ከሦስት ወራት በኃላ በቀጥታ እንደሚሰረዝ ባለፈው የካቲት 6 ቀን 2017 ዓመተምህረት ማስታወቁ ይታወሳል። ይህ ቀነ ገደብ በመጪው ሳምንት ግንቦት 5 ቀን 2017 ዓመተምህረት የሚጠናቀቅ ሲሆን የምርጫ ቦርድ የእስካሁን ሂደት የተቃወሙት በሳምንቱ መጨረሻ ስብሰባ ላይ የሰነበቱ የህወሓት ከፍተኛ እና መካከል አመራሮች የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት እንዲመለስ ጠይቀዋል።በትግራይ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ
የህወሓት መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች "የፓርቲያችን ህወሓት እውቅና በሚመለከት በትግራይ ህዝብ ልብ ታትሞ ያደረና በትግራይ ህዝብ የሚወሰን መሆኑ እናምናለን። ይሁንና ባጋጠመን ወረራ ምክንያት የፓርቲያችን ሕጋዊ እውቅና በኢትዮጵያ መንግስት ተሰርዞ ቆይቶ፥ በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት ወደነበረበት ሊመለስ ተወስኖ መጨረሻ ያገኘ ጉዳይ መሆኑ የታወቀ፣ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የፕሪቶርያ ስምምነት በሚፃረር መልኩ ወደ ተራ ቴክኒካዊ ጉዳይ ወርዶ ፓርቲያችን እንደአዲስ እንዲመዘገብ፣ ባካሄደው ህዝባዊ ትግል ምክንያት እንደ አማፂ እንዲታይ ተደጋጋሚ ጫና ለማድረግ መሞከሩ እየተቃወምን፣ አሁንም በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት የፓርቲያችን ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመለስ ጥሪ እናቀርባለ" ሲሉ በአቋም መግለጫቸው አመልክተዋል።እንወያይ፤ ማኅበረሰቡን ያስጨነቀዉ የትግራይ ፖለቲከኞች ሽኩቻ
ከዚህ በተጨማሪ የህወሓት መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች በርካታ ጉዳዮች በዳሰሱበት የአቋም መግለጫው፥ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በሙሉእነት እየተተረገበ አይደለም ያሉ ሲሆን የውሉ ፈራሚ የሆነው የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ለስምምነቱ ትግበራ ቁርጠኛ አልሆነም ሲሉም ወቅሰዋል።
የህወሓት ካድሬዎች በአቋም መግለጫቸው "ውስጣችን ተፈጥሮ በቆየ ብሔራዊ ክህደት ምክንያት፣ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ለስምምነቱ አፈፃፀም ቁርጠኛ ባለመሆኑ ምክንያት፣ አደራዳሪ አካላትም ቢሆን ትጥቅ ፍቱ ከማለት ውጭ ስምምነቱ በሙሉእነት እንዲፈፀም የሚያሳዩት ፍላጎት ውሱን ነው። እነዚህ ችግሮች ተደራርበው ስምምነቱ እስካሁን በሙሉእነት አልተተገበረም" ብለዋል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ባወጣው አዋጅ በክልሉ የተቋቋመው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ ህወሓት ክንፍ አባላት፣ ሲቪክ ተቋማት እና ሌሎች የተካተቱበት የትግራይ ግዚያዊ ምክርቤት የተቃወሙት እነዚህ ከአንድ ሺህ ሶስት መቶ በላይ የሚቆጠሩ የህወሓት መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች፣ የህዝብን ሕገ መንግስታዊ ስልጣን የሚጥስ እንዲሁም በህዝባችን ላይ የተጫነ ነው ሲሉ ኮንነውታል። ከዚህ በተጨማሪ ለምርጫ ዝግጅቶች እንዲደረጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት