"በግጭት ዐውድ የተባባሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ" ኢሰመኮ
ሰኞ፣ ሐምሌ 28 2017"በግጭት ዐውድ የተባባሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ" ኢሰመኮ
የመንግሥት ኃይሎች ከፋኖ እና ኦነግ ሸኔ ጋር በሚያካሂዱት የትጥቅ ግጭት በሚፈፀሙ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ በዜጎች ላይ "ግድያ እና የአካል ጉዳት" መፈፀማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አታወቀ። ኮሚሽኑ ከሰኔ 2016 እስካ ሰኔ 2017 ዓ.ም ያለውን ሀገራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኹኔታ ሪፖርት ዛሬ ሰኞ ይፋ ሲያደርግ በኦነግ ሸኔ የሚፈፀም እገታ መቀጠሉን ገልጿል።
ኮሚሽኑ "መረጃ የማግኘት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመንቀሳቀስ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ እና አቤቱታ የማቅረብ፣ ፍትሕ የማግኘት እና የዳኝነት ነጻነት" አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ጠቅሷል።
ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ ቀዉስ ማብቂያ ያገኝ ይሆን?
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ የተቋሙን ዓመታዊ የመብቶች ኹኔታ ሲገልፁ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች "የግጭት አካል ያልነበሩ ሰላማዊ ሰዎች" ሞትን ጨምሮ ለከፋ የአካል ጉዳት ተጋልጠዋል።
"የመንግሥት ኃይሎች በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች በተለምዶ ፋኖ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተለምዶ ኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጋር በሚያካሂዱት የትጥቅ ግጭት ዐውድ ውስጥ በሚፀሙ ጥቃቶች ሰዎች ተገድለዋል፤ እንዲሁም የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።" ኃላፊው እንዳሉት በሀገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተባብሶ ቀጥሏል።
"በግጭት ዐውድ የተባባሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ኹኔታዎች አሉ።"
ኦነግ ሸኔ ተሽከርካሪ በማስቆም የሚፈጽመው "ዕገታ ቀጥሏል" ያለው ኮሚሽኑ "ከፍተኛ የማስለቀቂያ ገንዘብ ይጠይቃል፣ መክፈል ባልቻሉት ላይም ግድያን ጨምሮ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ፈጽሟል" ብሏል። በሌላ በኩል በአማራ ክልል የአስቸኴይ ጊዜ አዋጅ ባይኖርም የጅምላ እሥር እንደነበርም ተገልጿል። "የአስቸኳይ ኹኔታ ያለ በሚመስል መልኩ የጅምላ እና የተራዘመ እሥር ተፈጽሟል። በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ካለው የትጥቅ ግጭት ጋር ተያይዞ ወቅታዊ ጉዳይ በሚል በሕገ ወጥ መንገድ ተይዘው በየ ፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙ ሰዎች ያሉ ሲሆን፣ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎች በፖሊስ ጣቢያዎች ታስረዋል።"
አማራ ክልል ውስጥ ባለው ጦርነት በመንግሥት በተተኮሰ የድሮን ጥቃት ሰዎች ስለመገደላቸው መረጃዎች እንዳሉ ተጠቅሶ ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ ይህንን ብለዋል። "ከመከላከያ ጋር ባደረግነው ውይይት ይህ ያልተረጋገጥ ክስ አለ ብለን አንስተናል። መቶ ምናምን ሰው [በድሮን ተገድለዋል] የተባለው ለእኛ የደረሰን ነገ የለም።" ኮሚሽኑ በየሦስት ወራት የሚያወጣውን መግለጫ ለምን እንዳቆመ የተጠየቁት አቶ ብርሃኑ "በማጯጯህ መፍትሔ አይገኝም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የተቃዋሚዎች ወቅታዊ ውይይቶች ለኢትዮጵያ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ያመላክቱ ይሆን?
"መግለጫው ሰው ከእሥር ቤት የማያስፈታ ከሆነ፣ አስገድዶ መሰወርን የማያስቀር ከሆነ፣ እኛ ብንጮህ ሌላው ተጠያቂነት የማያረጋግጥ ከሆነ እና ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ውጤት አናመጣም።"
ኢሰመኮ "መረጃ የማግኘት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመንቀሳቀስ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ እና አቤቱታ የማቅረብ፣ ፍትሕ የማግኘት እና የዳኝነት ነጻነት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ" ብሏል። ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት 3700 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል ብሏል። በሌላ በኩል የሴቶች እና ሕፃናት የመብት ኹኔታ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን፣ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የተሟላ የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ እንዳልሆነ እና ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊትም አሁንም መቀጠሉ ተመላክቷል። የፖለቲከኛ በቴ ኡርጌሳ ግድያን የምርመራ ሂደት የተጠየቁት ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ "በወቅቱ የነበሩ [የተቋሙ] የሥራ ኃላፊዎች በቂ መልስ ሊሰጡበት የሚችሏቸው ናቸው" በማለት ሪፖርቱ እንደሌላቸው ገልፀው አጣርተው "ምርመራው የደረሰበትን ደረጃ ላሳውቅ እችላለሁ" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ