በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች የተደረገ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ
ዓርብ፣ ጥር 16 2017ከመስከረም አግማሽ እስከ ታኅሣሥ አጋማሽ 2017 ዓ.ም በነበሩት 3 ወራት ውስጥ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልልሎች በመንግሥት እና በታጣቂ ኃይሎች ከ167 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ። ብሔራዊው የመብት ድርጅት ይፋ ያደረገው የምርመራ ውጤት "በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በሙሉ የሚሸፍን አይደለም" ያለ ሲሆን የሟቾች ቁጥርም ከዚህ ሊልቅ እንደሚችልም ጠቁሟል።“በኦሮሚያ ክልል ከሕግ ውጪ ስለተያዙት ሰዎች መልስ አላገኘሁም” ኢሰመኮ
ኮሚሽኑ "ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ከኦነግ ሸኔ ትተባበራላችሁ" የሚሉ ምክንያቶች የመንግሥት የጸጥታ አካላት ለሚወስዷቸው እርምጃዎች ምክንያት ተብለው መጠቀሳቸውን እና "መንግሥትን ትደግፋላችሁ፣ መረጃም ትሰጣላችሁ" የሚለው ደግሞ ታጣቂዎች ለሚፈጽሙት ግድያ በምክንያትነት መቅረቡን በግኝቱ አመልክቷል።
የኮሚሽኑ ዝርዝር የምርመራ ውጤት ምን ያሳያል?
"በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ሥጋቶች እና አሳሳቢ ሁኔታዎች መኖራቸውን" ያስታወሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የዚህኛው የምርመራ ውጤት በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በሙሉ የሚሸፍን አለመሆኑን ይፋ አድርጓል። "ከፍርድ ውጭ የሚፈጸም ግድያ፣ በግጭት ዐውድና አካባቢ የሚደርስ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ፣ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብትና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ፣ የሀገር ውስጥ መፈናቀል እና የዳኝነት ነጻነት መሸርሸር አሳሳቢ ሆነው የቀጠሉ የመብት ጥሰቶች መሆናቸውንም ገልጿል።
በጎዳና ላይ ውለው የሚያድሩ ሰዎችን ወደ ማቆያ ቦታ የመውሰድ ድርጊት ቀጥላል - ኢሰመኮ
ብሔራዊው የመብቶች ተቋም ከመስከረም አጋማሽ እስከ ታኅሣሥ አጋማሽ በክልል፣ በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ፣ የተፈፀሙ ጥሰቶችን አፈጻጸም ጭምር ዘርዝሮ ያስቀመጠ ሲሆን በድምሩ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት እና የፋኖ እና የኦነግ ሸኔ ኃይሎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች ከ167 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ራኬብ መሰለ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ ይህ ምርመራ ከዚህ በፊት የሚደረጉ ምርምራዎች ቀጣይ ሲሆን "አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ብለን የለየናቸውን" የተመለከተ ነው ብለዋል።በአማራ ክልል የመንግሥት የጸጥታ ኃይላት በሚወስዷቸው እርምጃዎች ሕፃናትን ጨምሮ ድርስ ነፍሰ ጡር ሴቶች፣ አረጋዊያን መገደላቸው ተገልጿል። የሞተን ሰው ለምን ትቀብራላችሁ፣ የተገደለን የፋኖ አባል ፎቶን ለምን ያዛችሁ በሚል ሰበብ ጭምር የተገደሉ መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን፣ አውድማ ላይ የተኙ ንጽፁሃን ዜጎች ጭምር በመንግሥት የፀጥታ አካላት ስለመገደላቸው በምርመራ ግኝቱ ተጠቅሷል።
ኢሰመኮ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተጸፈሙ ወታደራዊ ዒላማን ያልለዩ የድሮን ጥቃትን ጨምሮ የጦር መሣሪያ እርምጃዎች ግድያዎች የተፈጸሙ ሲሆን "ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ የፋኖ ቤተሰብ ናችሁ፣ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ግንኙነት አላችሁ፣ ስንቅና መረጃም ታቀብላላችሁ" የሚሉ ምክንያቶችን በመስጠት ግድያ መፈፀማቸው ተጠቅሷል። በሁለቱ ክልሎች የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች ደግሞ "መንግሥትን ትደግፋላችሁ" በሚል ሰዎችን እንደሚገድሉ በምርመራው ተመላክቷል።
«ከሕግ አሰራር ውጪ ለወታደራዊ ምልመላ ተይዘው ገንዘብ ተጠየቁ» ኢሰመኮ
የዘፈቀደ፣ ጅምላ እና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት ስለመኖሩ
በምርመራው ግኝት የዘፈቀደ፣ ጅምላ እና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት ስለመኖሩም ተገልጿል። በአማራ ክልል የመንግሥት አመራሮች፣ የጸጥታ ተቋማት አመራሮች እና አባላት፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ዳኞች፣ ዓቃብያነ ሕግ፣ የምክር ቤት አባላት፣ ነጋዴዎች፣ ጋዜጠኞች፣ መምህራን፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ በግል ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአብነት (የቆሎ) ተማሪዎች የዚህ ሰለባ መሆናቸው ተዘርዝሯል። ከ6ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች መደበኛ ባልሆ አራት ማቆያዎች አሁን ድረስ ታስረው እንደሚገኙም ኢሰመኮ አመልክቷል።
የኮሚሽኑ የበላይ ኃላፉ ወይዘሮ ራኬብ መሰለ እንዳሉት የዳኝነት ነጻነት መሸርሸር እና በዳኞች ላይ የሚደርሱ ትንኮሳዎች መቀጠልም በዚህኛው ሪፖርት በአሳሳቢነቱ የተመላከተ ነው።የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በግጭት ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም በማድረግ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በቁርጠኝነት እንዲሠሩ፤ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ በማስገደድ የተሰወሩና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ጉዳያቸው በመደበኛው የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት እንዲታይ ሲልም ጠይቋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ