በጌዲዮ ዞን በመሬት ናዳ የሞቱትን ፍላጋ ቀጥሏል
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 24 2017
በጌዴኦ ዞን ቡሌ ወረዳ በመሬት ናዳ በአፈር ተቀብረው የሚገኙ ሰዎችን በቁፋሮ ለማውጣት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ገልጸዋል ፡፡ በወረዳው በናዳው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩንም የዞኑ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አስታውቋል፡፡
የጌዴኦው የመሬት ናዳ
በጌዴኦ ዞን ቡሌ ወረዳ በምትገኘው አጋምሳ ቀበሌ በአምስት የመኖሪያ ቤቶች ውስጥ የነበሩ ሰዎች ከአፈር በታች በናዳ ተቀብረው ይገኛሉ ፡፡ ቁጥራቸው እስከ 17 ሊሆን እንደሚችል አደጋው የተከሰተበት ቀበሌ ነዋሪዎች ይናገራሉ ፡፡ አርሶአደር ሚጁ ኦዳሌ በአሳዛኙ የናዳ ክስተት ቤተሰቦቻቸውን ካጡት መካከል ናቸው ፡፡ ገበያ ሄደው ሲመለሱ ሁለት ልጆቻቸው በናዳ ተቀብረው እንዳገኟቸው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት አርሶአደሩ “ በናዳው ባለቤቴ ብትተርፍም ሁለቱ ልጆቼ እንዲሁም በቤቱ አቅራቢያ ታስረው የነበሩ በጎችና ላሞች በናዳው ተቀብረዋል ፡፡ እስከአሁን የአንዷ ልጄ አስክሬን ሲገኝ የሌላኛዋ እየተፈለገ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡
የፍለጋ ሥራው
ናዳው በተከሰተበት የአጋምሳ ቀበሌ አሁን ላይ በአፈር ተቀብረው የሚገኙትን ለማውጣት ጥረት እየተደረገ ይገኛል ፡፡ ቀበሌው ከዋና መንገድ የሁለት ሰዓት የእግር ጉዞ የሚርቅና ተሽከርካሪም የማይገባበት መሆኑ ደግሞ ፍለጋውን ከባድ አድርጎታል ፡፡ ያም ሆኖ በቁፋሮው የቤት እንስሳት ፣ የእንሰት ተክሎች እና የመኖሪያ ቤት ጣራዎች መታየታቸው ሰዎቹ ወደ ተቀበሩበት ቦታ ሥለመቃረቡ ምልክት ተደርጎ ተቆጥሯል ፡፡ እስከአሁን የአንድ ህጻን አስክሬን መገኙትን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የቡሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቦራቆ በራሶ ቀሪዎቹን ፍለጋ ቀጥሏል ብለዋል ፡፡
የሰብአዊ ድጋፍ
በጌዴኦ ዞን ቡሌ ወረዳ አጋምሳ ቀበሌ ከደረሰው የናዳ ክስተት አስቀድሞ በቀናት ልዩነት በዞን ራጴ ወረዳ ተመሳሳይ አደጋን አስተናግዷል ፡፡ በወረዳው ጫራቃ እና ሀሮ በተባሉ ቀበሌያት ውስጥ በተከሰው አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ባለሥልጣናት ገልጸዋል ፡፡ አስክሬናቸው ከናዳው ሥር ወጥቶ በክብር እንዲያርፍም ተደርጓል ፡፡ በአሁኑወቅት በሁለቱም ወረዳዎች ተጨማሪ ጉዳት እንዳይከሰት ነዋሪዎችን ከአደጋ አካባቢዎች የማራቅ ሥራ መከናወኑን የጠቀሱት የጌዴዮ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ዜና ማሞ “ በአጋምሳ ቀሪ ተጎጂዎችን የማፈላለጉ ሥራ ቀጥሎ ይገኛል ፡፡ከፍለጋው ጎን ለጎን ለተጎጂዎች የሰብአዊ እርዳታዎችን የማቅረብ ሥራም እየተሠራ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡
የሜትሮሎጂ ማስጠንቀቂያ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተዳፋታማ በሆኑ አካባቢዎችበተደጋጋሚ በሚከሰት የመሬት ናዳለበርካቶች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ ይገኛል ፡፡ በክልሉ ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ባለፈው ዓመት ክረምት በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡በኢትዮጵያ አብዛኞቹ አካባቢዎች በሚቀጥሉት 10 ቀናት ከመካከለኛ እስከ ከባድ የዝናብ ሥርጭት ሥለሚኖር በወንዝ ዳርቻዎችና ረግረጋማ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሲል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ባፈው ሳምንት ማስታወቁ አይዘነጋም።
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሂሩት መለሰ
ፀሀይ ጫኔ