በጀርመኗ ሀምቡርግ ከተማ ባቡር ጣቢያ በርካቶች በስለት ተወግተው ቆሰሉ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 16 2017በጀርመኗ ሀምቡርግ ከተማ ትላንት አርብ ማምሻ በስለት ተወግተው ከቆሰሉት 18 ሰዎች መካከል አራቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገለፀ። ሌሎች ስድስት ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ፖሊስ ጥቃቱን በመፈፀም የጠረጠራትን አንዲት የ39 ዓመት ጀርመናዊት በቦታው በቁጥጥር ስር አውሏል። ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠረችው ሴት በአዕምሮ በሽተኛነት እንደምትታወቅ የጀርመን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በሀምቡርግ ባቡር ጣቢያ የሚገኙ መንገደኞችን በዘፈቀደ በስለት በመውጋት ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር የዋለችው ይቺው ጀርመናዊት ዛሬ ፍርድ ቤት ትቀርባለች።
ፖሊስ እስካሁን ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በወንጀሉ ሌላ ሰው አልተሳተፈም። መንገደኞቹ በስለት የተወጉት በአንድ ሰው ብቻ ነው። ፖሊስ የጥቃቱ አላማ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው የሚል እምነት እንደሌለው ገልጿል።
ከጎርጎሮሲያኑ ጥቅምት 1 ቀን 2023 ጀምሮ በሀምቡርግ ባቡር ጣቢያ እና በአካባቢው ሽጉጥ ይዞ መገኘት የተከለከለ ሲሆን ከታህሳስ 2024 አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ በሰሜናዊቱ የጀርመን ከተማ በሕዝብ መጓጓዣ ላይ ስለት ይዞ መገኘት የተከለከለ ነው ።
በደረሰው ጥቃት ምክንያት የመንገደኞች ጉዞ መስተጓጎሉን እና አንዳንድ ጉዞዎችም በባቡር ጣቢያው መሰረዛቸውን የጀርመን የባቡር ድርጅት ዶይቸ ባን አስታውቋል።
በጀርመን በአንድ ሳምንት ውስጥ የስለት ጥቃት ሲፈፀም ይህ ሶስተኛው መሆኑ ነው። እሁድ ማለዳ አንድ የሶሪያ ተወላጅ የሆነ የ35 ዓመት ተጠርጣሪ በቤይሌፌልድ ከተማ በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አምስት ሰዎችን በስለት ያቆሰለ ሲሆን፣ አራቱ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በርሊን ውስጥ አንድ የ13 ዓመት ልጅ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ የ12 ዓመት ተማሪን በስለት ወግቷል በሚል አርብ ዕለት በቁጥጥር ስር ውሏል።