በጀርመን የውጭ ዜጎች የሥራ እድል
ማክሰኞ፣ ሰኔ 24 2017ብሬትልስማን የተባለው የጥናት ተቋምና የጀርመን መንግስት ጀርመን በአሁኑ ጊዜ ከ288 ሺህ እስከ 400 ሺህ የሚደርስ ሀገሪቱ በሚያስፈልጋት ሞያ የተካነየውጭ ሠራተኛኃይል ትሻለች። የጀርመን የፌደራል የሠራተኞች ቅጥር መስሪያ ቤት በዋነኛነት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በህክምና በቴክኒክና በትምሕርት ዘርፍ 646 ሺህ ክፍት የስራ ቦታዎች እንዳሉ በጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 2025 አስታውቆ ነበር። የዶቼቬለዎቹ ሲልያ ፍሮህሊሽና ግያና ካሪና ግሩን እንደዘገቡት ወደ ጀርመን የሚደረገው ፍልሰት ከቆመ ከዛሬ 15 ዓመት በኋላ የሠራተኛ ኃይል ቁጥር እጅግ እያሽቆለቆለ ይሄዳል። ይህም በሀገሪቱ የኤኮኖሚ እድገትና ተፎካካሪነት ላይ አሉታዊ መዘዞችን ማስከተሉ አይቀርም።
የቪዛ ችግር
ለዚህ ዘገባ ግሬስ ኦቼንግ የሚል ስም የተሰጣት የ26 ዓመትዋ ወጣት ኬንያዊት በዓለም አቀፍ ግንኙነት የዲግሪ ትምሕርት ለመከታተል የነጻ ትምሕርት እድል አግኝታ ጀርመን ለመምጣት ውጣ ውረድ ገጥሟታል። ለቪዛ ማመልከቻ ያስገባችው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር ።ኦቼንግ እንደምትለው ችግሩ የሚጀምረው ከቪዛ አሰጣጡ ሂደት ነው። ምንም እንኳን ኦቼንግ አስፈላጊ መስፈርቶችን ብታሟላም ጀርመን መግባት የሚያስችላትን ቪዛ ለማግኘት ሁለት ወራት ወስዶባታል። ከዛሬ18 ዓመት በፊት ጀርመን የመጣችው ቴሬስያ ትሮይትላይንም ተመሳሳይ ተሞክሮ አላት። ትሮትላይን ጀርመን የመጣችው በሞግዚትነት ነበር ። ያኔ የጀርመን ቢሮክራሲ ብቻ ሳይሆን ቋንቋውም አንገላቷታል።
ይሁንና የያኔው ተሞክሮዋ ታዲያ አሁን ያለችበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ረድቷታል። አሁን ነርስ ናት። ከባለቤትዋ ጋር ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አዛውንቶች የሚንከባከብ አገልግሎት ሰጭ ድርጅት ሀይድልበርግ ከተማ አቅራቢያ አላቸው። ድርጅታቸውከሀያ በላይ አፍሪቃውያን ነርሶች እና ሰልጣኞች አሉት። ድርጅታቸው በቅርቡ ባለሞያዎችን ከኬንያ ወደ ጀርመን ለማምጣት በሂደት ላይ ነው።ሆኖም ከቪዛ ጋር የተያያዘው ቢሮክራሲ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ትሮይትላይ እንደምትለው ችግሩ ቪዛ ብቻ አይደለም እዚህ ከመጡ በኋላ የሚያጋጥሙ ሌሎች መሰናክሎችም አሉ።
«እጅግ ተስፋ አስቆራጩ ነገር የመኖሪያ ቤት እጥረት ነው። በጣም ተነሳስቼ እዚህ ልመጣ እችላለሁ ግን የት እኖራለሁ? ለምሳሌ ጀርመን መጥተው መኖሪያ ያጡ በርካቶችን አውቃለሁ። ይሄ አንዱ ነገር ነው። ሌላው ቢሮክራሲ ነው። በአሁኑ ጊዜ ከኬንያ የመጀመሪያ የባለሞያዎች ቡድን ወደ ጀርመን ልናስመጣ በሂደት ላይ ብንሆንም ቢሮክራሲው አንቆ ይዞናል።»
ከተሞክሮዋ እንደምታናገረው በጀርመን በሰለጠኑበት ሞያ መሰማራቱ ቀላል አይሆንም። የውጭ ዜጎች ከሀገራቸው ለሚያመጡዋቸው ምስክር ወረቀቶች እውቅና መስጠቱ ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ከኅብረተሰቡ ጋር መዋሀዱም እንዲሁ ቀላል አይደለም።
Opportunity Card «የእድል ካርድ»
ከሰኔ 2024 ወዲህ ጀርመን ከአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ውጭ በሆኑ ሀገራት ለሚገኙ፣ ተፈላጊ በሆኑ ሞያዎች ለሰለጠኑ ባለሞያዎች Opportunity Card «የእድል ካርድ» የተባለ ቪዛ መስጠት ጀምራለች። ይህም የውጭ ዜጎች ፣ያለ ቋሚ የስራ ውል፣ ጀርመን ከገቡ በኋላ ፣ስራ የሚፈልጉበትን እድል የሚሰጥ ነው። የሚያስፈልገው ቢያንስ የሁለት ዓመት የሙያ ስልጠና ወይም የዪኒቨርስቲ ዲግሪ እና መሰረታዊ የጀርመንኛ ወይም የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ ነው። ለዚህ ቪዛ ብቁ ለሆኑ ጀርመን ውስጥ የሚፈለግ የሙያ ልምዳቸው እድሜና ክህሎታቸው ይመዘናል ። በጎርጎሮሳዊው 2025 ለዚህ ዓይነቱ ቪዛ፣ ስራ ፈላጊዎች በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የቪዛ መስጫ ቢሮዎች በኦንላይን ማመልከት ይችላሉ። ይህ አይነቱ የቪዛ አሰጣጥ አሰራር የእድል ካርድን ጨምሮ ሌሎች ቪዛዎችንም የሚያፋጥንና ይበልጥ ውጤታማም የሚያደርግ ይሆናል ተብሎ ነበር። ይሁንና በአዲሱ አሠራር ያመለከቱ እንደተናገሩት ይህም እንደሌሎቹ የቪዛ አሰጣጥ ስርዓቶች ፈጣን አይደለም። ከጀርመን አፍሪቃ የንግዱ ማኅበር ካዳ ካማራ እንደሚሉት ቪዛ አሁንም ትልቁ ችግር ነው።
«ቪዛ ትልቁ ችግር ነው እላለሁ። የዕድል ካርድ ለአንዳንድ ሰዎች የእድል ካርድ ነው። ሆኖም ለተሻሻለው የመግቢያ ቪዛ ሁኔታ አስፈላጊ የሆኑትን መስፈርቶች ማሟላት መጀመሪያ ላይ አመልካች ሊያሳካው የሚገባ ጉዳይ ነው። ይህ ግን በዚህ ወቅት ቀጣሪ ኩባንያዎች የሚፈልጉት መስፈርት ላይሆን ይችላል ኩባንያው ለጀርመንኛ ቋንቋ ችሎታ ቅድሚያ ባይሰጠውም የፌደራል መንግስት ግን መስፈርት አስቀምጧል፤ከዚህ ሌላ ናይጀሪያን በመሳሰሉ ሀገራት ለጀርመን ቪዛ ቀጠሮ ማግኘት የመጀመሪያው ፈተና ነው።»
ጀርመን ለምን የውጭ ዜጋ ሠራተኞችን መማረክ አልቻለችም?
ምንም እንኳን ጀርመን ተፈላጊ በሆኑ የስራ መስኮች ፣ብዙ አፍሪቃውያን እድሉን ባያገኙም የሰለጠኑ ባለሞያዎችን ለመሳብ የሚያስችል የፍልሰት ስምምነት ፣ጀርመን ከወራት በፊት ከኬንያ ጋር ተፈራርማለች። የቀድሞው የጀርመን መራኄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ በወቅቱ ኬንያ በርካታ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሰለጠኑ ባለሞያዎች እንዳሏት ተናግረው ነበር። እነዚህ ባለሞያዎችም ጀርመን ተጨማሪ ስልጠና በማግኘት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጀርመን እስካሁን የፍልሰት ስምምነት መፈራረም የቻለችው ከኬንያ ጋር ብቻ ነው። በዚህ ዓመት በታኅሳስ ወር በዚህ ስምምነት ጀርመን የመጡት 90 ኬንያውያን ነርሶች ብቻ ናቸው። አሁንም ታዲያ የጀርመን ቢሮክራሲ እዚህ መምጣት ለሚፈልጉ በርካታ የሰለጠኑ ባለሞያዎች ተስፋ አስቆራጭ መሆኑ አልቀረም።
በስምምነቱ መሠረት ከተጠየቁ ቪዛዎች በርካታዎቹ ውድቅ ተደርገዋል።በአጠቃላይ ከሰሀራ በታች ለሚገኙ የአፍሪቃ ሀገራት ከፍተኛ የሚባል የቪዛ ክልከላ ተደርጎባቸዋል እንደ ሲልያ ፍሮህሊሽ ዘገባ ። ከግራ ፓርቲ ክላራ ቡንገር በሚያዚያ በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተገኙበት ወቅት በ2022 ዓም ከናይጀሪያ ከቀረበ 7914 የቪዛ ማመልከቻ 3400 ው፣ ከጋና 8152 የቪዛ ማመልከቻ 1972ቱ ውድቅ ተደርገዋል።
ዶቼቬለ ከጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች ባገኛቸው መረጃዎች መሠረት በጎርጎሮሳዊው 2022 ጀርመን ለ 50,815 አፍሪቃውያን ቪዛ ሰጥታለች። ከመካከላቸው 20,545 ቱ 40 በመቶው ለስራ የተሰጠ ቪዛ ነው። ቪዛውን ካገኙት ውስጥ ተመራማሪዎች፣ በላቀ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሞያዎች ፣ ለሞግዚትነትም የመጡ ይገኙበታል ።ከሰሀራ በታች ለሚገኙ የአፍሪቃ ሀገራት ዜጎች ደግሞ 22 ሺህ 668 ቪዛዎች ተሰጥተዋል። ከመካከላቸው 7966 ቱ የስራ ናቸው። ቪዛ የተሰጠው ለየትኛዎቹ ሀገራት ዜጎች እንደሆነ ግን የጀርመን ፌደራል መንግሥት ይፋ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነም።
ጀርመን የውጭ ዜጋ ሠራተኞችን ትፈልጋለችን?
ጀርመን በሚፈለጉ ሞያዎች ለተካኑ የውጭ ዜጎች መስህብ መሆንዋን ብዙዎች እርግጠኛ አይደሉም። ለካማራ ለስራ ለሚመጡ ሰዎች ከኅብረተሰቡ ጋር ተዋህዶ መኖር ትልቁ ነገር ነው። ግን ጀርመን የአፍሪቃውያን መኖሪያ መሆን ትችላለች ወይ? መንግስት ዘረኝነት እና ሌሎች ገፊ ሁኔታዎችን ለማስተካከል ምን ያህል ዝግጁ ነው ሲሉ ጠይቀዋል።
«መንግስት ተፈላጊ ሠራተኞችን ለማስገባት ያለውን ጉጉት ስናይ እዚህ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። መንግሥት ምን ያህል ማስተካከያዎችን ለማድረግ ፈቃደኛ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ጀርመን በርግጥ የኬንያውያን የጋናውያን ወይም የሴራሎናውያን ወይም የደቡብ አፍሪቃውያን አዲሷ መኖሪያ መሆን ትችላለች ወይ? በዚህ ረገድ የውጭ ዜጋውን ከኅብረተሰቡ ጋር ማዋሀድ እና የዘረኝነትን ችግር መፍታት እጅግ አስፈላጊ ነው። የፌደራል መንግስቱ ሰዎቹ ተቀባይነት እንደሚኖራቸው ግልጽ አቋም ሊይዝ ይገባል። »
ለትሮይትላይን እና ለኦቼንግ ከተሞክሮአቸው ጀርመን ውስጥ ከኅብረተሰቡ ጋር ሙሉ በሙሉ የተዋኅደ ሕይወት ለመምራት ጀርመንኛ መናገር አስፈላጊ መሆኑን ተረድተዋል። በትሮይትላይን አስተያየት መንግሥትእዚህ መምጣት የሚፈልጉ ሰዎችን እዚያው ባሉበት ጀርመንኛ እንዲማሩ መደገፍ አለበት። ምክንያቱም እንደ ትሮይትላይን ያለ ጀርመንኛ ቋንቋ የትም መድረስ አይቻልም ። ካማራ ደግሞ ጀርመን ከፍተኛ ክህሎት ያላቸውን ባለሞያዎች ለመውሰድ ከሌሎች ባለሞያ ፈላጊዎች ጋር መፎካከር እንዳለባት ልትገነዘብ ይገባል ብለዋል።
«እኔ እንደማስበው ያሉት እድሎች መጥፎ አይደሉም። ምክንያቱም አሁን ማድረስ አለብን። ጀርመን ለረዥም ጊዜ በቅንጦት ስታርፍ ቆይታለች። አሁን ዓለም አቀፋዊ ጥምረት እየፈራረሰ ነው። እናም አዳዲስ አጋሮች መፈለግ አለብን። ብዙዎቹ በአፍሪቃ አህጉር ውስጥ ነው የሚገኙት።»
ትሮይትላይንን ለመሳሰሉት የጀርመን ኩባንያዎች ዋናው ጉዳይ የቢሮክራሲያዊ ችግሮች መወገድ ነው። እርስዋና ባለቤቷ አዳዲስ ሠራተኞችን ከኬንያ አምጥተው ለመቅጠር እንዲሁም የግል የጀርመንኛ ቋንቋና የነርሶች ትምሕርት ቤት ለመክፈት ወስነዋል። ትሮይትላይን የትንሹ ድርጅቷ ዓላማ በኬንያ በኬንያ ስራ አጥነትን መከላከልና ጀርመን የሚፈለጉ ሠራተኞችን ማምጣት ነው ትላለች። በርስዋ አስተያየት ወደ ጀርመን የሚደረግ ፍልሰት በጉዳዩ ውስጥ የሚሳተፍ ሁሉ አሸናፊ የሚሆንበት ነው። በጀርመን ከሚፈለጉት የውጭ ዜጋ ሠራተኞች ጥቂቱ ብቻ ጀርመን የመምጣታቸው ምክንያት ላይ ያተኮረው የዛሬው ዝግጅታችን በዚሁ አበቃ። ኂሩት መለሰ ነኝ ደኅና ቆዩኝ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ