በጀርመን የኢትዮጵያውያን ሕይወትና አገራዊ ራዕይ
ረቡዕ፣ መስከረም 9 2011እዚሕ ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያንም እንደ አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለዉጡን ይደግፋሉ።ወደ ሐገራቸዉ ለመለመለስም የለዉጡን ሒደት በጥሞና እየተከታተሉ መሆናቸዉን እየገለጡ ነዉ።የዛሬዉ አዉሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ኢትዮጵያዉያን በብዛት ወደ ጀርመን የተሰደዱበትን ጊዜ፤ስለ ትዉልድ ሐገራቸዉ ያላቸዉን ግንዛቤ እና አዲስ ለተጀመረዉ ለዉጥ የሚያደርጉትን ድጋፍ ይቃኛል።
የኢትዮጵያ እና የጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከአንድ ምዕተ ዓመት የዘለለ ታሪክ እንዳለው የተለያዩ መዛግብት ይጠቁማሉ :: በሁለቱ ሃገራት መካከል የተጀመረው ትብብር ጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባው በተለይም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ እ.ኤ.አ ከ 1945-48 ዓ.ም በጀርመን በተከሰተው ከፍተኛ የምግብ እጥረት እና ረሃብ ችግር ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ 2 መቶ ሺህ ዶላር የሚያወጣ ቡና ብርድ ልብስ እና ሌሎችንም ቁሳቁሶች ለጀርመን ሕዝብ ከለገሱ በኋላ እንደሆነ ይነገራል::
ከዛሬ 45 ዓመታት በፊት የነበረውን ታሪክ ስንቃኝ ዜጎቻችን ውጭ ሃገር ለትምህርት ተልከው በማይቀሩበት እንዲህ እንደ አሁኑ ስደት ባልተስፋፋበት እና ለኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ክብር በሚሰጥበት ዘመን ጀርመን ውስጥ ኑሮዋቸውን የቀለሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ 12እንደማይበልጥ ከመረጃዎች መገንዘብ ይቻላል :: ኢትዮጵያ ለጀርመን በክፉ ቀን በዋለችው ውለታ ብቻ ሳይሆን ከወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ሥርዓት በፊት እምብዛም ከአገር የሚሰደድ ሰው ባለመኖሩ ኢትዮያውያን ያለቪዛ በፈለጉት ጊዜ ጀርመን ይገቡ እንደነበር በደርግ ሥርዓት ቀዳማዊ ኃይለስላሴን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት በተገደሉበት ወቅት ለወሬ ነጋሪ በተአምር ተርፈው ፍራንክፈርት ከተማ ኑሮዋቸውን የመሰረቱት በጀርመን አገር የአፍሪቃ እና የመካከላኛው ምሥራቅ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አማካሪ እንዲሁም ከፍተኛ ሽልማቶችን ያገኙ ታዋቂ ደራሲ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ ካሳ አጫውተውናል :: " ዲያስፖራ " የሚለው ቃል በማሕበረሰባችን ከመቼ ጀምሮ እየተለመደ እንደመጣ እና ሌላውንም ትዝታቸውን እንዲህ አውግተውናል ::
ዶክተር አስፋወሰን እንደገለጹት በጀርመን ከ 45 ዓመታት በፊት እሳቸውን ጨምሮ ከ 12 የማይበልጡት ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተገን ጠያቂዎች ነበሩ:: በዛው አመት ወታደራዊው የደርግ ሥርዓት በሚከተለው አምባገነናዊ ርዕዮተ ዓለም ምክንያት የኢትዮጵያውያን የስደት ተገን ጠያቂዎችን ቁጥር እ.ኤ.አ በ 1975 ዓ.ም ወደ 275 እንዳሳደገው የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያቤትን ጠቅሶ ዓለማቀፉ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት በጥናቱ አመልክትቷል:: ዛሬ በመላው ጀርመን ኑሮዋቸውን የመሰረቱ ከ 19ሺህ የሚልቁ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውንም መረጃው ይገልጻል:: በዛሬው የአውሮፓ መሰናዶዋችን በአገራችን የታየውን የለውጥ ሂደት እና የዲያስፖራውን ሚና በተመለከተ ሃሳባቸውን እንዲገልጹልን ከጠየቅናቸው መካከል ወይዘሮ ላቀች አንዷ ናቸው::በፍራንክፈርት ከተማ ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት ሴት የታክሲ ሾፌር የሆኑት ወይዘሮ ላቀች በኢትዮጵያ የሚታየው የለውጥ እንቅስቃሴ የተደበላለቀ ስሜት እንደፈጠረባቸው ነግረውናል :: በአንድ በኩል የፖለቲካው ምህዳሩ መስፋቱ ቢያስደስታቸውም በሌላ በኩል ደግሞ አልፎ አልፎ የብሔርተኝነት የዘረኝነት እና የደቦ ጥቃት እየተስፋፋ መሄዱ እንዳሳሰባው ይገልጻሉ:: ለዲያስፖራው ማሕበረሰብም የሚሉት አላቸው::
እንደ ኬንያ ያሉ የአፍሪቃ አገራት በዲያስፖራ የሚኖሩ ዜጎቻቸው አገር ውስት ገብተው በውጭ ያካበቱትን ሙያ ለወገኖቻቸው በማስተማር የዕውቀት ሽግግር እንዲያካሂዱ እና መዋዕለ ንዋያቸውንም በተለያዩ የልማት እና የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው በከፍተኛ ሁኔታ የአገራቸውን ምጣኔ ሃብት እንዲያሳድጉ አመቺ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል :: ላለፉት 50 ዓመታት በውጭ የኖሩት ዶክተር ልዑል አስፋወሰን ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ለመርዳት በተለያዩ ጊዜያት የውጭ ኢንቨስትሮችን ጭምር ይዘው በመሄድ አያሌ ጥረቶችን ቢያደርጉም በነበረው የቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረድ ምክንያት ያሰቡትን ያህል ማሳካት እንዳልቻሉ በመጥቀስ አሁን በአገሪቱ የሚታየው የለውጥ ሂደት ግን የዲያስፖራውን ጥረት እንደሚያበረታታ ያላቸውን ተስፋ ገልጸውልናል ::
ሌላው ያነጋገርናቸው አቶ ተወልደ ይባላሉ:: ኤርትራዊ ናቸው ባለቤታቸው ኢትዮጵያዊት በመሆናቸው በዓላትን በደስታ ስሜት ሁሌም እንደሚያከብሩ ነው የነገሩን :: ከ 40 ዓመታት በላይ ጀርመን የኖሩት አቶ ተወልደ ፍራንክፈርት ውስጥ በንግድ ተሰማርተው ነው ኑሮዋቸውን የሚገፉት :: በአዲስ ዓመት በአዲስ ተስፋ የተጀመረው የሰላም የአንድነት እና የለውጥ ጉዞ ስኬት ለሁለቱም አገራት እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ ከበዓሉ ጋር ተዳምሮ ልዩ የደስታ ድባብ ስሜትን እንደፈጠረላቸው ነግረውናል:: አቶ ተወልደ ለዘመናት አብረን የኖርን ሕዝብ ነን :: ከመገዳደል ምናተርፈው የለም :: ምድሩ በቂያችን ነው :: ዲያስፖራው ለለውጡ ስኬት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አጭር መልዕክት አስተላልፈዋል ::
በውጭ የሚኖረው ማሕበረሰብ ከራሱ አልፎ አገሩን መጥቀም የሚችለው የሕይወት ዋስትና አግኝቶ በሚኖርበት አገር የባህል እና አብሮ የመኖር ውህደትን ፈጥሮ ሕግ እና ስርአትን አክብሮ በሰለጠነበት ሙያ እና በአቅሙ ሰርቶ ሕይወቱን መለወጥ ሲችል እንደሆነ ይታመናል :: ይሁን እንጂ ኑሮዋቸውን ለማሻሻል እና ከሚደርስባቸው የፖለቲካ ጥቃት ሸሽተው ተገን ጠይቀው የሚኖሩ አንዳንድ ወገኖቻችን በተለይም ወጣቶች በቡድን ጠብ በአልኮል መጠጥ ስካር በአደገኛ ዕጽ እንዲሁም በልዩ ልዩ የደረቅ ወንጀሎች እየተከሰሱ ውጥን እና ተስፋቸው በአጭሩ ሲቀጭ በሙያቸው አጋጣሚ መታዘባቸውን ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ በቁጭት ገልጸውልናል:: ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ በሕግ ሙያ እዚሁ ጀርመን ከፍራይድሪሽ ሺለር ዩኒቨርሲቲ የዶክተሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል:: በጥብቅና በሕግ አገልግሎት እና በትርጉም ስራ የግል ቢሮዋቸውን ፍራንክፈርት ከተማ ውስጥ ከፍተው እና ሰራተኞችን ቀጥረው እያገለገሉ ይገኛሉ:: ለዲያስፖራው ማህበረሰብ እንዲህ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዶክተር ልዑል አስፋወሰን ሕዝቡ በተለይም ደግሞ በውጭ የሚኖረው የዲያስፖራው ማሕበረሰብ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ተስፋ ሰጭ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲደግፍ አልፎ አልፎ የሚታዩ ግጭቶችም በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን መንገድ በማመቻቸቱ ረገድ የበኩሉን አገራዊ ድርሻ እንዲወጣም ምክራቸውን ለግሰዋል::
እንዳልካቸዉ ፈቃደ
ነጋሽ መሐመድ