ጀርመን የተማሩ ኢትዮጵያውያን ማኅበር፤ «የኢትዮ-ጀርመን ግንኙነት ድልድይ»
ሐሙስ፣ የካቲት 20 2017የጀርመን ተማሪዎች ማኅበር ፦ «የኢትዮ-ጀርመንን ግንኙነት ከፍ ማድረግ ነዉ»
«ጀርመን አገር የተማሩ ኢትዮጵያዉያን ቁጥር ከአፍሪቃ አንደኛ ነዉ። ከነካሜሩን ከነ ኬንያን ሁሉ ይበልጣል። ይህ በፊት በነበረዉ የደርግ ሥርዓት ምስራቅ ጀርመን የተላኩትን፤ እና ምዕራብ ጀርመን የተማሩትን ሁሉ ማለት ነዉ። ከ 10 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዉያን ተማሪዎች በጀርመን አገር ተምረዉ የተመለሱ አሉ፤ በአሁኑ ወቅት አዉሮጳ ዉስጥ የሚኖሩ አሉ፤ ወደ ሰሜን አሜሪካም የተሻገሩ አሉ»የኢትዮጵያ-ጀርመን የምርምር እና የባህል ልዉዉጥ
ፕሮፊሰር አበበ ድንቁ ይባላሉ፤ በጎርጎረሳዉያኑ 1996 ዓ.ም በጀርመን ሽቱትጋር ከተማ በሚገኝ ዩንቨርስቲ የሦስተኛ ዲግሪያቸዉን በምህንድስና ሞያ አጠናቀዉ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዉ አገራቸዉን እያገለገሉ ይገኛሉ። ኢንጂኔር ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ በቀድሞ መስርያ ቤታቸዉ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በኢንጂኔሪንግ ፋክልቲ፤ ተባባሪ ዲንነትን ጨምሮ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነዉ፤ ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል። አሁን ከሞያዊ አግልግሎታቸዉ ባሻገር በጀርመን አገር የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ማህበር የቦርድ ዋና ሰብሳቢ ናቸዉ።
አዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ኢንጂኔር አበበ ድንቁ፤ በጀርመን አገር የተማሩ የኢትዮጵያዊያን ማህበር የቦርድ ዋና ሰብሳቢ ከመሆን ባሻገር ላለፉት ሃያ ዓመታት የጀርመን የከፍተኛ ትምህርት ልውውጥ አገልግሎት በጀርመንኛው ምህፃሩ/DAAD/ ዉስጥ ባለ ፕሮግራም የቀጠናዉ ኤክስፐርት ሆነዉ እያገለገሉ ይገኛሉ። ፕሮፊሰር አበበ ድንቁ እንደነገሩን በአፍሪቃ ዉስጥ ኢትዮጵያ በጀርመን ያፈራቻቸዉ ምሁራን ቁጥር ከአፍሪቃ ሃገራት ቀዳሚዉን ስፍራ የያዘ ነዉ። ይህ ሊሆን የቻለዉ ቀደም ሲል በምስራቅ ጀርመን የተማሩትን ምሁራን ሁሉ ያካተተ በመሆኑ ነዉ፤ ሲሉ ነግረዉናል። ከጀርመን ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱ ምሁራን አዲሱን ኑሮዋቸዉን በቀላሉ ለማደራጀት፤ የልምድ ልዉዉጥ ለማድረግ ስንል ዛሬ 29 ዓመት ገደማ ጀርመን አገር የተማሩ የኢትዮጵያዊያን ማህበርን አቋቋም፤ በኢትዮጵያም ቢሆን፤ የጀርመናዉያን ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም ሲሉ ኢንጂኔር አበበ ድንቁ ገልፀዋል።
በጀርመን የተማሩ ኢትዮጵያዉያን ቁጥር 10 ሺህ ይደርሳል
«በኢትዮጵያ በጀርመን አገር የተማሩ ባለሞያ ዜጎች ቁጥር ከአፍሪቃ አንደኛ ነዉ። ጀርመናዉያንም በኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አሁን ትንሽ ቀንሷል፤ ብዙ ነዉ። GIZ በሚባለዉ የጀርመን ድርጅት ፤ ዓለም ላይ ካለዉ ፕሮጀክት ትልቁ ድርሻ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነበር። ስለዚህም ጀርመን እና ኢትዮጵያ ካላቸዉ የ 120 የዘለለ ይፋዊ ዲፕሎማስያዊ ግንኙነት፤ እንዲህ አይነት ነገር መሆኑ ጠቃሚ ነዉ ፤ በሚል በጀርመን አገር የተማሩ የኢትዮጵያዉያን ማህበር ተቋቋመ። የማኅበሩ መቋቋም ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል፤ ጀርመን አገር ተምረዉ ወደ አገር ቤት የመጡ ኢትዮጵያዉያን፤ ሃገር ቤት ሲገቡ ወደ ማኅበረሰቡ መዋሃድ እንዲችሉ ማድረግ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ የቀድሞ የጀርመን ተማሪዎች ከመንግሥት ጋር ያላቸዉን ግንኙነት አጠናክሮ መቀጠል። ከጀርመን ከተሞች ጋር የኢትዮጵያ ከተሞችን እህትማማች በማድረግ ልምድ መቀያየር፤ ቋንቋዉን በማስተማር ፤ ከጀርመን ኤንባሲ ጋር ቅርብ ግንኙነት መፍጠር፤ እና በመሳሰሉት ተቋቁመን በዚህም የተወሰነ ርቀት ሄድዋል።»
የኢትዮጵያ እና የጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ዳግማዊ አጼ ሚንሊክ ንጉሰ ነገስት ዘመነ መንግስት ታሪክ፤ ወደ ጎርጎርሳውያኑ 1905 እና 1907 ላይ ይመልሰናል። ከ 120 ዓመታት በላይ ማለትም ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በተሻገረው የኢትዮጵያ እና ጀርመን ይፋዊ ግንኙነት፤ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ወደ ጀርመን ገበያ ዋነኛዋ ቡና ላኪ በመሆን እንዲሁም ጀርመን በቀጥታ ለኢትዮጵያ የምታደርገው ኤኮኖሚያዊ ድጋፍ ይጠቀሳል።ጀርመን ለኢትዮጵያ የሰብአዊ አቅርቦት ተጨማሪ ድጋፍ ማድረጓ
በኢትዮጵያ የሚገኙት የቀድሞ የጀርመን እና የኢትዮ ጀርመን ማህበረሰብ ቀላል አይደለም ያሉን ኢንጂነር አበበ፤ በጀርመን ተምረዉ ወደአገራቸዉ የተመለሱት ኢትዮጵያዉያን ምሁራንም በአብዛኛዉ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
«በነገራችን ላይ ከጀርመን አገር የተማሩ ሰዎች፤ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ እርከን ፤ ከፍተኛ ስልጣን የያዙ ይገኙበታል። በተለይ አንድ ወቅትማ ፕሬዚደንት ለመሆን የጀርመን ተማሪ መሆን ያስፈልጋል ይባል ነበር። የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፤ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ፤ የሃዋሳ ዩንቨርስቲ ፕሬዚዳንት፤ ወዘተ በአብዛኞቹ የጀርመን ተማሪ ኢትዮጵያዉያን ነበሩ። እኔም በአጋጣሚ የመጣሁት ከኢንጂኔሪንግ ተቋም ነዉ፤ ኮሌጁብ በዲንነት ሲመሩ የነበሩት የቀድሞ የጀርመን ተማሪ ነበሩም እሳቸዉን ተክቼ እኔም ዲን ሆኜ ተተካሁ።»
ሌላዉ በጀርመን አገር የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ማህበር ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ብርሃኑ በየነ ናቸዉ። ዶ/ር ብርሃኑ በሰሜናዊ ጀርመን የወደብ ከተማ በሆነችዉ ሃምቡርግ ዩንቨርስቲ በኮምፒዉተር ሳይንስ ዘርፍ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ተምረዉ በዝያዉ ዩንቨርስቲ በምርምር ሥራ እና በመምህርነት ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል። ዶ/ር ብርሃኑ በጀርመን በአጠቃላይ ለ30 ዓመታት ኖረዉ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ወደ አስር ዓመት ሆንዋቸዋል።
የማህበሩ አባላት ቁጥር ስንት ነዉ?
« በአባላት ደረጃ ማህበሩ ሁለት አይነት የአባላት አይነት ነዉ ያለዉ። የተመዘገቡት እና በወረቀታችን ስማቸዉ የተመዘገቡት አባላት 838 አባላት ያሳያል፤ የአባል መዝገቡ። ነገር ግን ንቁ ሆነዉ የሚሳተፉ እና በተለያዩ ጊዜያት የሚካሄዱ ስብሰባዎችን እና ሌሎች የማህበሩን እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉ፤ የአባልነት መዋጮችን በየጊዜዉ የሚከፍሉ ከ150 እስከ 180 ይሆናሉ።»
በጀርመን አገር የተማሩ የኢትዮጵያዊያን ማህበር ፤ በጀርመን መንግሥት የሚታገዘዉ ፕሮጀክት ድጋፍ የሚሰጣቸዉ ከተለያየ አገር የመጡ እና በኢትዮጵያ ዩንቨርስቲዎች ዉስጥ የሚማሩ ስደተኞችን ማኅበሩ በመተባበር እና በማገዝ ወደ ስምንት ዓመታት በበላይነት ይመራል ያሉን ፤ ፕሮፊሰር አበበ ድንቁ ናቸዉ።
«ምን ማለት ነዉ ፤ የጀርመን መንግሥት በስደት ላይ ያሉ ተማሪዎችን፤ ማስተማር እንደዋና ጉዳይ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነዉ። ይህም በመሆኑ ለምሳሌ ኢትዮጵያዉስጥ የሚገኙ ኤርትራዉያን፤ ሱዳናዉያን፤ ሶማልያዉያን፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ባሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዉስጥ ያስተምራል። እና ወደ 2000 ያህል ተማሪዎች አንዳንድ ጊዜ በዓመት እናስተምራለን። ይህ የሆነዉ ከተለያዩ የጎረቤት ሃገራት የመጡ የከፍተኛ ተቋማት መማር የሚችሉ ስደተኞች የጀርመን መንግሥት ገንዘቡን እየሰጠ በኢትዮጵያ ዙርያ በሚገኙ ዩንቨርስቲዎች ዉስጥ ይማራሉ። ከሱዳን የመጡት በጋምቤላ ዬንቨርስቲ፤ ከሶማልያ የመጡት ጅጅጋ ዩንቨርስቲ፤ ከሱዳን ወይም ከሌላ የመጡት በባህርዳር ዩንቨርስቲ ፤ በዲላ ዩንቨርስቲ ፤ ከኤርትራ የመጡት በአብዛኛዉ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በመሳሰሉት እየገቡ እንዲማሩ፤ የጀርመን መንግሥት ገንዘብ እየሰጣቸዉ፤ የኛ ማህበር-በጀርመን አገር የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ማህበር ደግሞ የመመዝገብያ እና ሌሎች ነገሮችን እየሰራ በርካታ ተማሪዎች ከከፍተኛ ተቋማቱ ለመመረቅ እንዲበቁ፤ አግዘናል። ይህን አይነት ሥራ ከስደተኞች ጋር የፈፀመ ማህበር በኢትዮጵያም ይሁን በቀጣናዉ የለም። እንደዉም ማህበራችን በሌሎች ቀጣናዊ ስብሰባዊች ላይ ከሌሎች ማህበራት ጋር ስንገናኝ ስራችሁ በጣም የሚያስቀና ነዉ ይሉናል።»
ማኅበሩ ከጀርመን ጋር በመተባበር ስደተኛ የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎችን ይረዳል
በማኅበር የመደራጀታችን ዋናዉ ዓላማ የኢትዮ-ጀርመንን ግንኙነትን ከፍ ማድረግ ነዉ ያሉን ዶ/ር ብርሃኑ በየነ፤ ከጎረቤት ሃገሮች የሚመጡ እና በዩንቨርስቲ ትምህርት ጀምረዉ የነበሩ ተማሪዎችን በማገዝ በትንሽ ገንዘብ የተጀመረዉ በጀት በአሁን ሰዓት ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር እንደሆነዉ እና፤ ይህ አይነቱ ማኅበር በአፍሪቃ አንጋፋ አድናቆትን ያተረፈ መሆኑን ተናግረዋል።
«ከጎረቤት ሃገራት የሚመጡ እና በከፍተና ተቋማት ለሁለተኛ እና ለመጀመርያ ዲግሪ መማር የሚፈልጉ ተማሪዎችን ለማገዝ በትንሽ ገንዘብ የተጀመረዉ ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ወደ አንድ ሚሊዮን ዩኤስ ዶላር፤ ትልቅ ኦፊስ ኖሮናል። ይህ ገንዘብ በቀጥታ ከጄኔቫ ነዉ የሚመደበዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥም ይህን ስራ የሚያግዙ የመንግሥት ድርጅቶች አሉ። የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ን የመሳሰሉ፤ በቅርብም በርቀትም እያገዙ ያሉ ድርጅቶችም አሉ። ስለዚህም በጀርመን አገር የተማሩ የኢትዮጵያዊያን ማህበር ይህ ስራዉ በጀርመን ኤንባሲም በኩል ትልቅ አድናቆትን አግኝቶበታል፤ በመቀጠለም እየሰራ ነዉ። እንደመታደል ሆኖ በጀርመን ሃገር የተማሩ ኢትዮጵያዉያን መካከል በትልልቅ ሚኒስትር መስርያቤት ዉስጥ በሚኒስትር የሚያገለግሉ ናቸዉ። እነሱንም የማህበራችን አባል በማድረግ፤ አገር ዉስጥ ተጽኖ መፍጠር ይቻላል። ከጀርመን መንግሥት ፤ ከ BMZ፤ ከ Chamber of Commerce ከሚባሉት ትላልቅ ተቋማት ልዑካን በሚመጡ ጊዜ የኛ ማህበር እንደ አገናኝ ድርጅት ሆኖ ያገለግላል። በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲም፤ በኢትዮጵያ ያሉ ትልቅ ሰዎችን ለማግኘትም ሆነ፤ ስለኢትዮጵያ ማወቅ ከፈለጋችሁ፤ አብሮ ለመስራትም የሚመች ማህበርም አለ በሚል፤ የኛን ማህበር ነዉ የሚያገናኘዉ። በጀርመን አገር የተማሩ የኢትዮጵያዊያን ማህበርም ቁልፍ አጋር በመሆን ያስተናግዳል።የጀርመናዊዉ ሊቅ ሂዮብ ሉዶልፍና የአባ ጎርጎርዮስ ወዳጅነት
የጀርመን የከፍተኛ ትምህርት ልውውጥ አገልግሎት በጀርመንኛው ምህፃሩ/DAAD/ የተመሰረተበት፤ 100 ኛ ዓመትን በማስመልከት ጀርመን ሃገር ወደሚገኘዉ ዋና መስርያቤት ተጋብዘዉ ከሳምንታቶች በኋላ ወደ ጀርመን የሚያቀኑት፤ የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፊሰር አበበ ድንቁ፤ በተጋበዙበት ስብሰባ ላይ የማኅበሩን ስራ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
ሙሉዉን ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉ ላይ ያገኙታል።
አዜብ ታደሰ
ዮኃንስ ገብረእግዚአብሔር