በደቡብ ወሎ በመጠለያ ካምፕ ዉስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች እሮሮ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 12 2017በደብቡ ወሎ ዞን ከተለያዮ የኢትዮጱያ አካባቢ ተፈናቅለዉበመጠለያ ካምፕ ዉስጥ የሚገኙ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ዝናቡ በመጨመሩ መጠለያ ድንዃኖቻቸዉ እየፈረሱና ዝናብ እያስገቡ መሆኑን ተናገሩ።
ለስድስት ወራት አገልግሎት እንዲሰጡ የመጡ የመጠለያ ድንዃኖች ለሶስት አመት ያገለገሉ ሲህን በፀሀይና ዝናብ ብዛት ተቀዳዶ አገልግሎት የማይሰጥበት ደረጃ ላይ ደርሶል ብለዋል። ነፍሰ ጡር እናቶች ህፃናትና አረጋዉያን በከፍተኛ ችግር ዉስጥ እንዳሉም ተነግሯል።
ከ4 ዓመታት በፊት በሞቀ ጎጃቸው ውስጥ ሆነው የክረምቱን መምጣት በጉጉት የሚጠብቁ የሚያርሱ እና የሚያመርቱ ገበሬዎች ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ የሰላም መደፍረሶች ቤታቸውን ትተው የተፈናቀሉት እነኝህ በደቡብ ወሎ ዞን ባሉ 11 የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ቁጥራቸው ከ14 ሺ የሚልቅ ተፈናቃዮች ዛሬ ላይ ግን የተጠለሉበት የሸራ ድንኳን እና ላስቲክ ከክረምቱ ዝናብ የሚያስጥል ሆኖ አላገኙትም፡፡ ለበረከት ሲፈልጉት የነበረው ዝናብም ቤታቸውን አፍራሽ ሆኗል ነው የሚሉት፡፡
‹‹ በክረምቱ ብዙ ሰዎች ተቸገሩብን፤ ዝናብ እየጎዳን ነው በጣም ከብዷል፡፡ አሁን ከሞቱት እኛ እንሻላለን የሚል ነው እንጂ ዝናቡ ከባድ ነው፡፡›› ‹‹የዝናቡ ነገር አላህ ይዞት ነው እንጂ ልብስ ደራርበን ነው የምንተኛው በጣም ነው የተቸገርነው››፡፡
ችግሩ በሕጻናትና ሴቶች ብሷል
በደቡብ ወሎ ዞን የጃሪ ገራዶ መካነኢየሱስ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ነዋሪዎች እንደሚገልፁት ለ6 ወር ተብሎ የተሰጠ የመጠለያ ድንኳን 3 እና 4 ዓመታትን ክረምት ከበጋ አገልግሎ ዛሬ ላይ እኛም ማስጠለል አልቻለም ይላሉ፡፡
‹‹3 ዓመት ሆነው የዛን ጊዜ ለ6 ወር ተብሎ ነበር የተሰጠን መቼም ይሄው 3 ዓመት ሙሉ ተቀመጥንበት ዝናብ እቤት እየገባብን ተቀዷል፡፡ ንፋስ ሲመጣም ይነሳል፡፡››
በመጠለያ ድንኳኖች ውስጥ የሚኖሩ ህፃናት ነፍሰ ጡር እናቶች እና አረጋውያን ችግር ላይ ናቸው የሚሉት ተፈናቃዮቹ የክረምቱ ዝናብ ሳይከብድ እንኳን ሌሊቱን ላስቲክ ለብሰን እያደርን ነው ይላሉ፡፡
‹‹አጥቢዎች ነፍሰጡሮች አሉ፡፡ ህፃናቶችም አሉ፤ በጣም ተቸግረን የምናደርገው ጠፋን ላስቲክ ለብሰው ነው የሚኖሩት ንፋስ ሊያነሳው ደርሷል ድንኳኑን፡፡›› ‹‹ ህፃናቱ እኛ እየተቸገርን እኛን እየመታን እነሱን እየደረብን ነው እንጂ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ይመጣላችኋላ ከላይ እንደርብላችኋለን ይሉናል የመጣም የለም፡፡››
የጤና ስጋት
በዝናብ ምክንያት ከወራት ቆይታ በኋላ የሚሰጥ የምግብ እርዳታ በውሃ እየተበላሸ ነው ይላሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮቹ። በተጨማሪም የዝናቡ መጠን ለበሽታ እየዳረገን ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የተቀመጠው ምግብ ዝናብ ይፈስበታል፤ ዱቄቱ ራሱ እየተበላሸ የዛሬ ሳምንት ጁምአ የተሰጠናት በቆሎም ውሃ ሲፈስባት ተበላሸች፡፡›› ‹‹ ያገኘናት እህልም መቀመጫ አላገኘች በስብሷል፤ ያው የግድ ወዴት ይደረሳል ቢያመንም ሽታውንም እየቻልን ወዴት እንደርሳለን፡፡››
በደቡብ ወሎ ዞንበ11 የመጠለያ ጣቢያዎች ከ14,000 በላይ ሰዎች በመጠለያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንም ባለፉት 4 ዓመታት ያገለገሉ ድንኳኖችን በዚህ ክረምት እንዳያፈሱ ላስቲክ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የሚሉት የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አሊ ሰይድ ናቸው፡፡
‹‹ወደ 4 ዓመት አካባቢ ያገለገለ ድንኳን ስለሆነ እየተቸገሩም ቢሆን ኑረውበታል፤ አሁን ያለው የጥራት ችግር አለበት፤ ግን ለዚህ ክረምት በቂ ነው፡፡ ለቀጣይ ግን ተጨማሪ ነገር ያስፈልጋል፤ በርከት ያለ ፕላስቲክ ተሰጥቷል፡፡ ለዚህም ክረምት አያስቸግርም፡፡››
በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው መመለስ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በደቡብ ወሎ ዞን ያሉ ተፈናቃዮችን ለመመለስ የተደረገ ጥረት የለም ይላሉ አቶ አሊ ሰይድ፡፡
‹‹የፌዴራል አደጋ ስጋት ኮሚሽን ይህንን አስቦ ነው ለጊዜው ክረምቱ እስኪወጣ ሰው እንዳይጎዳ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የፕላስቲክ ሸራ እና የቤት ቁሳቁስ ያቀረቡ መፍትሄው ከካምፕ ቢወጡ ነው ወደ ቀድሞው ቦታቸው ቢመለሱ እነሱን ለመመለስ ምንም እንቅስቃሴ የለም ከላይ እያዳመጥን ነው፤ ምንም ነገር እንደሌለ ታስቦ ነው ባልተለመደ መልኩ ቁሳቁስ የቀረበላቸው፡፡››
በደቡብ ወሎ ዞን 34,000 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እና ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ይኖራሉ፡፡
ኢሳያስ ገላው
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር