በደብረ ብርሀን የተጠለሉ ተፈናቃዮች አቤቱታ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 21 2017ከ2013 ዓም ጀምሮ ከኦሮሚያና ከቤኒሽንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ደብረብርሐን ከተማ “ቻይና”፣ “ወይነሸት” እና “ባቄሎ” በተባሉ መጠለያዎች የሚኖሩ ተፈናቃዮች በመጠለያ እርጅናና በምግብ መዘግየት እጥረት በእጅጉ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተፈናቃዮች መካከል አንዱ ለዶይቼ ቬሌ እንደገለጡት አካባቢው ብርዳማ በመሆኑና ከ4 ዓመታት በፊት የተሰሩ ድንኳኖችና ሸራዎች ባለመቀየራቸው፣ የክረምቱን ብርድ፣ ነፋስና ዝናብ መቋቋም አልቻሉም፡፡ የአልባሳትና የምግብ እጥረትም እንዳለባቸው ነው አስተያየት ሰጪወው የተናገሩት፡፡
ከ3 ልጆቿና ከደካማ ወላጆቿ ጋር እንደምትኖር የገለፀችልን ሌላ ተፈናቃይ ያለው ችግር ከሚባለው በላይ ነው ትላለች፡፡ የችግሩን ሁኔታ እንደዚህ ትዘረዝራለች፣
“... ሶስት ልጆች አሉኝ፣ ከእኔ ጋ አራት ወላጆቸም አሉ በአንድ መጠላያ ድንኳን ቤት ነው የምንኖረው፣ ምግብ በወር ወይ በሁለት ወር አንዴ ቦቆሎ ብቻ ነው የሚመጣልን፣ የምንኖርበት ድንኳን በጣም አሮጌ ነው፣ ዘናቡ ከላይ ይወርዳል፣ ውሀ ከመሬት ይፈልቃል፣ ብርድ ነው፣ ጭቃ ነው፣ የብርድ ለብስ የወሰድን በ2013 ዓም ነው፣ ክዚያ ወዲህ ብርድ ልብስም የለም፣ ድንኳንም አልተቀየረ ችግሩ ከሚባለው በላይ ነው፣ በጣም ከባድ ነው” ብላናለች፡፡
ከምግቡ በላይ የሸራውና ድንኳኑ ሁኔታ ከፍተኛው ችግር እንደሆነም አመልክታለች፡፡
“የመጠለያ ሸራዎችና ድንኳኖች ብርድና ዝናብ መከላከል አልቻሉም” አንድ ተፈናቃይ
እርዳታዎች እየቀነሱ እንደሆኑ የገለፁልን በደብረብርሐን በቻይና የተፈናቃዮች ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃይ፣ ከክረምቱ ዝናብ ጋር በተያያዘም ያረጁ ድንኳኖች ያፈስሳሉ፣ መሬቱ ውሀ ያመነጫል በመሆኑም ለመተኛትም ሆነ ለመቀመጥ አስቸጋሪ ሁኔታ በመጠለያ ጣቢያው እንዳለ ነው የተናገሩት፡፡“ኑሮው ለህፃናት፣ ለአቅመ ደካሞችና ለበሽተኞች ፈተና ነው” ሲሉ አክለዋል፡፡
በአማራ ክልል ለሰሜን ሽዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበባው መለሰ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡን ወደ የእጅ ስልካቸው ያደረግነው አጭር የፅሁፍ መልዕክትና የስልክ ጥሪ ምላሽ አላገኘም፡፡
የተፈናቃዮችን ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው” የአማራ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን
የአማራ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ብርሐኑ ዘውዱ ተፈናቃዮቹ ያነሷቸውን ቅሬታዎች በተመለከተ ተጠይቀው እንደ አጠቃላይ የእርዳታ መቀነስና መዘግየት መኖሩን ጠቅሰው፣ ለተፈናቃዮቹ እርዳታ እንደተጠየቀላቸው አመልክተዋል፡፡ የመጠለያ ድንኳኖችን በተመለከተም ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ እንደቆዩ አስታውሰው አሁንም ጥረቱ እንደሚቀጥል ነው ያስረዱት፡፡ ለችግሮቹ መፈጠር የረጂ ድርጅቶች መቀነስ አንዱ ምክንያት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በደብረብርሐን ከተማ አቅራቢያ በሶስት የተፋናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች 22ሺህ ተፈናቃዮች ሲኖሩ በሌሎች የሰሜን ሽዋ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ደግሞ እስከ ቁጥራቸው እስከ 110ሺህ የሚደርሱ ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ ለማወቅ ችለናል፡፡
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሠ