በዚህ ዓመት በኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ሙሉ በሙሉ ወደ ቄያቸው ይመለሳሉ ተባለ
ሐሙስ፣ የካቲት 6 2017በኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን በዚህ ዓመት መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ወደ ቄዬአቸው እንደሚመለሱ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ ተናገሩ ። በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው ነበር ካሉት አንድ ሚሊዩን ገደማ ዜጎች መካከል 900 መቶ ሺ ያህሉ ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸውን አብራርተዋል፡፡ አንዳንድ ተፈናቃዮች በመናኛ የዳስ መጠለያዎች ውስጥ እንደሚገኙ በመግለጥ ምሬታቸውን አሰምተዋል ። በ2014 ዓ.ም ብዙ ሰዎች የተፈናቀሉበት የምስራቅ እና ሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን ውስጥ አብዛኛው የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ አካባቢአቸው መመለሳቸው ተገልጧል ። ለዝርዝሩ ነጋሣ ደሳለኝ ከአሶሳ ።
ዘጠኝ መቶ ሺህ ሰዎች ወደ ቀያአቸው ተመልሷል
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ በክልሉ ተፈናቀሉ ከነበሩት በሚሊን ከሚቆጠሩ ዜጎች መካከል ጥቂት የሚባሉ ብቻ በጊዜያዊ መጠለያ እንደሚገኙ በክልሉ ምክር ቤት 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ በጅማ፣በምስራቅ ባሌ፣ቦረና እና ምስራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ እና ሃሮ ሊሙ ወረዳ የሚባሉ ቦታዎች በአሁኑ ወቅት የተፈናቀሉ ዜጎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዓመት ለመጨረሻ ጊዜ ኦሮሚያን ከተፈናቃይ ነጻ ለማድረግና ወደ ቤታቸው ተመለሰው መታገዝ እንዳለባቸው በማለም ሰፊ ስራዎች መስራታቸውን አክለዋል፡፡
«ከአንድ ሚሊዩን በላይ የሚሆን ሰው ነው ተፈናቅለው የነበረው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ 9 መቶ ሺ የሚሆኑትን ወደ ቀዬአቸው መልሰናል፡፡ እስከዚህ ዓመት መጨረሻ ደግሞ ሙሉ በመሉ ወደ ቀዬያቸው መልሰን የሚያስፈልገውን ሁሉ እዛው ቀዬው ላይ ድጋፈ እናደርጋለን ብለን እቅድ ይዘን እየሠራን እንገኛለን፡፡ ከተረጅነት ወደ ምርታማነት በሚል መርሀ -ግብር ብዙ ስራዎችን አቀናጅተን እየሠራን ነው፡፡ በቀጣይ ዓመት ደግሞ ከዕርዳታ ነጻ እናደርጋለን ብለናል፡፡ በበረሀማነትና የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ደግሞ «በቡሳ ጎኖፍ» (አደጋ ስጋት ወይም ምግብ ዋስትና) በኩል ምላሽ እንሰጣለን ።»
በ2014 ዓ.ም በነበረው ግጭት ምክንያት ብዙ ሰዎች ከተፈናቀሉበት አካባቢዎች መካከል የምስራቅ ወለጋ አንዱ ሲሆን 210ሺ የሚደርሱ ሰዎች ተፈናቅለው እንደነበር የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡ በዞኑ ስር ከሚገኘው 50ሺ ያህል ህዝብ የተፈናቀለባት ኪረሙ ወረዳ አብዛኘው ሰዎች ወደ አካባቢው ከተመለሰ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡ በ2014 ዓ.ም ከኪረሙ ወረዳ ተፈናቅለው ጊዳ አያና የተባለ ወረዳ ከቆዩ በኃላ በአሁኑ ወቅት ወደ ወረዳቸው መመለሳቸውን ነገሩን ነዋሪ በሰጡን አስተያየት በወረዳው 8 በሚደርስ ቀበሌ ውስጥ የነዋሪ መኖሪያ ቤት በወቅቱ በነበረው ግጭት መውደሙን ተናግረዋል፡፡ በከተማ አቅራቢያ የሚገኙ የተወሰኑ አርሶ አደሮችም ባለፈው ክረምት ወደ ግብርና ምርት የገቡ ሲሆን በበረሀማ አካባቢዎች ደግሞ ዳግም ወደ ከተማ የተፈናቀሉ እንዳሉም አንስተዋል፡፡
ቤታቸው የወደመባቸው ሰዎች አሁንም በሸራ በተሰራ መጠለያ ውስጥ እየኖሩ ይገኛሉ
‹‹ ጊዳ ውስጥ አርብ ገበያ የሚባል ቦታ ነው የነበር ነው አሁን ወደ ቀዬአችን ተመልሰናል፡፡ በግጭት ወቅት ከብቶቻችን ስተዘረፈና ንብረታችን ስለወደመ ማረስ አልቻልነም፡፡ ቤታችን ተመርጦ ነወ የተቃጠለው አሁንም መኖሪያ ቤታቸው ያልተቀጠለው በቤታቸው ተመልሰዋል ቤታቸው የተቃጠለባቸው ደግሞ በሸራ በተሰራ መጠለያ እና ዘመድ ቤት እየኖሩ ይገኛሉ፡፡››
ከምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ተፈናቅለው በ2014 ዓ.ም ወደ አማራ ክልል ሸሽቶ ከነበሩት መካከል ባለፈው ዓመት የተወሰኑት ከጃራ ካምፕ ወደ ወረዳው ተመልሰዋል፡፡ በጊምቢ ወረዳ ቶሌ በሚባል ቀበሌ ከተመለሱት መካከል እንደዚሁም የተወሰኑት ሰልጥና በቆሎ ባለፈው ክረምት ማምረታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህ አካባቢም በግጭት ወቅት በርካታ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸው የተነገረ ሲሆን መኖሪያ ቤታቸው ያልተጠገነላቸው ነዋሪዎች በቦታው በተዘጋቸላቸው ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሰዎች ተፈናቅለው የነበሩ ሲሆን በዞኑ አሙሩ ወረዳ ከ40ሺ በላይ ሰዎች ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን የወረዳው አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት ቡሳ ጎኖፍ ከዚህ ቀደም ይፋ አድርገዋል፡፡ በዞኑ ሻምቡ የተባለ ከተማ ቆይቶ ወደ ቤታቸው ከተመሰሉት መካከል አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ አርሶ አደሩ መሉ በመሉ ያልተቋቋመ ቢሆን በከተማ አቅራቢያ ያሉ በተመሳሳይ በክረምት ወቅት ወደ ግብርና ስራ ገብተዋል፡፡ አልፎ አልፎ አሁንም በወረዳው ግጭቶችና እገታዎች እንደሚስተዋልም ነዋሪው ተናግረዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ‹‹ኦቻ›› በምዕራብ ኦሮሚያ ብቻ ከግማሺ ሚሊዩን በላይ ህዝብ ተፈናቅለው እንደነበር በዘገባው አመልክተዋል፡፡
ነጋሣ ደሳለኝ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ